ወርቃማ የሕይወት ሕጎች

በሕይወታችን ውስጥ የምንመራባቸው ሕጎች ወይም መርሆች ቢኖሩ መልካም ነው። ምክንያቱም ሕጎችና መርሆች እንድንለወጥና ቆራጥ እንድንሆን ያደርጉናል። የሚገርመው ነገር በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ያልተፃፉ ሕጎች አሉ። አንዳንዶቹ ጠቃሚ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ጎጂ ናቸው።

ያልተፃፈ ሕግ ማለት አልተደነገገም፣ የሚያስገድደን ሰው የለም ግን ሁሌ እንተገብረዋለን። ለምሳሌ በቀን ሁለቴ ወይ ሶስቴ እንድትበላ የሚያስገድድህ ሰው ወይም ሕግ የለም። ግን ታደርገዋለህ። ለምን? ስለሚጠቅምህ። በዚህ ፅሁፍ የሚቀርቡ ሕጎች አልተፃፉም። ግን ሕግ ናቸው። ሕይወታችን ላይ በጣም ይጠቅሙናል። እንደውም አንዳንዶቹ ሲገለፁ እስከዛሬ እንዴት አልሰማዋቸውም ? ያስብላሉ። እንሆ ወርቃማዎቹ የሕይወት ሕጎቹ….

1ኛ. ራስህን ለማወቅ ጊዜ ውሰድ

ምንድን ነው የሚያስደስትህ? በሕይወትህ ምንድን ነው የምትፈልገው? ላንተ ትርጉም የሚሰጥህ ነገር ምንድን ነው? ምን መማር፣ ምን መስራት፣ ምን አይነት ገቢ እንዲኖርህ፣ ምን አይነት ፍቅር ሕይወት፣ ምን አይነት ትዳር እንዲኖርህ ነው የምትፈልገው? ጊዜ ውሰድና አስብ። አንድ አንድ ሰው የሆነ ቀን ተነስቶ ፀሎት ያደርስና ‹‹አንተ ለካ መጸለይ ሰላም ይሰጣል›› ይልሃል። ከዛ ግን አይደግመውም። ሕይወቱ ላይ አይተገብረውም። አንዳንድ ሰው የሆነ ቀን ደስ ሲለው ስፖርት ይሰራና ‹‹አንተ ስፖርት መስራት ለካ ቀለል ያለ ስሜት ይፈጥራል›› ይልሃል። አይደግመውም። በዘፈቀደ የምንኖርበት ጊዜ ማብቃት አለበት። ማቀድ አለብን። ምን እንደምንፈልግ ማሰብና ማወቅ አለብን። ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ሰው ሁሉም መንገድ የሚያደርሰው ይመስለዋል። ራስህን ለማወቅ ግዜ ውሰድ፤ ወሳኝ ሕግ ነው።

2ኛ.ያንተ ስራ መዝራት ነው

ያንተ ስራ መዝራት ነው፤ የሚያበቅለው ደግሞ ፈጣሪህ ነው። ያንተ ስራ መልካም መሆን ነው። መልካም ሰው ወደ ሕይወትህ የሚያመጣው ፈጣሪ ነው። መልካም ጓደኛ፣ መልካም ፍቅረኛ፣ መልካም የትዳር አጋር የሚሰጥህ ፈጣሪ ነው። አንተ ብቻ መልካም ሁን። ያንተ ስራ የሚጠበቅብህን ሁሉ ማድረግ ነው። ውጤቱን የሚሰጥህ ፈጣሪህ ነው። ያንተ ስራ መሞከር ነው። የሚያሳካው ፈጣሪ ነው። አየህ! ገበሬ ከዘራ፣ ከኮተኮተና ውሃ ካጠጣ የዘራው እንደሚበቅል እርግጠኛ ነው። አንተም የሚጠበቅብህን ካደረክ ፈጣሪ ሌላውን ያደርጋል። በከንቱ አትጨነቅ። አንተ መቀየር የማትችላቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አታድርግ። አንተ የምትቀይራቸው ነገሮች ላይ አተኩር። ያንተ ስራ መዝራት ብቻ ነው።

3ኛ. የመጣህበትን አስብ

ብዙ ሰው የሆነ ነገር ይጀምርና የሚያቆመው የቀረውን አስቦ ‹‹ውይ! በጣም ብዙ ይቀረኛል›› ብሎ ተስፋ ቆርጦ ነው። አንተ ግን የቀረህን ሳይሆን የመጣህበትንና የጨረስከውን አስብ። ብዙ ነገር ጨርሻለሁ፣ ብዙ ነገር አሟልቻለሁ፣ ትንሽ ነው የቀረኝ ማለት አለብህ። የጎደለህን አትይ። ጉድለትህን የምታይ ከሆነ ተስፋ ትቆርጣለህ። አንድ ሰው ወርቅ ለማግኘት ቆፍሮ ቆፍሮ መጨረሻ ላይ አንድ እርምጃ ሲቀረው ተስፋ ቆርጦ ቦታውን ሸጦ ወጣ። ተረኛው ፈላጊ መጥቶ በአንድ እርምጃ ቁፋሮ ወርቁን አገኘ። የመጀመሪያው ሰው ምን ያህል ዘመን እንደሚቆጨው አስቡት። አንተም ለፍተሃል፣ ብዙ ቦታ ደርሰሃል። ታዲያ ለምንድን ነው የቀረህን ነገር አስበህ ተስፋ የምትቆርጠው ? የመጣህበትን አስብ ያኔ ተስፋ ይኖርሃል።

4ኛ. እድል የሚመጣው ለሚዘጋጅ ነው

ለምሳሌ አንድ ሰው ሎተሪ እንዲደርሰው ምን ያድርግ ብትባሉ መጀመሪያ ሎተሪ ይቁረጥ ትላላችሁ። አንድ ሎተሪ መቁረጥ ግን በቂ ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ስለሚቆርጡ ያ ሰው ላይደርሰው ይችላል። ስለዚህ እድሉን ለማስፋት በርካታ ሎተሪ መቁረጥ ይጠበቅበታል። በጣም ብዙ ሎተሪ ከቆረጠ ምን አልባት ሊደርሰው ይችላል። አያችሁ በሕይወትም በጣም ጠንክሮ የሚሰራ የሚሰራ ሰው፣ ጠንክሮ ገንዘቡን የሚያስቀምጥ ሰው፣ ጠንክሮ እውቀት የሚሰበስብ ሰው እድሉን እያሰፋ ነው። ብዙ ሎተሪ እንደሚቆርጥ ሰው ነው። ምክንያቱም የሆኑ እድሎች ሲመጡ እሱ በገንዘብም፣ በእውቀትም በብዙ ነገር ተዘጋጅቷል። ይጠቀምበታል።

ካልተዘጋጀህ ግን እድሉ ቢመጣ ራሱ ታባክነዋለህ። ይቆጭሃል። ‹‹ወይኔ! ገንዘቡን ባስቀምጥ ኖሮ አሁን ይህች ቢዝነስ ታዋጣኝ ነበር›› ትላለህ። አሁን አስቀምጥ፤ አሁን ተዘጋጅ! መዘጋጀት በራሱ በራስ መተማመን ይሰጥሃል። ልበ ሙሉነት ይሰጥሃል። ስትዘጋጅ እኔ ነገን አልፈራም ብዙ ነገር ላይ ሂይወቴ ላይ እየበረታሁ ነው፣ እየተለወጥኩ ነው፣ ነገ አያስፈራኝም ትላለህ። ወሳኝ ሕግ ነው እድል የሚመጣው ለሚዘጋጅ ነው።

5ኛ. ልታደርገው የምታስበውን

ነገር ሁሉ አትናገር

የሚገርም ሕግ ነው። ምክንያቱም ራዕይ የምትኖረው፤ የምታደርገው ነገር እንጂ የምትናገረው አይደለም። ለሰዎች በተናገርከውና በዘራኸው ቁጥር አቅም ታጣላህ። ያወራኸውን ወሬ ብዙ ግዜ አታደርገውም። ባትናገር ጥሩ ነው። በተለይ የሚጠቅምህ ካልሆነ፣ ያ ሰው ሕልምህ ላይ የሚረዳህ ካልሆነ ለምን ትነግረዋለህ? ሰምቶ ዝም ለሚልህ ወይ ደግሞ አትችልም እንደው ቢቀርብህ ለሚልህ ሰው ለምን ትነግረዋለህ? አትንገረው። አንተም ጉልበት ታጣለህ። አንዳንዴ በውስጥ የታመቀና ልውጣ ልውጣ የሚል ሀሳብ አለ። ግን ለራስህ ንገረው። ይህንን ነገር በንግግር አይደለም በተግባር ነው የምገልጠው በል። አንዳንድ ግዜ ህልሞች ወይም ራዕዮች በተግባር የምንተገብራቸው ናቸው። ስራህ ራሱ ጮሆ ይናገር። አንተ መናገር አይጠበቅብህም። የምታስበውን ሁሉ ለሰዎች አትናገር። በጣም ወሳኝ ሕግ ነው።

6ኛ. ነፃ ምሳ የለም

ንጉሱ ጠቢባንን ሰብስቦ ለሕዝቤ የሚሆን ጥሩ መልዕክት ፅፋችሁ አምጡ አላቸው። መፅሃፍ አመጡለት። ‹‹መፅሃፍማ ረጅም ነው አያነቡትም›› አላቸው። አሳጥረው በአስር ገፅ አመጡለት ‹‹ይህንን ሁሉማ ማንም የሚያነብ የለም›› አላቸው። አሁንም አሳጥረው በአንድ ገፅ አመጡለት። ‹‹ይህም በዛ›› አላቸው። ‹‹በቃ! አንድ አረፍተ ነገር አድርጉት›› አላቸው። ጠቢባኑ ተማክረው አንድ አረፍተ ነገር ይዘው መጡ። ‹‹ነፃ ምሳ የለም!›› የሚል።

ምን መሰለህ አንተ ካለፋህና ካልጣርክ በነፃ የምታገኘው ነገር የለም። በተለይ አጥብቀህ የምትፈልገው ነገር ትልቅ ከሆነ ትልቅ ልፋት ካንተ ይጠበቃል። አንድ ፎቅ ትልቅ እንደሆነ የምታውቀው ፎቁ ሲያልቅ አይደለም። ሲቆፈር ነው፣ መሰረቱ ነው ትልቅ የሚያስብለው። አንተም መዘጋጀት አለብህ። ትልቅ ነገር ከፈለክ ትልቅ ልፋት እንዳለብህ አስብ። በነፃ የምታገኘው ነገር የለም። የሆነ ሰው ከመሬት ተነስቶ አንተ ጎበዝ ነህ ብሎ የመቶ ሺ ብር ደሞዝተኛ አያደርግህም።

የመቶ ሺ ብር ደሞዝተኛ ለመሆን አንተ መቀየር አለብህ። መልፋት አለብህ። አየህ! ስበት የሚሰራው አንተ ከተለወጥክ ነው። አንተ ስትለወጥ የምትፈልጋቸው ነገሮች ወዳንተ ይሳባሉ። ወዳንተ ይመጣሉ። አንተ ትልቅ ነገር የምትፈልግ ከሆነ ትልቅ ነገር የሚገባው ሰው ሁን። ያኔ ሁሉም ይመጣል። ነፃ ምሳ የለም ወዳጄ!

7ኛ. ፍርሃትህን መጋፈጥ ተለማመድ

በጣም አጥብቀህ የምትፈልጋቸው ነገሮች ያሉት ከፍርሃትህ ጀርባ ነው። አየህ! ለውጥ ከፈለክና ፍርሃት ከያዘህ በቃ ትልቅ ነገር ሊያመልጥህ ነው። ስለዚህ መለወጥና ራስህን ማሳመን አለብህ። ጥልቅ መሻት ያለው ሰው በፍፁም ፍርሃቱን ይጋፈጣል። የማይፈራና ጥርጣሬ የማይሰማው የለም። ሁሉም ሰው ትንሽዬም ቢሆን ፍርሃት አለበት። ፍርሃትህን የምታሸንፈው ግን በፍላጎትህ፣ በጥረትህና በጥልቅ መሻትህ ነው። ምን ያህል ትፈልገዋለህ ያንን ነገር? ያኔ ዋጋ ትከፍልለታልህ። ያንን ነገር ባታደርግ የምታጣውንና የሚጎድልብህን አስብ። ያንን ነገር ደግሞ ታገኝ የምታደርገውን አስብ። ሽልማቱን፣ ውጤቱንና እርካታውን አስበው። ያኔ አትፈራም። ትደፍራለህ። ታደርገዋለህ። ለአይምሮህ ደግሞ ደፋር እንደሆንክ ንገረው። አይምሮህን ከነገርከው፣ አንተ ጥልቅ ፍላጎት ካለህ የምትፈራው ነገር አይኖርም። ስለዚህ ፍርሃትህን መጋፈጥ አለብህ።

8ኛ.ከትናንት ዛሬ መሻል አለብህ

እየኖርክ ነው የምትባለው ስለምትተነፍስ ብቻ አይደለም። ስታድግም ነው። በየቀኑ በትናንሹ ማደግ ጫፍ ላይ ያወጣሃል። ጀምስ ክሊር የተባለ ታዋቂ ራስን የማበልፀግ ፀሃፊ ‹‹በየቀኑ አንድ ፐርሰንት ብታድግ በዓመቱ መጨረሻ ላይ 37 እጥፍ ትለወጣለህ›› ይላል። ይህ ማለት በየቀኑ አንድ ፐርሰንት ብታነብ ወይ አዲስ ነገር ብትጨምር 37 እጥፍ እውቀት ይኖርሃል። 37 እጥፍ ገቢህ ሊያድግ ይችላል። በሁሉም አቅጣጫ በ37 እጥፍ ታድጋለህ። ትናንሽ ለውጦች ሕይወት ይቀይራሉ። በየቀኑ ማደግ አለብህ። አንድ መስመር፣ አንድ ገፅም ቢሆን ማንበብ አለብህ። ከትናንትህ ጥፋት ዛሬ መማር አለብህ። ዛሬ ምን አበላሸሁ፣ ምን ላስተካክል ማለት አለብህ። ከሰዎች ጥፋት መማር አለብህ። በየቀኑ አዳዲስና ትናንሽ ለውጦች፣ እድገቶች፣ አውቀቶች ያስፈልጉሃል። ከትላንት ዛሬን መሻል አለብህ ወዳጄ!

9ኛ.ምንም ነገር ስትሰራ መቶ ከመቶ ሁን

ምንም ነገር በሙሉ ልብህ ማድረግ አለብህ። በግማሽ ልብ የምትሰራቸው ነገሮች ግማሽ ውጤት ነው የሚሰጡህ። የተሟላ ነገር አታገኝም። በተለይ የምታምንበት፣የምትወደው ነገር ሲሆን በሙሉ ሀሳብህ፣ በሙሉ ትኩረትህ መስራት አለብህ። ያ ነው ከሰው በላይ የሚያደርግህ። ውጤት የሚሰጥህ። ስለዚህ ትኩረት በጣም ወሳኝ ነው። ሀሳብህን ሰብስበህ ስትሰራ ጉልበትህ ወደ አንድ አቅጣጫ ይሰበሰባል። ጥሩ ለውጥ ታመጣለህ። ተጠቀምበት! ምንም ነገር ስትሰራ መቶ በመቶ ሁን።

10ኛ.ሁሉንም ለማስደስት አትሞክር

መለወጥ ከፈለክ ምርጡ ግዜ አሁን ነው። አየህ! አሁን መለወጥ ካሉብህ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሁሉንም ሰው ማስደሰት አለብኝ የሚለውን ሕግ መሰረዝ ነው። ራስህን አስደስት። ለምትወዳቸውና ለምታከብራቸው ሰዎች ቅድሚያ ስጥ። ሁሉንም ሰው አስደስታለሁ ብለህ ግን ብኩን ሰው መሆን የለብህም። አየህ! ካረጀህና እድሜህ ካለፈ በኋላ የሚቆጭህ ካደረከው ይልቅ ያላደረከው ነው። ‹‹ምን አለ ይህን ባደርገው ኖሮ! ምን አለ እንዲህ ቢሆን ኖሮ!›› ትላለህ። ስለዚህ ሁሉንም ለማስደሰት የምታርገውን ጥረት ከአሁኑ አቁም።

11ኛ.ዝም ብለህ ቀጥል

አንዳንዴ ፍላጎት ታጣለህ። ማቆም ትፈልጋለህ። ትሰለቻለህ። ሕይወቱ፣ ትምህርቱ፣ ስራው ትርጉም ያጣብሃል። በቃኝ ትላለህ። ግን ዝም ብለህ ቀጥል። ምን መሰለህ? የምትፈልገውን ለማግኘት አንዳንዴ የማትፈልገውን መስራት ሊኖርብህ ይችላል። ሕይወት እንደዛ ነው። አየህ አንዳንዴ ዝምብለህ መቀጠል ትርጉም ይሰጥሃል። ማቆም ግዚያዊ ስሜት ነው። አሁን ብታቆም ትልቅ ነገር ሊያሳጣህ ይችላል። አልፎ ቆይቶ ነው የሚቆጭህ። ስለዚህ ዝም ብለህ ቀጥል። ጉሙ እስከሚታይህ ሂድ። አንዳንዴ እኮ ጉሙ የሚሸፍንህ፣ የሚጋርድህና ድምበር የሚሆንብህ ይመስልሃል እንጂ አያቆምህም። እስከሚታይህ ሂድ። ማቆም የለብህም። ዝምብለህ ቀጥል።

12ኛ.ከምታገኘው ላይ ለፈጣሪህ ስጥ

ክርስቲያን ከሆንክ መባ ወይም አስራት መስጠት አለብህ። ሙስሊም ከሆንክ ደግሞ ዘካ ማውጣት አለብህ። ምን መሰለህ? ለመንግስት ግብር ትከፍላለህ። ደህንነትህን ስለሚያስጠብቅልህ። በሰላም ወጥህ ስለምትገባ። ከሌባ ስለሚጠብቅህ። ወይ ደግሞ መሰረተ ልማት ስለሚሰራልህ። ለመንግስት አስራምስትም ይሁን ሀያና ሰላሳ በመቶ ግብር ትከፍላለህ። አየህ ፈጣሪህ ደግሞ ጤና ሰጥቶሃል። ወጥተህ እንድትገባ፣ ሰርተህ እንድታገኝ ሁሉን ነገር ሰጥቶሃል። እውቀቱን አሁን ያለህን ማንነት ሰጥቶሃል። ስለዚህ መክፈል አለብህ።

13ኛ.ከማይመስሉህ ሰዎች ራቅ

አንዳንዴ ማደግህን የምታውቀው በጣም የቅርቤ ናቸው ከምትላቸው ጓደኞችህ መራቅ ስትጀምር ነው። ለምን መሰለህ? እነሱ ካልተለወጡና ካላደጉ አንተ ቆመህ መቅረት የለብህም። ከሚሮጡት ጋር ነው መሮጥ ያለብህ። አንድ አይነት ቀለም ያላቸው ወፎች ናቸው አብረው የሚበሩት። አየህ! ጓደኞችህን መጥላትና መተው አይደለም ያለብህ። ግን እነርሱ ካልተለወጡና ካላደጉ አንተ ቆመህ መቅረትህ ነው። ማደግ አለብህ። ለትንሽ ግዜም ቢሆን ስትርቃቸው ለእነርሱም ቢሆን ትተርፋለህ። አየህ! ውሎህ በጣም ወሳኝ ነው። አሁን አጠገብህ ያሉትን ሰዎች ሕይወትህ ላይ እነርሱን መሆን ትፈልጋለህ? እንደነርሱ ገቢ እንዲኖርህ፣ እንደነርሱ ጥሩ ትዳር እንዲኖርህ ትፈልጋለህ? እንደነርሱ መሆን ከፈለክ ከእነርሱ ራቅ። ከሚመስሉህ ጋር ዋል። የማይመስሉህን ሰዎች ራቃቸው። ሕይወትህን ባዶ ያደርጉታል። ሕይወትህን የሚቀይረው ውሎህ ነው!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You