መቐለ፡- የዴሞክራሲ ስርዓት እየተሸረሸረ በመምጣቱ ሀገሪቱ የጸረ ሰላምና የፀረ ልማት ኃይሎች መናኸሪያ በመሆኗ ስርዓት አልበኝነትና ህገ ወጥነት መተኪያ የሌለውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወት ቀጥፏል ሲሉ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ፡፡
በትናንትናው ዕለት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ግብአተ መሬት በተፈጸመበት ወቅት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባደረጉት የሀዘን መግለጫ ንግግር፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ህገወጥነት መተኪያ የሌለውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወት ቀጥፏል፡፡
‹‹በነጋ በጠባ ይህን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ችግሩን ለማቃለል ስንታገል ቆይተናል››ሲሉ
የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ‹‹ ከእንግዲህ ትዕግሥታችን ተሟጥጦ ውሳኔ የምንሰጥበት ወቅት ላይ ደርሰናል››ብለዋል፡፡ከ31 ዓመታት በፊት በሰኔ 15ቀን የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ብሎ ለማመን የሚከብድ አሰቃቂ የአውሮፕላን ድብደባ በበርካታ ንጹሃን ወገኖች በትምክህተኛ ኃይሎች መሞታቸውን በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡በተያዘው 2011ዓ.ም ሰኔ 15ቀን የተፈፀመውን ግድያ ማንም ሊያስበው በሚያዳግት መልኩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ በአንድ ቅጥረኛ መሰዋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጀግኖች ለህዝብ ታግለው ለህዝብ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል፡፡
ጀግኖቹ ቢያልፉም የሥራ አሻራቸው ታሪክ ሲዘክረውና ሲያስታውሰው እንደሚኖር የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ህልፈተ ህይወታቸው ያልተጠበቀ ቢሆንም ጨቋኙን የደርግ ሰራዊት ለመደምሰስ ወደ ትጥቅ ትግል ሲገቡም ቀድሞ ህይወታቸውን ለህዝብ ሰጥተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው ሀገሪቱ ወደ ትርምስ ለመክተት በሚፈልጉ ትምክህተኛ ኃይል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ትምክህተኞች አለመረጋጋትና ብጥብጥ እንዲነግስ በማድረግ ስልጣን ለመቆጣጠር እንደሚፈልጉ በባህርዳርና በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸመው ግድያ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የትግራይ የበላይነት›› ማሳያ ተደርገው ለክርክር ይቀርቡ የነበሩ ጀነራሎችን በመግደል የትግራይ ህዝብ እንዲንበረከክ ታሳቢ ያደረገ ጥቃት መሆኑን ጠቁመው፣ ትግራይ ግን ማህጸነ ለምለም በመሆኗ ተተኪ ጀግኖች ሞልተዋታል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የትግራይ ህዝብ ግን አይፈራም፣ አይንበረከክም፣ አይከፋፈልም፣አይበታተንም፣ እርስ በእርሱ አይጠላለፍም አንድነቱን በማጠናከር ልማቱን ያፋጥናል ብለዋል፡፡ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ በጋራ ሆኖ በመታገል የትምክህት ኃይሉን ዳግመኛ ወደማይወጣበት ዋሻ ማስገባት ይገባል ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ፊዮሪ ተወልደ