ከመጋረጃው በስተጀርባ ከፀሐይ ጋር እየፈነጠቁ፣ ከጨለማው ጋር እየተደበቁ፣ በጥበብ የማለዳ ጀንበር ወጥተው በምሽት ጨረቃ አልባ ጀንበር የሚጠልቁ ብዙ ናቸው። ከአትሮኖሱ ፊት አቁመን የተመለከትናቸው ጥቂቶች ቢኖሩም፤ ከላምባ ብርሃን ተሸሽገው እንደ ሻማ እየቀለጡ ብቻ ያለቁ ግን እልፍ ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ከስመው ካለቁ ወዲያ እንጂ በርተው ሳሉ ፈልገን ስላልተመለከትናቸው ነው።
ከመጋረጃው በስተጀርባ ያሉ እጅግ በርካቶች ናቸው። ከቲያትር ቤት መጋረጃ ጀርባ ጥበብን ነፍስ የሚዘሩባት ግን ደግሞ ከዓይናችን እርቀው ሳናውቃቸውም እንዳላወቅናቸው፣ ስምና ሥራዎቻቸውን እንጂ እነርሱን እምብዛም የማናጤናቸው ዛሬም አሉ። መጽሐፉን እየተጋፋን ያነበብንለት ደራሲ ሳናውቀው ከመንገድ ታክሲው ውስጥ ሁሉ እየገፋነው እናልፋለን። ከብዙ የጥበብ ሰዎች አንደበትም እንዲህ ዓይነቶቹን ገጠመኞች ሰምተን ይሆናል። በጥበብ ቤት ተወልደው ለሚያድጉ ይኼ ብርቅ፤ ድንቃቸው አይደለም። ወይ ይላመዱታል፤ አለያም እጣ ፈንታቸው መሆኑን አውቀው ሳያላምጡ ይውጡታል። ይሁንና፣ የአሁኑ ሃሳባችን በዚህ መጨረሻ በሌለው ጠመዝማዛ መንገድ ውስጥ መባዘን አይደለም። የዛሬዋ ፋኖሳችን ግን ከብርጭቆው መጋረጃ ውስጥ ሆና በወርቃማ የእሳት ብርሃን ስትንበለበል መድረኩን ፏ! ታደርገዋለች እንጂ በንፋሱ ኃይል ተሸብራ የምትርገበገብ አይደለችም። ከበርካታ ትያትሮች መጋረጃ ውስጥ ምስሏ ውብ፣ የሥራዎቿ መዓዛ እንደ ሮዝ አበባ ነው። ለቲያትር ጥበብ ነፍስን የዘራች፣ ከመጋረጃው ውስጥ የምትገኝ ፋኖስ እሷ መዓዛ ወርቁ ናት።
የትያትር ቤትን ደጅ እረግጠው፣ ከአዳራሹ ትያትርን ኮምኩመው ቀልብን ከሚሰውሩ የትያትር ትዕይንቶች ጋር አብረው የተሰወሩ ሁሉ ስለ መዓዛ ወርቁ አለማወቅ አይችሉም። ምክንያቱም ልባቸውን ተሰርቀው ያሰረቀውን ሳይጠይቁና ሳያጠያይቁ አይሄዱም። ወደ እዚያ አካባቢ ብቅ ብለው የትያትር ጸሀፊና አዘጋጅ ካሉ ስሟ ናኝቶ ከፍ እያለ እንደ እንፋሎት ሽቅብ ይግተለተላል። እዚህ ብቻም ሳይሆን አልፎም በአውሮፓና በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እንደ ጨረቃ በርታ የታየችባቸው ጊዜያት በርከት ያሉ ናቸው። ሥራን እንደ ሥራ፤ ተፈጥሮን እንደተፈጥሮው የምታስተናግድና በራሷ አምሳል እራሷን ብቻ መስላ የምትኖር እንስት ናት። ወርቅ ሁሌም የትም ቦታ ላይ ወርቅ ነው፤ ወርቀዘቦ መባል ቢያንስ እንጂ አይበዛባትም። ዝነኛዋ ዘምናኒት “ዝነኞቹ” የተሰኘ ትያትርም ጽፋ ለመድረክ አብቅታ ነበር። ከሬዲዮ ድራማ እስከ ትያትር መድረክ ድረስ ማራኪ የትዕይንትና የታሪክ ደሴት ሠርታ ስታስደስተን ኖራለች። ከአበቦች መሀል እንቡጡን እንደምትቀስም ንብ፤ ከቀፎዋ የጥበብ ማር ከጓዳዋ ወለላው ጠፍቶ አያውቅም። ጣፋጩን እየቀሰመች ጣፋጩን ታበላለች። ከዚህም ከዚያም እያነሳሱ ከቀመሱላት ምን ቢጠገብ አይሰለችም። ከጥበብ መቅረዟ ፊት ሲቆሙም ከጽጌረዳም የላቀ ሰንፔር ከመዓዛው ጋር ፈክቶ እንመለከታለን።
ልጅነት የሌለው ሰውና መጀመሪያም የሌለው መጨረሻ የለም። ሁሉም መጀመሪያ ከልጅነት ይቀዳል። የልጅነቷም “ሀሁ” በ1971 ዓ.ም በአስመራ ተጀመረ። ገና አንድ ዓመት እንደሞላት ግን ወላጆቿ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ መጡና ሁሉም የሕይወት ምዕራፎቿ የሚጀምሩት ከዚሁ ሆነ። ዛሬም ይኸው ከዚሁ አለች። ከማህደረ ትዝታዋ ውስጥ ጥበብ የፍቅር ፊቷን አዙራ ትመለከታታለች። እቃቃና አኩኩሉም አብረው ሳይጫወቱ አይቀሩም። ጥበብስ ብትሆን መች እኩያ አላትና ከህጻን ጋር ህጻን ከአዛውንቱም ጋር አዛውንት ናት። መዓዛ ወርቁ ገና በለጋነቱ ሰሞን ልጅነቷን የሚመስሉ ጽሁፎችን ትጽፍ ነበር። የአሁኑን እሷነቷን ለማብሰል ጉልቻውን ጎልታ ውሃውን የጣደችው ያኔውኑ ነበር። ብዕር ጨብጣ ከደብተር ወረቀት ጋር ስታገናኘው ከፊደል ገበታው የላቁ ፊደላትን ትመለከታለች። ከኩራዝ የላቀች ፋኖስ ጭል … ጭል ስትል ትታያለች። ቤተሰቦቿ ለቀለም ትምህርት ያላቸው ቦታ ከፍ ያለ ነበርና እርሷም የምትፈሰው በዚያው በቀደዱላት ቦይ ነበር። ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው በተሸጋገረች ቁጥር የጥበብ መዓዛ ይበልጥ እያወዳት መጣ። የተሻለውን ዕውቀት በቀሰመች ቁጥር ወደ ተሻለ የጥበብ ጋራ ወሰዳት እንጂ በማንም ጫና አልከሰመባትም። እምብዛም ስለራሷ ስትናገር የማትደመጠዋ መዓዛ ከልጅነት ትዝታዎቿ የምታነሳው አንድ ነገር አላት።
ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት አንድ ትልቅ ነገር ታያት። ከምትሞነጫጭርበት ብዕሯ ውስጥ የሚያተኩሰው የደራሲነት ስሜቷ ከመዳፏ እያለፈ ልቧን እየቆሰቆሰ ከመላው አካላቷ ሲዘዋወር ተሰማት። “የኛ ልጅ በርቺ! በርቺ! በማንም እንዳትረቺ” አለቻት ጥበብ። ይኼኔ እሷም ነሸጣት። የወኔው ግለት ያጋላት መዓዛ መጽሐፍ ካልጻፍኩ… ስትል ሃሳብ ቋጥራ ተነሳች። ሄደች….ሄደች ግን ከመሀል ደርሳ ሁሉንም ነገር እረሳች። እየጻፈች ሄዳ ግን ከመሀሉ ስትደርስ ለትውስታውም ጠፋት። መጀመሯን እንጂ አለመጨረሷ ስለምን እንደነበረ ትዝ አይላትም። ሁሌም ከዚያም ከዚም በልጅነት ብዕሯ መጻፍን የማትታክት እንደነበረች ግን አትዘነጋውም። መዓዛ በጥሩ ውጤት ለከፍተኛ ትምህርት አልፋ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስትገባ ህልምና ምርጫዋ አንድና አንድ ነበር። በቀጥታ ወደ ትያትርና ጥበባት ትምህርት ቤት አመራች። በነበራት የዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ከትወናው ጀምሮ ሁሉንም የቲያትር ጥበባት ብትቀማምሳቸውም የድርሰቱ ማዕድ ግን ይበልጥ ጣፈጣት። ከዚያ ሁሉ ጥቅል የእርሷ ክር የተመዘዘችው ከትያትር ድርሰቱ ፈትል ውስጥ መሆኑን አውቃና ወስና ተከተለችው። በ1992 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ ለመጀመሪያው ወግ ማዕረግ በቃች።
ድርሰትና መዓዛ ወርቁ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በሬዲዮ ነበር። ኤፍኤም 97.1 ለፋኖሷ የዕድል በሩን ከፈተላት። አጋጣሚውን በመጠቀምም አንዲት አጠር ያለች ድራማ ጽፋ ራሷን ልታስተዋውቃቸው ቻለች። እንግዲህ ከዚህ በኋላ እየቀጠለችና እያቀጣጠለች የፋኖሷን ክር ከፍ አድርጋ የብርሃኗን ኃይል ጨመረችው። ለሬዲዮና ለቴሌቪዥን የሚሆኑ በርካታ ድራማዎችንም ወደ ማሰናዳቱ ገባች። መዓዛ የሕይወቷ ወርቅ የሚገኘው በመድረክ ትያትሮች ውስጥ እንደሆነ ብታውቅም፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ስትወጣ ግን የወሰነችው አንድ ውሳኔ ነበር። ይኸውም ለአሥር ዓመታት ያህል ከመድረክ ትያትር ሥራዎች እርቆ መኖር ነበር። ከሚወዱት ነገር እርቆ በመኖር ውሳኔ ውስጥ አንድ አስገዳጅ ምክንያት እንደሚኖር መገመት ቀላል ነው። የመድረክ ትያትር ከሌሎቹ አንጻር ከበድ የሚል በመሆኑ በተማረችው ትምህርት ብቻ ተነስታ ለመግባት አልፈለገችም። ስለዚህ ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ተጨማሪ ልምድና ዕውቀት ማካበት ነበረባት። በእነዚህ ጊዜያትም የመድረክ ትያትርን ንክች ሳታደርገው በውሳኔዋ ጸናች።
ዓመታቱ አልቀውና የምትፈልገውን ብስለት ማግኘቷን እርግጠኛ ስትሆን መዓዛና የመድረክ ትያትር ተገናኙ። ከዚያ ወዲህ በርከት ያሉ የመድረክ ትያትሮችን ጽፋ አዘጋጀች። ከሁሉም ሥራዎቿ ግን “ዝነኞቹ” እና “ከሰላምታ ጋር” የተሰኙት ሁለቱ ትያትሮች በልዩነት መታወቂያዎቿ ሆኑ። ለአሥር ዓመታት ያህል ብዙ ማገዶ የፈጀችበትና ስታበስለው የነበረው የትያትር ክሂሎት በስተመጨረሻም ያከበረችውን ያህል አከበራት። የመጀመሪያውንም ጣፋጭ ማዕድ ለትያትር አፍቃሪው በሙሉ አቀረበች፤ “ዝነኞቹ” በአዲስ አበባ ትያትርና ባህል አዳራሽ ቀረበ። በእርግጥ ከጥፍጥናውም ጣትን እንደ ሚያስቆረጥም ጣፋጭ ምግብ ነበር። በከተማዋ ውስጥ ባሉ በአብዛኛዎቹ ትያትር ቤቶች ብትዞርም መዓዛ አንድ ያልተመቻት ጉዳይ ነበር። በየትያትር ቤቱ ያሉ ውጣ ውረድችና እጅ በአንገት የሆኑ ሕጎች በምታስበው ልክ እንዳትሠራ የፊት ጋሬጣ ሆኑባት። ከዚህ ትርምስ በመውጣት በግሏ ለመሥራት የምትችልባቸውን መንገዶች ማሰስ ውስጥ ገባች።
በዚህ መሀልም አንዲት ዕድል በሯን ከፍታ ሰተት ስትል ገባች። ዕድሏም የ “ሰንዳንስ ኢንስቲትዩት” መልዕክተኛ ነበርች። “ሰንዳንስ” በሀገረ አሜሪካ የሚገኝ ዓለም አቀፍ የፊልምና የመድረክ ሥራዎች አዘጋጅ ተቋም ነው። ከወደ አሜሪካ ለምስራቅ አፍሪካ የመድረክ ጠበብት የመጣ ትልቅ ዕድል ነበር። አይበገሬዋም ስትሰማ እንዲያመልጣት አልፈለገችም። ወዲያው ውስጣዊ ወኔዋ ልቧን ፈንቅሎ ወጣ። አንድ የእንግሊዘኛ ትያትር ለመጻፍ ግድ እንደሚላት አወቀች። ትንፋሽዋንም ሳብ በማድረግ ኃይሏን አሰባስባ ገባችበት። ለውጭ ሀገር ተመልካቾች የሚቀርበውን ትያትሯንም ጽፋ አሰናዳችው። ብዙዎች ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ የተሠራ የሚመስለን “ከሰላምታ ጋር” የተሰኘው ትያትሯን የጻፈችው እንዲህ ባለ መልኩ አስቀድማ በእንግሊዝኛ ነበር። ኋላ ነው ወደ አማርኛ ተርጉማው በአዲስ አበባ መድረኮች ላይ የታየው። ገና ያኔ ስትጽፈው ትያትሩም መልከ ቀናና ዕድለ እረጢብ ነበር። ሁለት ጊዜ በኬንያ፣ ሌላ ጊዜም በዩጋንዳ፤ እንዲሁም፣ ጎራ እያለ በሩዋንዳና በቡሩንዲ ለእይታ በቃ። ነገር ግን በዚህ አላበቃም።
እንደ ቦሌው አውሮፕላን ክንፉን ዘርግቶ ወደ ላይ እያለ ከምስራቅ አፍሪካ ወጥቶ ሲውዲንና ጀርመንን ሳይቀር አዳረሰ። ከሰርቢያ ደርሶም ወደ ራሳቸው ቋንቋም ተተረጎመ። አፈትልኮም አሜሪካን ኒውዮርክ ገባ። የዕድል በሩ ግን እየሰፋ እንጂ እየጠበብ የሚሄድ አልነበረምና ከመታየት አልፎ ወደ ማስተማሪያነት ተሸጋገር። ሀገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የትያትር ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተምረው እያስተማሩበት ብቻ ሳይሆን ምርምርም እያካሄዱበት ይገኛሉ። እንግዲህ ሁሉም ዞሮ ዞሮ መግቢያው ቤቱ፤ ሀገሩ ነው የእናት አባት እርስቱ። ከጥቁሩም ከፈረንጁም፤ ከአውሮፓና አፍሪካ ሲዞር ኖሮ እዚያው ከገደመ (ገዳም እንደ ገባ ሁሉ) እርሱን ሳይሆን እሷን መታዘባችን አይቀርም። በሀገሯ ጉዳይ ለሀሜቱም የማትሆን ናትና በቶሎ ወደ አማርኛ ቀይራ “ከሰላምታ ጋር” እንዲሆን አደረገችው። በጃዝ አምባ ላይጠፋ በርቶ በሀገሯም አኮራት። በአንድ ወቅት ግን አንድ ችግር ተከሰተ። ከዚያው የጃዝ አምባ ሳይወጣ በጎን የጣይቱ ሆቴል በእሳት ነበልባል ተቀጣጠለ። እሳቱም ተዛምቶ የትያትሩ ሙሉ መረጃ ከነመሥሪያ ቁሳቁሱ ጋየ። ነገር ግን እሳት ቁሱን እንጂ መች ከሰው አዕምሮ ለማጥፋት ይችልና… በድጋሚ ተሠርቶ በሌላ ጊዜም ታየ። የመዓዛን የጥበብ መቀነት በውስጥና በውጭ ያጠበቀው የትያትር መቀነቷ እንዲህ ያለውን እላይና ታችም የያዘ ነበር።
ከባህሪዋ ሁሉ ምኗ ግሩም ነው ብትሉ ማረም የሕይወቷ ትልቁ ላምባ ይመስላል። ስህተትን በይሉኝታ ፈጽሞ አታልፍም። ቅን አሳቢነቷ ጌጧ ነው። ከተፈጥሮ በላይ የሆነን ተፈጥሮ አትወድም። ከራሷ ተፈጥሮ በላይ የሆነ ውበት አለመኖሩ ይገባታልና በአርቴፊሻል መሽቀርቀር ፈጽሞ ስሜት አይሰጣትም። ሀገርና ባህሏን ስታከብር የእውነትም ገብቷት፤ ከልቧ ስለመሆኑ እያንዳንዱ የሕይወት እርምጃዎቿ ገልጠው የሚያሳዩም የሚናገሩም ናቸው። ሴትነቷ የውበቷ ቀለምና የችሎታዋ የኃይል ድፍድፍ እንጂ የጉድለት በርሜሏ አይደለም። በራስ መተማመኗና በራሷ ላይ ያላት እምነት የማይገፉትና የማይጋፉት ነው። ሰውን “ጀግና!” ሲሉት ልቡን ያደለድለዋል። “ጀግኒት!” ያሏትም ሴት እንዲሁ ደስ ይላታል። መዓዛ ግን “ጀግኒት” ያሏት እንደሆነ እንኳንስ መደሰት ይባስ ንድድ ያደርጋታል። ሙገሳን አትጠላም፤ ሌላውን ለማድነቅም አትዘገይም። ግን ደግሞ ለራስ ቆርሰው ለቋንቋ ማሳነሱን አትወደወም። “ጀግና” እንጂ ጀግኒት የሚል የቋንቋ መደብ የለንምና ስለምንስ ብለን ለቃላቱም እንሻኮት የሚል እሳቤን ትጋራለች። በሴትነቷ ብቻ ከወንዱ በተለየ መንገድ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዲደረግላት አትሻም። ምክንያቱም ተፈጥሮ ያጎደለችባት ምንም ነገር እንደሌለ ስለምታስብ ነው። መዓዛ ምን ብትሠራ እንኳን ታይታን አትወድም። ብልጭልጭ ሁካታም ሆነ ግርግር አትወድም። ነጠል ብሎ ማድመጥን ትመርጣለች። ለሽልማትም ሆነ ለምስጋና ብላ የምትሠራው ምንም የለም። ቢጠይቋትም “ከሥራዬ በላይ ምንስ ሽልማት ሊኖረኝ ይችልና?” ትላለች። ለድርሰት አንዴ ካቀረቀረች ወዲያ የወሰዳት የምናብ ባቡር መልሶ ካላመጣት በስተቀር መድፍ እንኳን ቢተኮስ ቀና አትልም።
ስለ መዓዛ ወርቁ ጥቂት ለማለት ስነሳ በእጅ ያለወርቅ እንደ መዳብ… ሆኖብን ብዙ እንዳልተመለከትናት ተሰማኝ። ከእኛ ይልቅ ሌሎቹ፣ ከሀገሯም ይልቅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ይበልጥ በርታና ደምቃ የታየች ይመስለኛል። ከምናውቃት በላይ ያውቋታል። ከተናገርንላት በላይ ተናግረውላታል። ከመጋረጃው ውስጥ ያለችውን ፋኖስ ተመልክቶ ከፍ ለማድረግ የመጀመሪያዎቹ መሆን ነበረብን፤ ግን እነርሱ ቀድመው አክብረዋታል። በሀገሯ አልተከበረችም ለማለት ሳይሆን ከድሮ ዛሬም ያለው ባለውለታን የመዘንጋት አባዜ ይዞን የሚገባትን ያህል ልንሰጣት አልቻልንም። ባላት የትያትር ጥበብና ዕውቀት በበርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይም ተሳትፋለች። ለአብነትም በ2004 ዓ.ም በሲውዲን (ስቶኮልም) በተካሄደው ዓለም አቀፉ የሴት የመድረክ ጸሀፊያን ጉባዔ ተመርጣም ለመሳተፍ ችላ ነበር። በሄደች፣ በደረሰችበት ሁሉ የሀገሯን ባህልና እሴቶችን ከማንጸባረቅና ከማስተዋወቅ አፈግፍጋ አታውቅም። ምንም እንኳን አብዛኛው የህይወት ክፍሏ የተጋመደው ከትያትሩ ላይ ቢሆንም ከሌሎች ጥበባትም የራቀች አይደለችም። በፊልሙ ዘርፍም የፕሮዳክሽን ተቋም ከፍታ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥ የማማክር አገልግሎት ትሰጣለች። የኪነ ጥበብ ዘርፉን በተመለከተ ሂሳዊና ልዩ ልዩ አምዶችን እያዘጋጀችም በተለያዩ ድረ-ገጾች ታካፍላለች። የጥበብ መዓዛ ከሚያውድበት ከየትኛውም ቦታ ጠረኑ ይጠራታል። በአሁኑ ሰዓት ግራና ቀኙን ሳይመለከቱ እልህ በፈነቀለው የመንፈስ ወኔ ለሀገራቸው የኪነ ጥበብ እድገት ከልባቸው እየታተሩ ካሉ ጥቂቶች መካከል አንዷ ፋኖሷ መዓዛ ወርቁ ናት።
ጠበብቷ የትያትር ጸሀፊ በአንድ ወቅት እንዲህ አለች፤ “ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው” ስትል ትያትር ጻፈች። ለመጻፍ ስትነሳ ግን ብዙ ለማሰብም ሆነ ሥራውን ለማብሰል የነበሯት ጥቂት ቀናት ብቻ ነበሩ። የሀገራችን የዘመናዊ ትያትር የወርቅ እዮቤልዩ ከመቶኛ ዓመት የልደት በዓሉ ጋር በደረሰበት ሰሞን ላይ ነበር። ለዚሁ የሚሆን ትያትር በአጭር ጊዜ ውስጥ ጽፎ የሚያዘጋጅ ቢጠፋ ጊዜ፤ መዓዛ እራስዋ ለመጻፍ ወስና ተያያዘችው። ርዕሱ እንደወረደ ተቀብለን መስሎን እንዳንታለል። በእርግጥም ሼክስፒር የሁሉም ዓለማት የቲያትር ቁንጮ ስለመሆኑ ባትክድም፤ የሚበልጡት ግን ከእኛው ዘንድ አሉ በማለት የማይወላውል አቋም አላት። ልዩነቱ እንግሊዛውያኑ የእርሱን ስም በመጠቀም ብቻ ዛሬም ድረስ ሀገራቸውን ከፍ እያደረጉ ያውለበልቡበታል፤ የኛዎቹ ግን በዚያው ደህና ሁኑ ተብለው መረሳታቸው ነው። መዓዛ ስማቸውን በታላቅነትና በአድናቆት የምታነሳቸው የኛ እድለ-ቢስ ሼክስፒሮች ከበደ ሚካኤል፣ መንግሥቱ ለማ እና ጸጋዬ ገ/መድህን ናቸው። “ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው” ትያትርን ስትጽፍም ግብአት አድርጋ የተጠቀመችው ሼክስፒርን ሳይሆን እነርሱኑ ነው። እውነትም ይበልጡ እንደሆን እንጂ የሚያንሱ እንኳን አይደሉም። ችግሩ ግን ታማኝነታችን በዛና አትግለጡት ካልተባልን በስተቀር ከፍተን ከመጋረጃው በስተጀርባ አንመለከትም። ፋኖሷ ግን፤ ሁሌም ሳታቋርጥ ብርሃኗን ስለመስጠት እንጂ ስለጨለማው አያስጨንቃትም። ቀሪው ግን የእኛው ሥራ ነው።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም