አዲስ ዘመን ድሮ

ትናንት ለመላው ኢትዮጵያ የመረጃ ቋት ነበረ። በእነዚህ ትናንቶች ውስጥ ያለፉት መረጃዎች ዛሬ ላይ የታሪክ ማህደር ነጸብራቆች ሆነው ይታያሉ። ሁሉንም ነገሮች በአዲስ ዘመን ድሮ መስታወት ፊት ቆመን የድሮዋን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ምስል እንመለከታለን። በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ክስተትና ታሪኮች ሁሉ በአዲስ ዘመን ድሮ ውስጥ ተሰንደው ተቀምጠዋል። እኛም ተገልጦ ከማያልቀው ክምችት ውስጥ የመራረጥናቸውን ጥቂት ጉዳዮች እናካፍላችሁ። የጋዜጠኞች ማህበር ጉባኤ ስላስተላለፈው ውሳኔ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ በአንድ ወቅት አንድ የሆነ ችግር አጋጥሞት ነበር፤ ለመሆኑ የገጠመው ችግር ምን ይሆን…ውስኪ ያልሆነን ነገር ውስኪ ነው እያሉ ለብዙዎች እያከፋፈሉ ስለነበሩት አጭበርባሪዎች….እንዲሁም ደግሞ ከመፍትሔ ቢሆንዎ ገጽ ላይ አንዲት ግለሰብ ጓደኛዬ የወሰደውን ድንግልና ውለጂ እያለ ክፉኛ ያስጨንቀኛልና መላ በሉኝ ያለችበትን አስገራሚ ዘገባ እንደሚከተለው እናስታውሳችሁ።

የጋዜጠኞች ማህበር ጉባኤ ውሳኔ አሳለፈ

(ኢ.ዜ.አ)- ክልሎች ከዋናው ማህበራቸው የሚወርድ መመሪያ ሳይጠብቁ በራሳቸው አቅም ሊፈጽሙዋቸው የሚገቡ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችል መመሪያ እንዲቀረጽ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር የምክር ቤት ጉባኤ ወሰነ።

ለሁለት ቀናት የቆየው የማህበሩ ምክር ቤት ጉባኤ እሁድ ሲጠናቀቀ ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው፤ ይህንኑ ተግባራዊ የሚያደርግ የማህበራት ጉዳይ ኮሚቴ በማዕከል ተቁቁሞ የግኑኙነት መመሪያና አጠቃላይ መርሀ ግብር ይነድፋል።

ጉበኤው ባወጣው መግለጫ ቀደም ሲል ማዕከሉ ከክልሎች ጋር የነበረው የግንኙነት መስመር በውል ያልታወቀ፣ የሥራ ክፍሉም በግልጽ ያልተመለከተ እንደነበርና በዚህ ረገድ አያሌ ችግሮች መከሰታቸውን አውስቷል።

(አዲስ ዘመን፣ የካቲት 19 ቀን 1989 ዓ/ም)

አየር መንገድ አሳሳቢ ችግር ውስጥ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፎከር ከተባለ የሆላንድ ኩባንያ አምስት አውሮፕላኖችን ለመግዛት ተዋውሎ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከስሮ በመዘጋቱ በቀብድ መልክ የተከፈለውን 7 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር / ከ33 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ/ የማስመለሱ ተግባር አጣዳፊና አሳሳቢ መሆኑን የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ዶ/ር አህመድ ቀሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ በጽ/ቤታቸው ለተገኘው ለፕሬስ ጋዜጠኞች ቡድን በሰጡት መግለጫ አየር መንገዱ ውሉን በሚፈጽምበት ጊዜ ጭምር ፎከር የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ እንደገባ ያውቅ እንደነበር ገልጸው፤ ነገር ግን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ጨርሶ ይዘጋል ተብሎ እንዳልተገመተ አመልክተዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኩባንያው ለመግዛት የተዋዋለው አምስት አውሮፕላኖች ዋጋ 87 ሚሊዮን ዶላር ነው። ውሉ ሰፊ ሲሆን፤ የጥገና ማዕከል መስራት፣ 2 ሺ ሰላሳ የሚሆኑ የተለያዩ መለዋወጫዎችን መስራት፣ሥልጠና ማካሄድና የመሳሰሉትን የሚያካትት ነው።

(አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 27 ቀን 1988 ዓ/ም)

የመጀመሪያ ዙር የኃይል ማመንጫ ግንባታ እየተካሔደ ነው ተባለ

(ኢ.ዜ.አ)- የግልገል ጊቢ ሃይደሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ግንባታ ሲጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ስድስት የማመንጫ ጣቢያዎች የሚይዘውን 340 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 480 ከፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክና መብራት ኃይል ባለሥልጣን አስታወቀ።

……….

እንደ ሥራ አስኪያጁ አባባል ከሆነ ፕሮጀክቱን በአዲስ መልክ ለማዋቀር ያስፈለገበት ምክንያት ቀደም ሲል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው መንገድ ባለመዋቀሩና ባለፉት አስር አመታትም በተጓዳኝ ስራዎች ላይ ብቻ ሲያዘግም በመቆየቱ ነው።

ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሌለው ዓይነቱ አወቃቀርም አስተዳደራዊ በደልንና ሙስናን ለማስወገድ ከማስቻሉም በላይ የጊዜ ብክነትንም እንደሚያስወግድ አስታውቀዋል።

(አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 27 ቀን 1988 ዓ/ም)

ሐሰተኛ ውስኪ ሲያከፋፍሉ የተገኙ ተያዙ

የአዲስ አበባ መስተዳድር ፖሊስ ኮሚሽን የተለያዩ የአልኮል መጠጦችን የተወሰነ መጠን ካለው ውስኪ ጋር በመቀላቀል እውነተኛ ውስኪ አስመስለው እየቀመሙ በሽያጭ አከፋፍለዋል ያላቸውን ሶስት ሰዎች ሰሞኑን መያዙን አስታወቀ።

በወረዳ 10 ቀበሌ 05 ውስጥ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ይህንኑ ሐሰተኛ ውስኪ የሚሰሩት ሰዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት ለዞን አራት ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በደረሰው የሰዎች ጥቆማ መሠረት እንደሆነ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ የመቶ አለቃ ያሬድ መለሰ ገልጠዋል።

………………….

በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑት ግለሰቦች ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ በዚህ ስራ ከተሰማሩ ሁለት ዓመት እንደሚሆናቸውና ይህንንም ምርታቸውን የሚያከፋፍሉት እዚህ አዲስ አበባ ለሚገኙ ደንበኞቻቸው መሆኑን ገልጠዋል።

(አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 27 ቀን 1988 ዓ/ም)

ጓደኛዬ የወሰደውን ድንግልና ውለጂ እያለ ክፉኛ ያስጨንቀኛል

ጥያቄ – ለኔ የመጀመሪያ የምለው ጓደኛዬ ጋር ከተዋወቅን ሁለት አመት ሊሆነን ነው። በእርግጥ ለመተዋወቅ ብዙ ጊዜ ጨርሶብናል። በዚህ ጊዜም “የሚዋደዱና የሚተማመኑ ጓደኞች ላይ ላዩን ይሄዳሉ” ስላለኝም አምኜው ሄድንበት። በዚህም ጉዞ ያመኝ ነበር። በዚህ መልኩ 6ወር ከቆየን በኋላ ልጃገረድ አይደለሽም ከሚልበት ደረጃ ላይ ደረስን። እኔ እንኳንስ ለዚህ የሚያበቃኝን ስሞኛል የምለው ጓደኛ አልነበረኝም። በጣም የባሰብኝ ደግሞ በትንሽ ነገር የተነሳ የሚያወርድብኝ የስድብ ናዳ ነው። ይልቁንም “አንቺ እኮ እንደዚህ ነሽ፣ እኔ ሕጻን ወይስ ምንም የማላውቅ መሐይም መሰልኩሽ? ልታታይኝ ነው? ያልተነካ ነው እንጂ የጠፋው ትርፍራፊማ ሞልቷል” እያለ በጠበጠኝ። ከዚህ የተነሳ በጣም ተጨነቅሁ።

ሰላም

(አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 16 ቀን 1988 ዓ/ም)

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You