በህይወት ያጣናቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ዘመድ ወዳድና ሰብሳቢ እንደነበሩ እንዲሁም ማህበረሰባዊና ቤተሰባዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ እንደነበሩ በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የቅርብ ዘመዶቻቸው ይገልፃሉ፡፡ ካነጋገርናቸው መካከልም የአጎታቸው ልጅ ወይዘሪት ቅድስት ምስጋናው ‹‹ዶክተር አምባቸው ለዘመድ ሰፍሳፋ ናቸው፡፡ አባታቸው በልጅነታቸው የሞቱባቸው የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸውም የታናሽ እህትና ወንድማቸው በአጠቃላይ የቤተሰብ ኃላፊነት በእርሳቸው ላይ በመውደቁ እንደአባት ሆነው አሳድገዋል›› በማለት ለቤተሰባቸው ያላቸውን ፍቅርና እንክብካቤ አጫውታናለች፡፡
ከወራት በፊት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሲሾሙ ኃላፊነቱን በደስታ እንደተቀበሉትና ክልላቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል ‹ጥሪ ቀርቦልኛል› ብለው ልጆቻቸውንና ትዳራቸውን በመኖሪያቸው አዲስ አበባ ከተማ ትተው ወደ ክልሉ እንደሄዱ ታስታውሳለች፡፡ ‹‹ሀገራቸውን ለማገልገል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሙሉ ልብ ተቀብለው እየሰሩ ባሉበት በራሳቸው በሆነው እና በሚያምኑት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ምን ይባላል›› ስትል በኀዘን ስሜት ነግራናለች፡፡
ዶክተር አምባቸው ከአርሶአደር ቤተሰብ የተገኙ እና ከልጅነታቸው ጀምሮ አስተዋይ ፣ እንደነበሩ፣ በትምህርታቸውም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ፣ለቤተሰቦቻቸው ጥልቅ ፍቅር ያላቸውና ስብዕናቸውም ለዘመድ ሁሉ ምሳሌ የሚሆን ከፍተኛ የቤተሰብ ፍቅር ያላቸው፣ የመጡበትን ማህበረሰቡንና ያደጉበትን አካባቢ፣ አብሮ አደጎቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ሁሉ እያነሱ መጫወት የሚወዱና የቤተሰቡ ሰብሳቢና መካሪ መሆናቸውን የቅርብ ዘመዳቸው አቶ ጌታቸው ሲሣይ ይናገራሉ፡፡
አቶ ጌታቸው እንዳሉት ዶክተር አምባቸው እውነትን ይዘው የሚቆሙና ለቆሙለት ዓላማም ታምኝ ነበሩ፡፡ ዶክተር አምባቸው በ1982 ዓ.ም የ11ኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት የነበረውን ሥርዓት በመቃወም የአባታቸውን መሳሪያ አንግበው ከቤታቸው እንደወጡና ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስም ለታገሉለትና ለቆሙለት ዓላማ ውስጥ የቆዩ ታማኝ መሪ ናቸው፡፡ በተለይም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ሲሾሙ ‹እኔ ከዚህ በኋላ የህዝብ እንጂ የቤተሰቤ ብቻ አይደለሁም› ብለው ቁርጠኛ አቋማቸው ዛሬ ምስክር ሆኗቸዋል ይላል፡፡
ዶክተር አምባቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ቆራጥና የአቋም ሰው እንደሆኑ፣ እውነትን ይዘው የሚናገሩና ቅን ልብ ያላቸው መሆናቸው ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ሥራቸው ምስክር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው ዶክተር አምባቸው አንድ ወንድና ሶስት ሴት ልጆቻቸውን እንዲሁም አቅመ ደካማ እናታቸውን ትተው በማለፋቸው በቤተሰቡ ውስጥ ትልቅ ኀዘን እንደተፈጠረ ያስረዳሉ፡፡
‹‹እውነትን ይዘው ነው የተገደሉት እንጂ ሚሊዮን ወይም ቢሊዮን ብር ይዘው አልተገደሉም፡፡ አይሰርቁም፣ አይዋሹም አሳፋሪ ታሪክም አልሰሩም በዚህ እንደቤተሰብ እንኮራባቸዋለን›› በማለት በጥሩ ምግባራቸው እንደሚጽናኑ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የዶክተር አምባቸው የአክስት ልጅ አቶ ዘውዱ ቦጋለ በበኩላቸው ዶክተር አምባቸው ለሀገራቸው ፣ለህዝባቸው ፣ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር ሰው ሊገላቸው ቀርቶ በክፉ ያያቸዋል ብለው አልጠረጠሩም። ለህዝብ ለወገን ብለው ግንባራቸውን ለጥይት የሰጡት የደርግ ሥርዓት ተቃውመው ከቤታቸው ሲወጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ህይወታቸው ያልፋል ብለው ግምታቸው አለመሆኑን በቁጭት ይገልፃሉ፡፡ ሞታቸው በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንዳለፈም ያስባሉ፡፡ጥቃቱ በወገናቸው መፈጸሙ እጅግ እንዳሳዘናቸውና ኀዘናቸውም መሪር እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
ከዶክተር አምባቸው ጋር በልጅነታቸው አብረው እንደተማሩና በ1982 ዓ.ም የነበረውን አስከፊውን የደርግ ስርዓት ለመጣል የተደረገውን ትግል አብረው እንደተቀላቀሉ የሚናገሩት ሻምበል ጀምበር አስማማው ናቸው፡፡
እስከ አሁን ድረስ በድንጋጤ ውስጥ እንዳሉና አዕምሯቸውም ህልፈታቸውን መቀበል እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ዶክተር አምባቸው ጊዜያቸውን ለትምህርት እንደሰጡና በጣም ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋር በሳቅ በጨዋታ በፍቅር የሚያሳልፉ ሰው እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡ እንኳን በጥይት ሊገደሉ ይቅርና ኃይለ ቃል እንኳን ሊናገሯቸው የሚገባ ሰው አይደሉም የሚሉት ሻምበል ጀምበር በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ኢያሱ መሰለ