በጎ ፍቃደኝነት ሰዎች ትርፍ ወይም ጥቅም ሳይፈልጉ በራሳቸው ተነሳሽነት ሌሎችን ለማገዝ የሚያከናውኑት ተግባር ነው:: ይህን በጎ ተግባር ሰዎች በራሳቸው ፍቃድ ሲያከናውኑ ታዲያ ዘርን፣ ፆታን፣ የቆዳ ቀለምን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋንና ፖለቲካን መሠረት አድርገው አይደለም::
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው የበዛ በጎ ፍቃደኞች እንደየፍላጎታቸው በየጊዜው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ይሳተፋሉ:: በኢትዮጵያም ቀደም ሲል ስለ በጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አነስተኛና በመንግሥት በኩልም የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በዚህ አገልግሎት የሚሳተፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል::
በዚህ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ወጣቶች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ:: እስካሁንም በርካታ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል:: በዚህም በርካታ ዜጎች በልዩ ልዩ መልኩ ከበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል::
በዚህ የክረምት ወቅትም በርካታ ወጣቶች በልዩ ልዩ መስኮች በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጥ በስፋት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል:: አምናና ካችአምና በነበረው መረጃ መሠረትም በአረንጓዴ ዐሻራ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሰላም፣ መንገድ ደህንነት፣ የጤና አጠባበቅ ሥራዎች፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ግንዛቤ በመፍጠርና በሌሎችም የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይ ተሳትፈዋል::
የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ የአረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤት እድሳት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልና ግንዛቤ መፍጠርም ወጣቶቹ ከተሳተፉባቸው የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ውስጥ በተጨማሪ የሚጠቀሱ ናቸው::
ከዚህ ቀደም ወጣቶች ከተሳተፉባቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ውስጡ አንዱና ዋነኛው የሰላም ጉዳይ እንደሆነ ይታወሳል:: ከሶስትና አራት ዓመታት በፊት በተለይም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያትና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ ተከስቷል::
በጦርነቱ ወቅትና ጦርነቱ በስምምነት እስከተቋጨበት ጊዜ ድረስ የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል:: ጦርነቱ በስምምነት ከተቋጨ በኋላ በመንግሥትና በህወሓት በኩል የገፅ ለገፅ ግንኙነት ተደርጓል:: በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምት መሠረት መንግሥትና ህወሓት የስምምነቱን አፈፃፀሙን ገቢራዊ ሲያደርጉ ቆይተዋል::
ከዚሁ ጎን ለጎን ታዲያ ሁሌም ቢሆን የሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ሲደፈርስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የግጭቶች ሰለባ የሚሆነው ወጣቱ ነውና ሰላምን በማስፈን ሂደት የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም:: ለዛም ነው ባለፉት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ ወጣቶች በሰላም ዙሪያ ውይይት እንዲያደርጉና ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትና በሌሎችም እነርሱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሲሳተፉ የቆዩት::
በዋናነት ደግሞ የወጣቶችን እርስ በርስ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና አጠቃላይ የወጣቶች ተሳትፎ የጎላ ሚና እንዲኖረው በሰላም ዙሪያ ያተኮሩ ግንኙነቶችም ተካሂደዋል:: አሁንም ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው የሀገሪቱ አጀንዳ ነው:: ምንም እንኳን አቅማቸው እየተሸመደመደ ቢመጣም በኦሮሚያና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች አሁንም የአካባቢያቸውን ፀጥታና ሰላም እየነሱ ነው:: አልፎ አልፎም ቢሆን በሌሎች አካባቢዎች ላይ ግጭቶችና አለመስማማቶች ሲከሰቱ ይሰማል::
እንዲያም ሆኖ ግን መንግሥት ባደረጋቸው የሰላም ውይይቶችና በወሰዳቸው የማረጋጋት እርምጃዎች ግጭቶች በሚስተዋልባቸው በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎች አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል:: ሕዝቡም በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ችሏል:: ገበሬው ወደ እርሻው ተመልሷ:: ነጋዴውም ንግዱን አጧጡፏል:: ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል::
የሚፈለገው አስተማማኝ ሰላም በኢትዮጵያ እንዲረጋገጥ ከተፈለገ ግን በይበልጥ ወጣቱ ላይ አተኩሮ መሥራት ያስፈልጋል:: በተለይ አሁን አብዛኛው ወጣት የትምህርት ጊዜውን አጠናቆ ወደየቤቱ የሚመለስበት ጊዜ እንደመሆኑ ይህን ጊዜ በደምብ መጠቀም ይገባል:: አብዛኛው ወጣት የትርፍ ጊዜውን ማህበራዊ ሚዲያዎችን እየተጠቀመ እንደሚያሳልፍ ይገመታል::
የማህበራዊ ሚዲያዎችን ሲጠቀም ደግሞ አንዳንዴ ትክለኛ ባልሆኑ መረጃዎችና ትርክቶች ጭንቅላቱ ተሞልቶ ለግጭት ሊነሳሳ ይችላል:: ነገሮችን በሰከነና በበሰለ መንገድ በማት የማህበራዊ ሚዲያዎችን በበጎ መልኩ የሚጠቀም ከሆነ ደግሞ በተቃራኒው የሰላም ዘብ ይሆናል::
ስለዚህ ወጣቱ በዚህ ክረምት ወቅት ባለው ትርፍ ጊዜ ማህበራዊ ሚዲያውን በበጎ በመጠቀም ለሰላም ዘብ መጠበቅ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላል:: ይህ በቀጥታ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ውስጥ ሳይሳተፍ በራሱ አስተዋፅኦ የሚያደርገው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ ሊሆን ይችላል::
ወጣቱ ትኩስ ሃይልና ብዙ ነገሮችን መፍጠር የሚችል እንደመሆኑ ማህበራዊ ሚዲያውን በመጥፎ መንገድ በመጠቀም ምድርን እንደሚያናውጥ ሁሉ ይህን መንገድ ትቶ ስለሰላም በመዘመርና በመስበክ ለሰላምና ፀጥታ መጠበቅ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረግ ይችላል:: ይህ ሲባል ግን ወጣቱ ያሉትን ጥያቄዎች አይጠይቅ፤ መብቱንም አያስከብር ማለት አይደለም:: ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ ማንሳት ይችላል::
ስለዚህ ወጣቱ ለሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ እንዱና በራሱ ተሳሽነት የሚያደርገው ነገር ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ስለሰላም መስበክ ሆኖ ሳለ የክረምት ወቅቱን ተከትሎ መንግሥት ወጣቶችን በማሰባሰብ በሚያካሂደው የወጣቶች ክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትም በመሳተፍ ለሰላም መረጋገጥ የድርሻውን መወጣት ይችላል::
በዚህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ወጣቶች በሰላም ጉዳይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል:: የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ጉዦዎችም እንደሚደረጉ ይታመናል:: ስለዚህ በዚህ ክረምትም ወጣቶች በእንዲህ አይነቱ ውይይትና የሰላም ጉዞ ላይ በስፋትና በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል::
ይህ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቱ ቁጭ ብሎ ስለሰላም የሚነጋገርበት መድረክ ነው:: ሃሳቡን የሚለዋወጥበትና የሃሳብ አሸናፊነት ምን ያህል ከጠመንጃ ሃይል የበለጠ ገዢ መሆኑን የሚያይበት ነው:: የሰላም ዋጋዋ ከፍ ያለና ከሰላም የሚገገኘው በረከትም ምን ያህል ለእርሱ ጠቃሚ መሆኑን የሚረዳበት አጋጣሚ ነው::
በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ተነጋግሮና ተወያይቶ መፍትሄ ላይ መድረስ እንደሚቻል የሚገነዘብበትም ጭምር ነው:: ከዚህ አንፃር ወጣቱ መንግሥት በሚያመቻቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በተለይ በሰላም ጉዳይ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ለሰላም መጠበቁ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይጠበቅበታል::
በተለይ ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ ወጣቱን በስፋት የሚያሳትፍና ከአጀንዳ ማሰባሰብ ወደ ምክክር ሂደት እየተሸጋገረ በመሆኑ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወጣቱ ስለሀገሩ ሰላም መምከር ይኖርበታል:: በርግጥ ወጣቱ አሁንም ድረስ ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታመናል::
ስለዚህ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስለሰላም ከመስበኩ በዘለለ ወጣቱ በሀገራዊ ምክክሩ ያሉበትን ጥያቄዎች ማንሳት ይኖርበታል:: መንግሥትም ለወጣቱ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርበታል::
የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ወጣቱ እንደመሆኑ መንግሥትም ለወጣቱ ትኩረት ሰጥቶና በክረምቱ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሰላም ውይይት መድረክ በማመቻቸት ወጣቶች ሃሳባቸውን እንዲተነፍሱና ለሰላም መጠበቅ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል::
የወጣቶች የእርስ በእርስ ግንኙነቶችም ለሰላም መምጣት የራሳቸው አስተዋፅኦ ስላላቸው ወጣቶች ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተጓጉዘው እርስበርስ እንዲወያዩ፣ አንዳቸው የሌላቸውን ባህል እንዲያውቁና እንዲማማሩ፣ ስለ ሰላም እንዲሰብኩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል::
ወጣት ላይ መሥራት የነገ ትውልድ ላይ መሥራት ነው:: ወጣት ላይ መሥራት የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት ነው:: ወጣት ላይ መሥራት ሀገርን በሁለንተናዊ መልኩ መቀየር ነው:: እናም ወጣት ሆይ በክረምት ስለ ሰላም ዘምር:: ስለሰላም ዘክር:: ስለሰላም አውራ::
ያኔ ወደቀጣዩና ትክክለኛው የሕይወት መስነመርህ ትገባለህ:: መንግሥትም ወጣት ላይ ሥራ:: ለወጣቶች መወያያና መነጋገሪያ የሚሆኑ መድረኮችንና ሁኔታዎችን አመቻች:: ያኔ የሀገርን ሃላፊነት ተሸክመው ለቀጣዩ ትውልድ አደራ የሚያስተላልፉ ወጣቶችን ማፍራት ትችላለህ!!
ሙዘይን ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም