አዲስ አበባ፣ ‹‹የግድያ ድርጊቱ በሀገራችን ከስልጣንና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የነበሩ የመጠፋፋት ባሕሎች ዳግም ላይከሰቱ፤ የተሻገርነውን ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት በመሆኑ ሁሉም በነቂስ ሊያወግዘውና በጽናት ሊታገለው ይገባል፤››ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
ትናንት በባሕርዳር ስታድየም ተገኝተው በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለተሰዉ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአስከሬን ስንብት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የተፈጸመው ድርጊት የሕዝባችንን ታሪክ የማይመጥን ፤በጭካኔ የታጀበ አረመኔያዊ ድርጊት ነው፣ ድርጊቱ በሀገራችን ከስልጣንና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የነበሩ የመጠፋፋት ባሕሎች ዳግም ላይደገሙ የተውናቸውን ወደኋላ የመለሰ አደገኛ ክስተት ነው፡፡ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈጸመው የግድያ ድርጊት የሕዝባችንን ታሪክ የማይመጥን ፣እጅግ አሳዛኝና ጨካኝነት የተሞላበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ ለሕዝብ አገልግሎት ሕይወታቸውን፣ ማሕበራዊ መስተጋብራቸውን የሰጡ ፤ለለውጡ ከባድ ዋጋ ከፍለው ለብዙዎች ነጻነትን ካወጁና ለመጪው ዘመን ብርቱ ክንድ ሆነው በተሰለፉ የለውጥ ዘዋሪዎች ላይ እንዲህ አይነት መርዶ መስማት እጅግ ከባድ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እጅግ ውስጥን የሚያደማ ጉዳት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በያዝነው የሰኔ ወር እኩሌታ ለስራ ጉዳይ ወደ ውጭ ሀገር ባቀናሁበት አጋጣሚ ከመድረሴ በመጀመሪያ የተቀበልኩት የስልክ ጥሪ ለማመን የሚከብድ፤ ሰውነትን በድንጋጤ የሚያርድ እንዲሁም ልብን በሀዘን የሚሰብር እኩይ መልእክት የያዘ ነበር ብለዋል፡፡
ዛሬ ያጣናቸው ወንድሞቻችን ጓዶቻችንን ወደ ውጭ ከመውጣቴ ከሰዓታት በፊት ከሦስቱም ጋር በተከታታይ ስለመጪው ሥራዎቻችን እኔ በሄድኩበት ጉዞ ልሰራቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ምክረ ሀሳቦቻችንን በስልክ ተወያይተን ነበር ሲሉ ገልጸዋል።ሰው ባሰበው አይውልምና ያልተጠበቀው ሆነ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ታዲያ የሀገሬ ሰው ይህን ምን ይሉታል? ሲሉ ጠይቀው እጅግ አሳዛኝ፣ ትራጂክ፣ ጨካኝነት የተሞላበት ድርጊት ነው ሲሉ የተፈጸመውን ወንጀለኛ ድርጊት አውግዘዋል፡፡
በሕዝቡ ባለቤትነትና በአዴፓ መሪነት ለለውጡ ምክንያት ከሆኑት ዋና ዋና አጀንዳዎች ነጻነትን ለማስፈንና ሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለማረም በግንባር ቀደምትነት የታገሉ ጓዶቻችን ‹‹በእስር ቤት ያሉ ጓዶቻችን ተስፋቸው ጨልሟል ፤ አካላቸው ጎድሏል ፤ የሕሊና እስረኛ ሆነዋል›› ብለው በግንባር ቀደምትነት ለታገሉ መሪዎች ምላሹ ጥይት መሆኑ ምን አይነት እንቆቅልሽ ፣ክህደትና ከእናት ጡት ነካሽነት ውጪ ምን ሊባል ይችላል?
‹‹ለፌዴራልና ለክልል ተልዕኮ መሳካት በተሰለፉበት አውድ ውስጥ ሆነው ከልጅነት እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው በሥራ ላይ እያሉ ሰሞኑን ሕይወታቸው ላለፈው የመከላከያ የጦር መኮንኖችና ለድርጅታችን ከፍተኛ አመራሮች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን በራሴና በመንግሥት ስም ለመግለጽ እወዳለሁ›› ብለዋል ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ወንደወሰን መኮንን