የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው በአልደፈርም ባይነት ጐልቶ ይታያል። እጄን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም ብለው እራሳቸውን ከሰዉት አፄ ቴዎድሮስ እስከ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መሣሪያ እስከታጠቁት ድረስ በርካታ ታሪኮች ተፈጽመዋል። እነዚህንም ባለውለታዎች በርካታ ምሑራንና ጸሐፍት እንዲሁም ፖለቲከኞች ሲያወድሷቸውና ሲዘክሯቸው ዘመናትን አስቆጥረዋል።
የሀገር ባለውለታዎች እትብታቸው በኢትዮጵያ ምድር የተቀበረ እና በሥጋ በደም ኢትዮጵያውያን የሆኑት ብቻ አይደሉም። ከማሕፀኗ ሳይወለዱ ከሩቅ አገር ባሕር ተሻግረው ለኢትዮጵያ ነፃነት የተዋደቁላት ልበ ኢትዮጵያውያኖችም ብዙ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ጥቁር አሜሪካዊው ፓይለት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ነው።
አፍሪካ አሜሪካዊው ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን ተወልዶ ያደገው በአሜሪካ ፍሎሪዳ ግዛት ውስጥ ነው። የልጅነት እድሜውን ከእናቱና ከእንጀራ አባቱ እንዲሁም በአራት ዓመት ከምትበልጠው እህቱ ጋር በመሆን በሚሲሲፒ ባሕረ ሰላጤ የወደብ ከተማ አሳልፏል።
ትንሹ ሮቢንሰን እንደ አዕዋፋት በሰማይ የመብረር ፍላጐት ያደረበት ገና በሕፃንነቱ ነበር። የሰባት ዓመት ታዳጊ በነበረበት ወቅትም አውሮፕላን መሰል ተንሳፋፊ በማዘጋጀት ወደ ሚሲሲፒ የባሕር ወደብ አምርቶ እንደነበር መዛግብት ያወሳሉ።
ሮቢንሰን የቀለም ትምህርቱን በ1919 በአውሮፓውያኖቹ የቀን ቀመር በባሕረ ሰላጤ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በዚህ ጊዜም የሥነ እንቅስቃሴ ኃይልንና የመኪና እቃዎችን ምንነት የማወቅ ፍላጐቱ እጅግ የናረበት ነበር። ይሁን እንጂ አፍሪካ አሜሪካውያን ከ10ኛ ክፍል አልፎ የመማር እድል ስላልነበራቸው ሮቢንሰን በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ሆኖ ትምህርቱን መቀጠል አልቻለም።
በመሆኑም ሮቢንሰን ወደ ደቡብ ምዕራባዊው የአሜሪካ ክፍል አልባማ ከተማ ለማምራት ተገደደ። መስከረም 1921 የአውቶሞቲቭ ማሽን ሳይንስ ለማጥናት ቸስኪጊ ወደተሰኘ ተቋም አመራ። ከሦስት ዓመት የትምህርት ዘመን በኋላ ተመርቆ የወጣው ሮበን የአውቶሞቢል፣ የአፈታሪክ፣ ሥነጽሑፍ፣ የድርሰትና የታሪክ ትምህርትንም በተጨማሪነት ተከታትሏል።
በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እራሱን የማሳተፍ ፍላጐትና የበረራ ፍቅር በውስጡ የሚንተገተግበት ሮቢን ቺካጐ ለሚገኘው የበረራ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በተደጋጋሚ ቢያመለክትም ተቀባይነትን አላገኘም። ሁኔታዎች እስኪመቻቹለት ድረስም በፅዳትና ተላላኪነት መሥራት ጀመረ። ሆኖም ቆየት ብሎ በአንድ አሠልጣኝ አማካኝነት ሥልጠናው ከተመቻቸለት በኋላ ሮቢን የመጀመሪያው ጥቁር የበረራ ተማሪ በመሆን ከነጮቹ ጋር እኩል ወንበር ላይ ተሰየመ። በጥቁርነቱ በትምህርት ቤቱ ታሪክ የመጀመሪያም ሆነ።
የሮቢንሰን የሥራ ተሞክሮ፦
ሮቢንሰን ወደ በረራ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ከመግባቱ አስቀድሞ በጫማ ማስዋብ ወይንም እንደ ሀገራችን “ሊስትሮ” ሥራ ላይ ተሰማርቶ ነበር። እትብቱ በተቀበረባት በባሕረ ሰላጤ የወደብ ከተማ ቢሲሲፒ ምንም አይነት ሥራ ለማግኘት አልታደለም። በነጮች የሚመራ ጋራዥ ውስጥ የመሥራት አጋጣሚውን ቢያገኝም የሚደርስበት መገለል ሠላም ነሳው።
በአንድ ወቅት ለአባቱ “የጋራዥ ባለቤቶች እንድሠራ የሚፈቅዱልኝ ማፀዳዳት፣ የጋዝ ታንከር መሙላት፣ ጐማ መቀየር ወይንም ማጠብ ብቻ ነው። እኔ ግን የመካኒክነት ሙያ አለኝ። በሙያዬም ስለ አውቶሞቲቭ ሳይንስ ስነግራቸው እርስ በእርስ ተያይተው ይስቁብኛል። ምንም ነገር የማልችል አድርገውም ይቆጥሩኛል” በማለት ተናግሮ ነበር።
ሮቢንሰን በመቀጠል ወደ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ መቀመጫ ከተማ ወደሆነችው ዲትሪዮት ነበር ያመራው። እዚህም ቢሆን የሥራውን መስመር ለማግኘት እጅግ ተቸግሯል። የቀድሞውን ተሞክሮ በመጠቀም በፅዳትና ተላላኪነት ተቀጠረ። ቀስ በቀስም ወደ ረዳት መካኒክነት ተዘዋወረ። አሁንም በነጮች የሥራ ባልደረቦቹ መገለል ይደርስበት ነበር። ይህንንም በመልካም ጐኑ ለቀረባቸው ነጭ የሥራ አጋሮቹ ያጫውታቸዋል። ልምዱንም ያካፍላቸዋል። በዚህም ችሎታውን እያስተዋወቀ በመምጣቱ ከረዳትነት ወደ ዋና መካኒክነት እንዲሁም ከፍተኛ ሜካኒክ መሆን ቻለ።
የሮቢንሰን የበረራ ሕይወት፦
በመካኒክነት ሙያው ስኬትን እያጣጣመ የመጣው ሮቢንሰን በአየር ላይ ለመንሳፈፍ የሚያስችለውን አጋጣሚ ማማተር ጀመረ። ለመስክ ሥራ በሚወጣበት አጋጣሚ ከፓይለት ሮበርት ዊልያም እና ፐርሲ ጋር ይገናኛል። ለዋኮ 9 (WACO 9 ) የመጀመሪያ ክፍያውን በመፈፀም በረራ አካሄደ። ወደ ችካጐ በመመለስም ጋራዥ ከከፈተ በኋላ ወደ ከርቲስ ራይት የአብራሪዎች ማሠልጠኛ ማመልከቻ ያስገባል። እንደተለመደውም ተቀባይነት አላገኘም። በጎን አጋጣሚ ተጠቅሞ የመሄድ ልማድ ያለው ሮቢን አሁንም በጠራጊነት ማሠልጠኛውን ተቀላቀለ።
ሮቢንሰን በአንድ ምሽት የበረራ አሠልጣኙ ለተማሪዎቻቸው በሚያስረዱት ወቅት በደንብ አደመጠ። ያዳመጠውንም በተግባር ለመሥራት ሞከረ። የራሱ አውሮፕላንም ሠራ።
በዚያች ምሽት ሙከራ አደረገባት። ሮቢንሰን ወደሚያፀዳው ክፍል የገቡት መምህሩ አቶ ኢንደርሰን እጅግ ይደነቁና ከበረራ አሠልጣኙ ሚስተራ ሲንዲራ ጋር ያገናኙታል። ፍቃድ ያለው አብራሪ ያደርጉታል። አልፈውም በማሠልጠኛው ውስጥ ካሉ ሠልጣኞች ጋር ተቀምጦ ትምህርት እንዲከታተል ዕድሉን አመቻቹለት። የፓይለት /የአብራሪነት/ ማዕረግም ተጐናፀፈ። በመቀጠልም ብርኔሊየስ ኮፊ ከሚባል ጓደኛው ጋር በመሆን የማብረር ፍላጐት እያላቸው ግን ያልቻሉትን የአፍሪካ አሜሪካዊ ችግር መፍታት የሚችል የፓይለቶች ማኅበርን መሠረቱ።
የበረራ ማሠልጠኛዎች ለአፍሪካ አሜሪካውያን በራቸውን መዝጋት እንደሌለባቸው የወሰኑት ሮቢንስንና ጓደኛው ኮርኔሊየስ ኮፊ ሮቢንስ አሊኖስ የተሰኘውን የአውሮፕላን ጣቢያ ከፈቱ። የጥቁር ፓይለቶችን ይበልጥ ለማበረታታት ሮቢንሰንም የቀድሞውን ቱስኪን ተቋሙን ወደ በረራ ማሠልጠኛነት አሳደገው። በርካቶችንም መታደግ ቻለ።
ሮቢንሰን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፦
እንደ ጐርጐሮሳውያኑ የቀን ቀመር በ1935 ሮቢንሰን ኢትዮጵያን መርዳት እንደሚፈልግ አሳወቀ። የነጮች በጥቁሮች ላይ የበላይ መሆን ሠላም የማይሰጠው ሮቢንሰን ኢትዮጵያ ላይ ኢጣሊያ ባንዣበበችበት ወቅት በኔግሮ ፕሬስ ስፖንሰር አድራጊነት ጥቁር የቢዝነስ ባለቤቶች እና የማኅበረሰብ መሪዎች ምክክር መድረክ ላይ በመገኘት ነበር ኢትዮጵያን ለመርዳት ያለውን ፍላጐት ያሳየው።
በዚህ ጊዜም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአክስት ልጅ ዶክተር መላኩ በየነ ጋር መገናኘትና መነጋገር ችለዋል። ዶክተሩም ጥያቄውንም ለአፄ ኃይለ ሥላሴ አቅርበውላቸዋል። ንጉሡም የሮቢንሰንን ጥያቄ ስለመቀበላቸው በቴሌግራፍ አሳወቁት።
ጥያቄው ተቀባይነት ያገኘበት በርካታ ምክንያቶች አሉት። አንደኛውና ዋነኛው የሮቢንሰንና የሥራ ባልደረቦቹ በፖለቲካውና በውትድርናው ዓለም ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረጋቸውና ኢትዮጵያ ላይ በፋሽስቱ የኢጣሊያ ጦር ወራሪ ኃይል ለመመከት በፍላጐቱ መነሳቱ። ሌላኛው አጋጣሚ ደግሞ በአሜሪካ የአየር ጦር ኃይል ውስጥ የጥቁሮች መብት ውስን በመሆኑ ሮቢንሰንና መሰል ጓደኞቹ ለጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት ከሆነችው አፍሪካዊት ሀገር ጎን እንዲሰለፉ ምክንያት ሆኗል።
በኢትዮ ኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ የንጉሡን ጦር ከፊት ሆኖ በመምራት ዘመተ። በጋዝ የተሞሉ ቦንቦችን የተሸከሙ የኢጣሊያ ጦር መሣሪያዎች በንፁሐን ኢትዮጵያውያኖች ላይ ስለደረሱት ጉዳት እውነተኛ ምስክር ነው።
ምንም የጦር መሣሪያ ያልተጠቁ ነገር ግን ሙሉ ወኔ ያነገቡ የኢትዮጵያ ወዶ ዘማቾችን ሲያይ የጣሊያን ጦር ወደ ኋላ ባፈገፈገበት ወቅት በተተኮሰ ጥይት ሮቢንሰን ተጐዳ።
ሆኖም ግን መልሶ ለመተኮስ ሙከራ አላደረገም። የጣሊያን ጦር እንደገና በማንሰራራት በአዲስ አበባ የጥፋት ዘመቻውን ከፈተ። ሮቢንሰንም የኢጣሊያን ጦር መመከት የሚያስችል ጉልበት አዳብሮ በመመለስ ዳግም ጦርነት ገጥሟል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር የኢጣሊያን ጦር ከኢትዮጵያ በወጣበት በ941 ዓ.ም ሮቢንሰን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል። ኮሎኔል ሮቢንሰን ከሌሎች አፍሪካ አሜሪካውያንና ከወቅቱ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስቴር ይልማ ዴሬሳ ጋር በመሆን የንጉሠ ነገሥቱን አየር ኃይል ግንባታን አከናወነ።
ኮሎኔል ሮቢንሰን ከልዑል መኮንን ጋር በመሆን የአብራሪዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈተ። በዚህም የሲቪል ንግድ ዘርፉን ተቀላቀለ። ብሎም በሀገሪቷ በርካታ ከበረራ ጋር በተያያዘ የሚውሉ ክስተቶች መታየት ጀመሩ። በምሥራቅ አፍሪካም በኮሎኔል ሮቢንሰን አማካኝነት የተከፈተው አቪዬሽን ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም አድርጓታል።
ለበርካታ አስርተ ዓመታት የኢትዮጵያን አየር መንገድ ሲያገለግል የቆየው ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰን ሕልፈቱም በዚሠችው በደከመላት ሀገር በደረሰበት የአውሮፕላን አደጋ ነው።
“ቡናማው ጭልፊት” በሚባል ተቀጥያ የጀብዱ ስም የሚጠሩት ኮሎኔል ሮቢንሰን በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እጅግ የጎላ ሚና መጫወታቸው ይነገርላቸዋል።
ኮሎኔል ሮቢንሰን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተቀሰቀሰባቸው የመጀመሪያ ዓመታት የግርማዊነታቸውን አየር ኃይል ለመመሥረትና ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ ያደረጉ ከመሆኑም በላይ ዛሬ ሥማቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ በስኬትና በጥንካሬ ከሚጠራ ገናና አየር መንገዶች አንዱ ለሆነውና በአፍሪካ አቪዬሽን ግዙፉና ግንባር ቀደሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መፈጠር መሠረት የጣሉ ባለሙያ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል።
ኮሎኔል ሮቢንሰን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲያከናውኗቸው የነበሩ ውጤታማና ፋና ወጊ ተግባሮች አሜሪካም ውስጥ እየታወቁና ልዩ ትኩረት እያገኙ በመምጣታቸው በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይሎች ውስጥ በሚያገለግሉ ጥቁር ወታደሮች ላይ የነበረው የተዛባ አመለካከት በጠንካራ ገፅታ እንዲለወጥና የሚገባቸውን ክብር እንዲያገኙ የጎላ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አዲስ አበባ የሚገኘው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ከጥቂት ዓመታት በፊት ያወጣው የፕሬስ መግለጫ ያስታውሳል።
በዚህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ የተባበሩት ኃይሎች በሰሜን አፍሪካና የጣሊያን የጦር አውድማዎች ላይ ለተቀዳጇቸው አንፀባራቂ ድሎች ጉልሁን ገድል የፈፀሙ ጥቁር አሜሪካውያን ጄት አብራሪዎች ብቻ የተሣተፉበት ግዳጅ እንዲሳካ “ቡናማው ጭልፊት” ምክንያት ሆነዋል።
ያኔ በኮሎኔል ሮቢንሰን የተቋጠረው ግንኙነት ዛሬ በአቪዬሽን መስክ ኢትዮጵያና ዩናይትድ ስቴትስ አጠናክረው ለቀጠሉት የንግድና የደኅንነት ትስስር፣ እንዲሁም የአየር ጣቢያዎች አስተማማኝነት የተቀናጁ ሥራዎች መሠረት የጣለ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአሜሪካ ኩባንያዎችና የዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ተቋማት ትብብሮቻቸውን ማፅናታቸውና ማጥበቃቸው ይነገራል።
እኛም በዚህ ለሀገር የላቀ አበርክቶ ያኖሩ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች በሚመሰገኑበት ዓምድ የኢትዮጵያ አቪዬሽን አባት ተብለው የሚታወቁትንና እትብታቸው በኢትዮጵያ ምድር ሳይቀበር በሥጋ በደም ኢትዮጵያዊ ባይሆኑም ለፍትሕ ተሰልፈው ለኢትዮጵያ መስዋዕትነት የከፈሉትን ጥቁር አሜሪካዊው ፓይለት ኮሎኔል ጆን ቻርለስ ሮቢንሰንን አመሰገንን። ሰላም!
ለዚህ ፅሑፍ እንደ ምንጭነት የተለያዩ ማኅበራዊ ድረገፆችን ተጠቅመናል።
ክብረዓብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2016 ዓ.ም