የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም አመሻሽ ለኢትዮጵያ መልካም ዜና አላበሰረም፡፡ ከባህር ዳር ከተማ የዶክተር አምባቸውንና የአቶ እዘዝ ዋሴን የግፍ አሟሟት ሲያሰማ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የጀነራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን መስዋዕት አርድቷል፡፡ ውሎ አድሮም የቅዳሜው ምሽት ጦስ የአቶ ምግባሩን ሞት አርድቷል፡፡ የጀነራሎች አስከሬን አሸኛኘት ላይ አዲስ አበባ ከተማ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ድርጊቱ አሳዛኝ፣ አሳፋሪና በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው የሚገልጹት።
አስተያየት ከሰጡን መካከል አቶ ሰለሞን ጽጌ ሜጫ እንደሚያመለክቱት፤ ድርጊቱ በጣም አስነዋሪና የወታደራዊ ስነምግባርን ከሚያውቅ ሰው የማይጠበቅ ብለውታል፡፡ የሞቱት ጀግኖች ሰላም እንዲሰፍን፣ አገሪቱ እንድትለማ ሲታትሩ የነበሩና ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም መስፈን መኩሪያ መሆን የሚችሉ እንደነበሩም ይጠቁማሉ፡፡ በእነርሱ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በጣም አሳፋሪ ነው ሲሉም ድርጊቱን ይኮንናሉ፡፡
ወታደር ከፖለቲካ አሰራር የተገለለ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ለአገር ሰላም መስፈንና ለህዝብ ደህንነት ዘብ የሚቆም፣ ለሚሰራው አጠቃላይ ሥራም ተጠያቂነት እንዳለበትም ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም የሚፈጽማቸው ተግባሮችን ሁሉ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መፈጸም ይጠበቅበታል ባይ ናቸው። ወታደራዊ ስነ ምግባር፣ ደንብና መመሪያም አለው፡፡ በተማረውና በሰለጠነው መሰረት አክብሮ መስራት ይገባዋል ይላሉ፡፡ ከዚህ ባፈነገጠና ከወታደራዊ ስነምግባርና ደንብ ውጪ መፈጸሙ አስነዋሪ ድርጊት የሆነ ከአንድ ወታደር የማይጠበቅ ተግባር ነው ሲሉም ያመለክታሉ፡፡
ሰፊ የምርመራ ሥራ በመስራት የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ ሰዎችን ለይቶ ተገቢና አስተማሪ የህግ እርምጃ መውሰድ አለበት የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ የአገር ሰላም ማስፈንና የህዝብን ደህንነት የማስጠበቅ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ በመሆኑ ህዝቡ በየአካባቢው ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ጀግኖች ናቸው። ጀግና ደግሞ አይሞትም፡፡ በርካታ ጀግኖች የተኩ በመሆናቸው አልሞቱም፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ ጀነራሎቹ ባካበቱት ወታደራዊ ሳይንስ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪክ የሚዘነጋው አይደለም፡፡ ለአገርና ለአህጉር ሰላም መስፈንም ያበረከቱት አስተዋጽኦ የሚደነቅና የሚከበር ነው። ለአገራቸው መስዋዕት ሆነዋል፡፡ መቼም የማይዘነጋ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ ግን ሌላ ችግር ወይንም ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በተቋሙ ውስጥ ያለው አሰራር በደንብ መፈተሽ ይኖርበታል ሲሉም መክረዋል፡፡
ወይዘሮ ስንዳይ አሰፋ፤ ተግባሩ በጣም አሳዛኝ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አመራሮቹ በጣም ታታሪ የነበሩ፣ ጥሩ ሰዎችና አገርን ለመገንባት ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩ መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ለአገርና ለወገን የሚያስቡ እንደነበሩ በመግለጽም፤ ድርጊቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ለአገር የሚጠቅሙ ሰዎች ላይ እንዲህ አይነት ተግባር መፈጸም ጥሩ አይደለም፡፡ አገሪቱን ወዳልተገባ መንገድ የሚመራ ተግባር ነው›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡ ድርጊቱ በምንም አይነት ሁኔታ ተቀባይነት የለውም፡፡
የተሰዉትን መመለስ አይቻልም፡፡አሁን ድርጊቱ ተፈጽሟል፡፡ ግን በትዕግስት ማሳለፍ ያስፈልጋል፡፡ በግልፍተኝነት ተነሳስቶ አገር ማጥፋት አያስፈልግም። በሆደ ሰፊነት ነገሮችን ማሳለፍ ይገባል፡፡ ወደፊት ለመጓዝ መነሳሳት መፈጠር አለበት። አገርን መገንባት ያስፈልጋል። የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ ወጣቱ መነሳሳት ይገባዋል ሲሉም ያመለክታሉ፡፡ የመከላከያ ሰራዊት የተሰዉ ጀነራሎች ሲተገብሩት የነበረውን ፈለግ መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ሰላም የማስከበር ሥራ መቀጠል ይኖርበታል፣ ለአገር ሰላምና ዕድገት መልፋትም መድከምም ይኖርባቸዋል። ህዝቡም ልማቱን ማስቀጠል አለበት፡፡ እንጂ ወደ ጥፋት መንገድ መመራት የለበትም ሲሉም ወይዘሮ ስንዳይ መክረዋል፡፡
አቶ ገብረህይወት ወልደአብእዝጊ፤ የተፈጸመው ድርጊት አገርን የሚለያይ፣ በህዝብ ላይም ከፍተኛ ችግር የሚደቅን መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆን ብለው ያቀነባበሩት የጸረ ሰላም ሃይሎች ድርጊት በመሆኑ ተገቢነት የሌለው ነው ሲሉም ድርጊቱን ይኮንናሉ። እነዚህ ሰዎች የሄዱበት መንገድ በምንም አይነት ሁኔታ ሊሳካ የሚችል አይደለም ባይ ናቸው፡፡ ሰዎቹ ገድለዋል እንደገናም ተገድለዋል፡፡ ይህ ምንም አይነት በጎ ውጤት የለውም የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ የብሄር፣ ብሄረሰቦችን አንድነት ለመናድ፣ እርስ በእርስ ለማጣላት፣ የአገሪቱን በጎ ገጽታ ለማጠልሸት፣ በዓለም ላይ የሚታወቀውን የህዝቡን ሰላማዊ መስተጋብር ለማጥፋት ካልሆነ በስተቀር በእንዲህ አይነት ሁኔታ ስልጣን መያዝ እንደማይቻልም ይናገራሉ።
‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተባብረን ጸረ ሳላም ሃይሎችን እናጠፋለን፣ ሰላም እንዲሰፍን ሌት ተቀን እንሰራለን የሚሉት አቶ ገብረህይወት፤ እነርሱ ቢሞቱም የሚተኳቸው በርካታ ጀግኖች ማፍራታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹እነርሱ ሃላፊነታቸውን ይወጣሉ፣ አገራችንም አትደፈርም›› ይላሉ፡፡ ባለፉት ጊዜያት ለኢትዮጵያ ሲሉ በርካታ ጀግኖች መሰዋታቸውን በመጠቆምም፤ ጀግና እየተፈጠረ ኢትዮጵያ ቀጥላለች፡፡ ህዝቡ አንድነቱን አስከብሮ የአገሩን ሰላም ማስጠበቁንም ይቀጥላል ብለዋል፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ዘላለም ግዛው