በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሴቶች ተጠቃሚነትን ለማሳደግ

በዲጂታል ዘመን ቴክኖሎጂ በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ እየሆነ ይገኛል። ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ ቢሆንም ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እየሆነ አለመሆኑ ይነገራል። መረጃዎች እንደሚያመላክቱት አሁንም ድረስ በዓለም ላይ ግማሽ ያህሉ ሕዝብ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ተጠቃሚ አልሆነም። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ሴቶች አብዛኛው ቁጥር ይይዛሉ።

የዓለም አቀፍ ቴሌኮም ሕብረት ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ በዓለም ካሉ ሴቶች ውስጥ 52 በመቶ ያህሉ የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ተጠቃሚ አይደሉም። የሴቶች የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ተጠቃሚነትም እንዲሁ ከወንዶች ጋር ሲነጻጻር አነስተኛ ነው።

በተለይ በይነ መረብ (ኢንተርኔት) ተደራሽነት ባልተስፋፋባቸው ታዳጊ ሀገራት ደግሞ ችግሩ ከዚህም የባሰ ስለሆነ የሴቶች ተጠቃሚነት በእጅጉ አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከዲጂታል ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየተጓዘ ባለበት በዚህ ዘመን ደግሞ አብሮ መጓዝ የሚያስችለው ዲጂታል እውቀት ስለሚያስፈልግ የሴቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲሻሻልና አቅማቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ በምታደርገው ሂደት በመንግሥት ሆነ በግሉ ዘርፍ የሴቶችን ዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ሰሞኑን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ የሚሠራ ‹‹ስቲም ፓውር›› የተሰኘ ዓለም አቀፍ ተቋም በኢትዮጵያ 741 ሴቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ አሰልጥኖ አስመርቋል። በኢትዮጵያ የስቲም ፓወር ኃላፊ ስሜነው ቀስቅስ (ዶክተር) እንዳሉት ፤ ‹‹ስቲም ፓውር›› በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚሠራ 14 ዓመት በፊት የተቋቋመ ድርጅት ነው። የተቋቋመበት ዋና ዓላማ የዩኒቨርሲቲ፣ የኮሌጅ፣ የሁለተኛ ደረጃና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው።

‹‹ስቲም ፓውር›› በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በሒሳብ ትምህርቶች እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ይሠራል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ 65 የሚደርሱ የላብራቶሪ ማዕከላት በማቋቋም ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በተማሪዎቹ ማዕከላቱ ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያገኙና ባገኙት ትምህርት የአካባቢው ችግር በቴክኖሎጂ እንዲፈቱ በማድረግ የሚያበረታታት ነው።

‹‹ስቲም ፓውር›› በትምህርት ላይ ያልሆኑ አቅም ያላቸው ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች የሥራ እድል እንዲፈጥሩና ዲጂታል እውቀት እንዲኖራቸው ለማድረግ የተለያዩ ሥልጠናዎች በመስጠት ብቁ ዜጎች ለማፍራት እየሠራ መሆኑን ስሜነው (ዶ/ር) ይገልጻሉ። በመሆኑም ከፊላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዙሪያ በመጀመሪያ ዙር ያሠለጠናቸውን 741 ሴቶች ማስመረቁን ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት በዓመት አንድ ሺ ሴቶች ለማሠልጠን ታቅዶ የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን ሥልጠናውን ለመውሰድ የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር በርካታ በመሆኑ በመጀመሪያ ዙር ብቻ 741 ሴቶች አሠልጥኖ ማስመረቅ መቻሉን አመላክተዋል። ሥልጠናው በዘጠኝ የሥልጠና አይነቶች በበይነ መረብ (በኢንተርኔት) በኦንላይን ለሶስት ወራት ያህል የተሰጠ ሲሆን ሥልጠናውን ጨርሰው ያጠናቀቁና ብቁ የሆኑት መመረቃቸውን ያመላክታሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ በሥልጠናው ኢትዮጵያውያን ሴቶችና ወጣቶች በዲጂታል እውቀት ዘርፍ ተሠማርተው ዓለምን እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ነው። ሥልጠናው ከፊላንድ ኤምባሲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሦስት ወራት የተሰጠ ነው። ይህ የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ የተያዘው ሥልጠና ለሦስት ዙር ይሰጣል። የተመረቁት ሴቶች የመጀመሪያ ዙር ያለፉ ናቸው። ተማሪዎቹ በቀጣይ ተጨማሪ ሥልጠናዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ባለፈም ሥራ የሌላቸው ትልልቅ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን እንዲቀላቀሉ የሚያደርግበትና ሥራ ያላቸው ደግሞ የተሻለ ነገር እንዲያገኙ ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል። ድርጅቱ አሠልጥኖ የሚለቅ ብቻ ሳይሆን ሥራ እንዲያገኙና የራሳቸው ድርጅት እንዲፈጥሩ ማስቻል ላይ ይሠራል ሲሉ አስረድተዋል።

ሥልጠናውን በዲጂታል እውቀት በየትኛውም የሙያ ዘርፍ የሠለጠነ ሁሉ መቀላቀል ይችላል የሚሉት ስሜነህ (ዶ/ር)፤ ያመለከቱት ሁሉም መሠልጠን የሚችሉ ቢሆንም አሁን ላይ በዘርፉ ያላቸው ልምድ ታይቶ የሚመረጥ ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ በመሆኑም ‹‹ስቲም ፓውር›› ያለው አቅም ትንሽ ስለሆነ ያመለከቱት ሁሉ ማሠልጠን አልተቻለም ይላሉ። በዚሁ መሠረት በመጀመሪያ ዙር እንዲሠለጥኑ የተደረጉት ሴቶች በዲጂታል እውቀት ያላቸውም ሆነ በአይሲቲ፣ በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ሳይንስ ዙሪያ ልምድ ያላቸው ተመራጭ ሆነዋል። ‹‹ከአቅም አንጻር እንጂ ዲጂታል እውቀት ለሁሉም አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም በቀጣይ በዲጂታል ላይ ለሴቶች ሥልጠና መስጠቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› በማለት ተናግረዋል።

እንደስሜነው (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ ሥልጠናው በሳይበር ደህንነት፣ ዳታ አናሊሲስ፣ ዌብ ዴቨሎፕመንት እና መሰል የዲጂታል ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። የመጀመሪያና ዋነኛው የሳይበር ደህንነት ሥልጠናም ተሠጥቷል። ሳይበር ደህንነት ተቋማት ላይ ብቻ የሚጠበቅ ሳይሆን የእያንዳንዳችን የራሳችንን ዳታ ለመጠበቅ የሚያስፈልግ ነው። እንደሀገር የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ ስለጸደቀ ግለሰቦችም የራሳቸው ዳታ መጠበቅ ላይ እውቀቱ እንዲኖራቸው ሥልጠናው ተሠጥቷቸዋል። በተጨማሪም ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ ዌብ ሳይቶችና መተግበሪያዎች በማበልጸግ ለግለሰቦች፣ ለተቋማት እና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀገራት ማቅረብ የሚያስችላቸው ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ተደርጓል።

ሥልጠናውን በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ደረጃ ሥራን ለመፍጠር እንደሚያስችል ስሜነው ዶ/ር ያመላክታሉ። የሚሰጠው ሰርተፊኬትም ታዊቂነት ያለው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ኮርፖሬሽን /IBM/ የሚሰጠው ዓለም አቀፍ እውቅና የሚያስገኝ በመሆኑ ሥልጠናውን ያገኙ ሴቶች በዓለም ላይ ባሉ ተቋማት ተቀጥረው መሥራት ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ሠልጣኞቹ እንደሀገር ኢትዮጵያ ለጀመረችው ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የራሳቸው ሚና ይጫወታሉ ያሉት ስሜነው (ዶ/ር)፤ ቴክኒካል እውቀትን ይዘው ስለሚወጡ በመንግሥት ተቋማት ሆነ በግሉ ዘርፍ ቢሰማሩ የራሳቸው ሚና እንደሚጫወቱ ይገልጻሉ። በተጨማሪም አዳዲስ መተግበሪያዎችንና ዌብሳይቶችን በማልማት ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹በሌላ በኩል ሠልጣኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጭ ብለው በዓለም ላይ ባሉ ድርጅቶች ተቀጥረው መሥራት ይችላሉ›› ያሉት ስሜነው (ዶ/ር)፤ ይህንንም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ የሳይበር ደህንነት ስጋት የሠለጠኑት ሥልጠና ሳይበር ጥቃትን በመከላከል እና እንደሀገር ያለውን አቅም ማሳየት የሚችሉ ናቸው። ይህ በቂ ላይሆን ስለሚችል ተጨማሪ የእውቀት ሥልጠናዎችን በመውሰድ የተሻለ አስተዋጽኦን ያበረክታሉ ተብሎ ይታሰባል ሲል ያስረዳሉ።

‹‹ስቲም ፓውር›› ከዚህ በተጨማሪ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በጣም ብዙ ሥራዎች ይሠራል። እንዲሁ በሮቦቲክስም 20 በሚሆኑ ማዕከላት የሁለተኛ ደረጃና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ የሮቦቲክ ውድድር ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ሥልጠና እየተሰጠ ነው። በተጨማሪ በክረምት ወራት በ65ቱም ማዕከላት ለበርካታ ወጣቶች ሥልጠና በመስጠት በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄድ የዓለም ሳይንስ ቀን ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ አፍልቀው እንዲወዳደሩ በማድረግ በማበረታታት ሽልማት እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር ሠልጣኞቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የስቲም ፓወር ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ አቤል ተፈራ በበኩላቸው ሥልጠናው በኦንላይንና በአካል የተሰጠ መሆኑን ይገልጻሉ። ሥልጠናውን ወስደው ከተመረቁት 741 ሴት ሠልጣኞች ውስጥ 200 በላይ በአካል ተገኝተው የተመረቁ ሲሆን ሌሎቹ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም በኦንላይን እየተከታተሉ እንደነበር አስታውቀዋል።

ሥልጠናው በኦንላይን በዘጠኝ የተለያዩ ኮርሶች የሥራ ተነሳሽነት (ዝግጁነት) ለመፍጠር የሚያስችል ሥልጠና እንደሆነ አስታወሰው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ዳታ ትንታኔ፣ በዌብ ሳይትና በሌሎች የትምህርት አይነቶች ላይ ትኩረት ያደረጉ እንደነበር አስረድተዋል።

አቶ አቤል ‹‹ሥልጠናው በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ሴቶች የተሳተፉበት ለሦስት ወራት በኦንላይንና በአካል የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሥልጠናው የተወሰነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እውቀት ላላቸውና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ተሰጥቷል ነው ያሉት። የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና በኦንላይን ቢሰጥም ክትትልና ድጋፍ አብሮ የሚሰጥ በመሆኑ በአካል ወርክሾፖች ተሰጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ሥልጠናው ሁለት ዓይነት ጠቀሜታ አለው። አንደኛው እውቀቱን ማግኘታቸው ሙያ ላይ ተሰማርተው በሀገር ውስጥና በዓለም ሀገራት መሥራት ስለሚያስችላቸው እንደግለሰብ ለራሳቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሁለተኛው አልፎ ተርፎ እንደሀገር ሲታሰብ ሴቶች ትጉና ታታሪ እንደመሆናቸው ያላቸውን ክህሎትና እውቀት ተጠቅመው የትም ቦታ ሆነው መሥራት ያስችላቸዋል። በዚህም ሀገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላታል። አሁንም እየሠሩ በዶላር የሚከፈላቸው ስላሉ ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል ከግለሰብ አልፎ እንደሀገር ማስፋት ያስፈልጋል።

‹‹ኦንላይን ኮርሶች ማንኛውም ሰው በራሱ የሚወስደው ቢሆንም በስቲም ፓውር መሰጠቱ ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት በኦንላይን የሚሰጠው ሥልጠና በሠልጣኞች የጊዜ ውስጥ የሚመራ እንደመሆናቸው የሚቆጣጠረው አካል የለም። በመሆኑም ሠልጣኞችም ሥልጠናው ሲጀምር እንደነበር ሳይሆን ቀርቶ ትጋታቸው እየቀነሰ የሚመጣበት ሁኔታ ስለሚኖር በስቲም ፓወር ደግሞ በየጊዜው በሚያደርገው ድጋፍና ክትትል የጀመሩት እንዲጨርሱ በማበረታትና በማትጋት የሚፈልጉት ደረጃ ማድረስ ያስችላል›› በማለት ያስረዳሉ። ሠልጣኞች ሥልጠናው ለመሠልጠን በምስራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ ትልቅ በሚባለው ‹‹ቴክባይ ኢትዮጵያ›› በተባለ የቴሌግራም ቻናል ላይ በመግባት ሊያመለክቱ እንደቻሉ ተናግረዋል።

በቀጣይ ሁለተኛ ዙር ሥልጠና ከዘጠኝ ሺህ በላይ ፍላጎት ያላቸው ሴቶች ተመዝግበዋል ያሉት አቶ አቤል፤ ተግተው እንዲሠሩና ራሳቸው ተጠቅመም ሀገራቸውንም እንዲጠቀሙ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል። ‹‹ፕሮጀክቱ ‹‹ትጋት›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ሴቶች ደግሞ በትጋት ስለሚታወቁ በዚህ ፕሮግራም ተሳታፊ ሆነው ትጋታቸውን ማሳየት ይችላሉ›› ሲሉ አስገንዘበዋል።

በዕለቱ ሥልጠናውን ወስደው ከተመረቁት 741 ሴቶች መካካል አንዷ የሆነችው መስከረም ወልደሚካኤል ናት። መስከረም በመጀመሪያ በዲጂታል ዘርፍ ለሴቶች ነጻ የሆነ ትምህርት ለመስጠት እድሉን አግኝታ ተሳታፊ በመሆኗ አዘጋጆቹን አመስግናለች። ሥልጠናው በሦስት ወር ቆይታ ጊዜን በአግባብ መጠቀም ያስቻለና ጥሩ እውቀት የቀሰሙበት መሆኑን ጠቅሳ፤ ‹‹እኔ ጊዜዬን በአግባቡ የተጠቀምኩበትና ብዙ እውቀት ያገኘሁበት ጥሩ ቆይታ ነበር›› ብላለች። ፡

የስቲም ፓውር አባላትም ሥልጠናው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሥልጠናውን የተመለከቱ ጥያቄዎችንም ሆነ ማንኛውንም ነገሮች በተለያየ መልክ ስናቀርብ ያለመሰልቸት ድጋፍና ክትትል እያደረጉልን ቆይተዋል የምትለው መስከረም፤ ሥልጠናው በዚህ ዲጂታል ዘመን እጅግ ጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም አልፈን ሌላውን መጥቀም የምችለበት ነው። ‹‹በሶስት ወራት ቆይታዬ መሠረታዊ ዳታ እና ኢንፎርሜሽ፣ ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ኮርሶችን ወስጃለሁ። ይህም ትምህርቱን መውሰድ ብቻ ሳይሆን ከሰዎች ጋር ያለኝ ትውውቅና የመግባባት እንዲጨምር እድሉን ፈጥሮልኛል›› ብላለች።

ሥልጠናው በሞጁል መልኩ የተዘጋጁት ኮርሶች በቪዲዮ የተዘጋጁ ቢሆንም የተሻለ መሆኑን ነው መስከረም የምትገልጸው። ምክንያቱም በሥራ ቦታ፣ በትራንስፖርትም ሆነ በየትኛውም ቦታ ሥልጠና እንድንከታተል ጊዜያችንን በአግባብ እንድንጠቀም አስችሎናል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

እድሉን ያላገኙ ሴቶች ሥልጠናውን ቢወስዱ ራሳቸውን ማሳደግ ይችላሉ። በተለይም በጊዜያቸው በአግባብ እንዲጠቀሙና የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል ስትል መስከረም ምክረ ሃሳብ ትለግሳለች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2016

 

 

Recommended For You