አስተማሪ መልዕክት!

ይቅርታ መጠየቅ ከሰብአዊ ማንነት የሚመነጭ የትህትና መገለጫ ነው። በተለይም ከፍ ባሉ ማኅበራዊ ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች በተገነባ ማህበረሰብ ውስጥ በእለት ተእለት ህይወት ያለ ትልቅ ሰብአዊ እሴት ነው። እንደ ሰው ፍጹም አለመሆንን ፣ ከስህተት ለመማር ዝግጁ መሆኑንም ይገልጻል፡፡

የሰው ልጅ በፍጥረቱ ፍጹም ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ የዕለት ተዕለት ሕይወቱ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሚፈጠሩ ስህተቶች የተሞላ ነው። እነዚህ ስህተቶቹ በየትኛውም ሁኔታ ይፈጠሩ፣ የትኛውም አይነት ትርጓሜ እና ማብራሪያ ይሰጣቸው ተጨባጭ ከሆነ እውነታ ጋር የሚያስማማው ይቅርታ ነው።

ይህን ታሳቢ በማድረግም የይቅርታ ጉዳይ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በግለሰቦችም፣ በቡድኖችም ሆነ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ላለመግባባት ምክንያት የሚሆኑ ስህተቶች ወደ ኩርፊያና የግጭት ምዕራፍ እንዳይሻገሩ የጎላ ፋይዳም ይኖረዋል።

በተለይም በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውንም ሆነ ሊኖር የሚችለውን ሰላማዊ ግንኙነት አስጠብቆ በማስቀጠል፤ በሕዝብ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነትን ለማግኘት በመንግሥት በኩል የሚቀርብ የይቅርታ ጥያቄ ከፍያለ ስፍራ የሚሰጠው፤ ለሚመራው ሕዝብ ያለውን ከበሬታ የሚገልጽበትም አንዱ መንገድ ነው።

መንግሥት እንደ ተቋም የውሳኔ ሰጪ ግለሰቦች ስብስብ ነው፤ እነዚህ ግለሰቦች ሰው እንደመሆናቸው መጠን በግልም ይሁን በጋራ በሚደርሱባቸው ውሳኔዎች ስህተቶችን ሊሠሩ ይችላሉ። ብዙ ፍላጎቶች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ አይነቱ ሁኔታ የተለየ ገጽታ ሊሰጠው ይችላል፤ ለተለያዩ ትርጓሜዎችም ሊጋለጥ ይችላል።

በለውጥ ወቅት ከሚፈጠር ማኅበረሰባዊ /ሀገራዊ/ መሻት አንጻር በመንግሥት በኩል የሚቀርቡ ሕዝብን ይቅርታ የመጠየቅ መልካም አካሄዶች፤ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለው የሕግ እና የሞራል መስተጋብር ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ከማስቻል ባለፈ በለውጡ ተስፈኛ የሆነው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን አመኔታ ጠብቆ ማስቀጠል እንዲቻል ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ሕዝቡ የለውጡ ባለቤት እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ለውጡን በተሻለ የባለቤትነት መንፈስ ማስቀጠል የሚያስችለውን አመኔታ ይፈጥርለታል፤ ካልተገባ ኩርፊያ እና ከለውጥ የመነቃቃት መንፈሱ እንዳይቀዛቀዝ ትልቅ ጉልበት ሊፈጥርለትም ይችላል፤ ከሁሉም በላይ የመንግሥት ሹመኞች ሊሳሳቱ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለና ለዚህ ስህተታቸውም ይቅርታ መጠየቅ የሚችል ሰብአዊ ማንነት እንዳላቸው ያመላክታል።

በርግጥ እኛ ኢትዮጵውያውያን በዘመናት በትውልዶች መካከል የተፈተነ እና እንደ ሕዝብ በመላው ዓለም እወቅና ያስገኙልን የብዙ ማህበራዊ ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ባለቤቶች ነን። ከይቅርታ ጋር የተያያዘው ማህበረሰባዊ ማንነታችንም ቢሆን የዚህ እውነት አንድ አካል ተደርጎ ይወሰዳል።

የግለሰባዊ ፣ ቡድናዊም ሆነ ማህበራዊ አለመግባባቶች ምንጭ የሆኑ ስህተቶችን በይቅርታ ማለፍ በዘመናት ውስጥ የዳበረው የእርቅ ባህላችን ዋንኛ መገለጫም ነው። የሀገሪቱ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ለመቀበል ሰፊ ልብ ያላቸው ናቸው ። ይህም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተደጋግሞ የሚስተዋል እና የሚበረታታ ማህበራዊ እሴት ነው።

ይህም ሆኖ ግን ከዚሁ ማህበረሰብ እሴት ውስጥ የሚገነባው የሀገሪቱ ፖለቲካ ሥርዓትም ሆነ ሥርዓቱን የሚፈጥረው የፖለቲካ ስብእና ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ለመቀበል የተከፈተ ልብ የሌለው ሆኖ ቆይቷል። ከዚህ ይልቅ ይቅርታ መጠየቅን እንደ ትልቅ ውርደት እና ሽንፈት አድርጎ ሲወስድ ኖሯል።

ከዚህ የተነሳም በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ያልተለመደ ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የማይታሰብ ሆኖ ዘመናት ተቆጥረዋል። በዚህም በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ከኃይል ባለፈ ይቅርታ በሚወልደው ትህትና የመቃኘት እድል ሳያጋጥመው ዘመናትን ተሻግሯል።

ይህም ሕዝቡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ውሳኔ ሰጪ ግለሰቦችን /ሹማምንቶችን/ ለሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ አድርጎ የማየት የተሳሳተ ማህበራዊ ቅኝት እንዲኖረው አድርጓል፤ እነዚህ ውሳኔ ሰጪ ግለሰቦች /ሹማምንቶች/ ከሕዝቡ የሚጋሩትን ትልቁን ማህበራዊ እሴት እንዲያጡም አድርጓቸዋል። ይህ የተዛባ ማህበረሰባዊ እሳቤ በመንግሥት እና በሕዝቡ መካከል ያለውን የሕግ እና የሞራል መስተጋብርም ጤናማ እንዳይሆን አድርጎታል።

ይህን እንደ ጥላ ሲከተለን ዘመናት ያስቆጠረ ሀገራዊ /ማህበረሰባዊ/ ችግር ለመሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያዘም ሆነ በሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎች በየትኛውም ምክንያት ሊፈጠሩ ለሚችሉም ሆነ ለተፈጠሩ ስህተቶች ሕዝብን በአደባባይ ይቅርታ መጠየቃቸው ትልቅ ጅማሬ፤ ከፍያለ እውቅና ሊሰጠው እና ሊበረታታ የሚገባ ተግባር ነው!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You