የኢድ አልአድሃ በዓል የመረዳዳት እና የመደጋገፍ በዓል ነው›› – ሀጅ ጦሃ ሃሩን -የአንዋር መስጊድ ኢማም

በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የኢድ አልአድሃ (አረፋ) በዓል አንዱ ነው። ኢድ አል አድሃ ወይም አረፋ ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸው እስማኤልን በአላህ ትእዛዝ ለመስዕዋት ሲያዘጋጁ በምትኩ ሙክት በግ መቅረቡን የሚያስታውስ በመሆኑ የመስዋዕት በዓል ተብሎም ይከበራል። አዳምና ሄዋን ከገነት ወጥተው ለረጅም ዘመናት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአራራት ተራራ ላይ መገናኘታቸው የሚዘከርበት በዓል መሆኑንም የሃይማኖቱ አባቶች ይናገራሉ።

ኢድ አልአድሃ የመተሳሰብና መረዳዳት በዓል ከመሆኑም ባሻገር ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን አረፋ እርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምህረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል። ይህም ያጡ ወገኖች የሚደገፉበትና መረዳዳትና መደጋገፍ የሚታይበት በመሆኑ በዓሉ የተለየ ገጽታ ይዞ ይከበራል።

አዲስ ዘመን – የኢድ አልአድሃ በዓል የሚከበርበት ምክንያት ምንድን ነው?

ሀጅ ጦሃ ሃሩን – ሀጅ ማድረግ ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች አንዱ ነው። ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ መካን ዘይረው መመለስ አለባቸው። መካ በመገኘትም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ።

ቅዱስ ቁርዓንና ሌሎች ተያያዥ ጽሁፎች እንደሚያብራሩት የዒድ አል-አድሃ ታሪካዊ ዳራ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅ ያሳየው የተለየ ጽናት ነው። ነቢዩ ኢብራሂም የበኩር ልጃቸው የሆነውን ዒስማኢልን ያገኙት በእርጅና ዘመናቸው ነው። ታላቅ ሚስታቸው ሳራ ለፍሬ ባለመብቃቷ “ያ አላህ ያለ ዘር አታስቀረኝ፤ እኔን የሚተካ ሷሊህ የሆነ ልጅ ስጠኝ” በማለት ዱዓ አደረጉ። በዚሁ መሠረት በሳራ ፈቃደኝነት ሐጀራ የምትባለውን የቤት ሠራተኛቸውን አገቡ። ሐጀራም ዒስማኢል የተባለ ልጃቸውን ወለደችላቸው። ይህ ልጅ በአላህ ፈቃድ በመካ ከተማ እንዲያድግ የተወሰነ ስለነበረ ኢብራሂም ሐጀራን እና ዒስማኢልን ወደ ዐረቢያ ከተማ ወሰዷቸው።

ዒስማኢል ካደገ በኋላ ደግሞ አላህ “ልጅህን እንድትሰዋ ታዘሃል” የሚል ትዕይንት በህልማቸው አሳያቸው። የነቢያት ህልም ደግሞ ከራዕይ የሚቆጠር ነው። ስለዚህ ኢብራሂም በህልማቸው ያዩትን በዝምታ አላለፉትም። በወቅቱ የሆነውን ቅዱስ ቁርዓን እንዲህ ይተርካል።

ከርሱ ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜም “ ልጄ ሆይ! እኔ በህልሜ የማርድህ ሆኜ አይቻለሁ፤ (እስቲ አንተም ነገሩን) ተመልከት። “ምን ይታይሃል” አለው። (ልጁም) አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ፈጽም፤ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ሆኜ ታገኘኛለህ አለ” (ሱረቱ -ሷፍፋት፤ 102) አባትና ልጅ በዚህ መንገድ ከአላህ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሊፈጽሙ ተነሱ፤ ነቢዩ ኢብራሂም ልጃቸውን እንዲሰው የታዘዙት ከአረፋት መሬት ብዙም ባልራቀ ቦታ ላይ ስለነበረ ወደዚያው ጉዞ ጀመሩ። በመንገዳቸው ግን ኢብሊስ በሰው ተመስሎ በጣም ተፈታተናቸው፤ ሶስት ጊዜ ያህል እየወጣ “ ከስንት ዓመት በኋላ ያገኘኸውን አንድዬ ልጅህን ስትሰዋ ምንም አይጸጽትህም?… እንዴት ጅል ትሆናለህ” እያለ ሞገታቸው። ከአላህ ትዕዛዝ ፍንክች የማይሉት ኢብራሂም ግን ድንጋይ ከመሬት በማንሳት “አዑዙቢላሂ ሚነ-ሸይጣኒ ረጂም” እያሉ ኢብሊስን ወገሩት።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ነብዩ ኢብራሂም ዒስማኢልን ሊያርዱት አጋደሙት። ልጁም ምንም ሳያንገራግር ከመሬቱ ላይ ተኛ። ኢብራሂም ልጁን ሊያርዱት ሲሞክሩ ግን ቢላዋው አላርድ አላቸው። ኢብራሂም እንደገና ቢላዋውን ገዘገዙት። ነገር ግን ፈጽሞ ዶለዶመ። ልጁ የሆነው ነገር አልገባውም። አባቱ ቶሎ ስላላረደው ተገረመና “አባዬ! ፣ ምናልባት የአባትነት ፍቅር ይዞህ ይሆናል በቶሎ ያላረድከኝ፤ እስቲ ዓይኔን በጨርቅ ሸፍነውና እርዱን ሞክር” የሚል አስተያየት ሰጠ።

በዚህን ጊዜ ግን ከወደ ሰማይ ጥሪ መጣ። የአላህ መልአክ “ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” በማለት አወጀ። በምትኩም መልአኩ ከገነት ያመጣውን በግ እንዲያርድና ልጁን ወደቤቱ እንዲወስደው ነገረው። በዚህም መሠረት በጉ ታረደ። ኢብራሂምና ዒስማኢልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ። ሁለቱ ሰዎች ለፈጣሪ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል-አድሃ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ። ዒስማኢል ለመስዋእትነት የቀረበበት ድርጊት ደግሞ በዚሁ ዕለት የሚታረደው “ኡድሒያ” መነሻ ሆነ።”

ይህን ታሪክ መነሻ በማድረግ ኢድ አል-አደሃ ይከበራል። በዓሉ የመስዋዕት፣ የእርድ በዓል ነው። በተለይም የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታ አለበት። በተለይም በግ ማረድ የበለጠ የተወደደ ተግባር ነው።

ይህን ታሪክ መነሻ በማድረግ ኢድ አል-አደሃ ይከበራል። በዓሉ የመስዋዕት፣ የእርድ በዓል ነው። በተለይም የሐጅ ጸሎት የሚፈጽም ሰው በዚህ ቀን ከብት የማረድ ግዴታ አለበት። የተቀረውም ሙስሊም ዕለቱን አቅሙ በፈቀደ ከብት በማረድ ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ጋር ያሳልፈዋል። ለኢድ አል አድሃ አንድ ሰው ከሚያርደው ከብት ሲሶውን ብቻ እንዲወስድ ነው ደንቡ። የተቀረው ሲሶው ለዘመድ አዝማድ፣ ሲሶው ደግሞ አቅም ለሌለው ደሃ እንዲከፋፈል እስልምና ያዛል።

የአረፋ በዓል ታላቅ በዓል ነው። ከበዓሉ ቀን አንድ ቀን አስቀድሞ ወይንም የዋዜማው ቀን አረፋ ይባላል። የእስልምና እምነት እንደሚያስተምረው አረፋ የሚለው ቃል በዐረብኛ “አወቀ” እንደማለት ነው። ይህም ታሪክ አለው። አዳምና ሔዋን ወይንም አደምና ሃዋ ከጀነት ወደ ምድር ከወረዱ በኋላ ለብዙ ዘመናት ተጠፋፍተው ነበር። ለረጅም ጊዜ ሲፈላለጉ ከቆዩ በኋላ በዚህ ዕለት በሳዑዲ ዐረቢያ ባለው የአረፋ ተራራ ላይ ተገናኙ። እዚያም “ዐረፍቱከ… ዐረፍቱኪ” ተባባሉ። “አወቅኩህ! አወቅኩሽ” ማለታቸው ነው። ይህንን ታሪክ ለመዘከር ሲባል ነው የዐረፋን በዓል ማክበር የተጀመረው ይህ በዙልሂጃ ዘጠነኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው።

አዲስ ዘመን – የኢድ አልአድሃ በዓል እንዴት ይከበራል ?

ሀጅ ጦሃ ሀሩን – የኢድ አልአድሃ በዓል በሁለት አይነት መልኩ ይከበራል ብለን መውሰድ እንችላለን። አንደኛው ኃይማኖታዊ መስፈርቶችን ጠብቆ ወደ መካ በመሄድ የሚደረግ የጸሎት ሥነሥርዓት ነው። የሃጂ ተጓዦች ከሚከውኗቸው አበይት ሃይማኖታዊ ተግባራት አንዱና ወሳኙ የአራፋት ተራራን መውጣት ነው። ከመካ በስተምስራቅ 20 ኪሎሜትር ርቆ የሚገኘውን ቅዱስ ተራራ መመልከትና ሃይማኖታዊ ሥነርዓቶችን በዚያው መፈጸም እንደሚገባ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮ ያዛል። በአረፋ ቀን (ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ) የሃጂ ተጓዦች ከሚና ወደ አራፋት ተራራ ይወጣሉ። ጸሀይ እስክትጠልቅ ድረስም ቅዱስ ቁርአን እያነበቡ፣ ፈጣሪን እያወደሱና እና የምህረት እጁን እንዲዘረጋ እየለመኑ ይቆያሉ።

ሁለተኛው ደግሞ ወደ መካ ለመሄድ ዕድልን ያላገኙ በሀገር ውስጥ የኢድ አልአድሃን በዓል በደመቀ ሁኔታ ያከብራሉ። በሀገር ውስጥ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በክልል የመስገጃ ሜዳዎች ሰፊው ሕዝበ ሙስሊም በተገኘበት ይከበራል። ከሰላት በኋላ አቅም ያላቸው ሰዎች በግና ሌሎች እንስሳትን በማረድ አቅም ለሌላቸው ጎረቤቶቻች በማካፈል በዓሉን በጋራ ያሳልፋሉ።

አዲስ ዘመን – በኢድ አልአድሃ የሚታየው መረዳዳት ምን ይመስላል?

ሀጅ ጦሃ ሃሩን ፤ የኢድ አልአድሃ በዓል የእርድ በዓል ነው ። አቅሙ ያለው ለበዓሉ በግ ወይም ከብት አርዶ ከድሆች ጋር ተካፍሎ መብላት ይጠበቅበታል። በየቤቱ አቅም እንደፈቀደ ምግብ አዘጋጅቶ ከዘመድ ወዳጅ ከጎረቤት ጋር መብላት መጠጣትም በዚህ በዓል የተለመደ ነው ።

የዕርድ በዓል በመባል ለሚታወቀው የአረፋ በዓል ከተገኘ በግ፣ ፍየል፣ በሬ የመሳሰሉትን ማረድ ግድ ይላል። አቅሙ ለሌላቸው ሰደቃ መስጠት ኢስላማዊ ግዴታ ነው። በዓሉ እርድና የመረዳዳት በዓል ተብሎ ይታወቃል።

የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል የእርድ ሥነ ሥርዓቱ የሚፈጸመው የኢድ ሶላት ከተሰገደ በኋላ ነው። ነብዩ ኢብራሒም (ዐ.ሰ) የአምላካቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ልጃቸውን ለመስዋእትነት እንዳቀረቡ ሁሉ ሙስሊሞችም ፈጣሪያቸውን ለማስደሰት ትዕዛዙን በአግባቡ እየተገበሩ ይገኛሉ። በአረፋ መረዳዳትና መደጋገፍ ቢስተዋልም በዚህ ወቅት ሚስተዋለው መደጋገፍ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሚከናወን ተግባር ሊሆን ይገባል። የደካሞችን ቤት በማደስ፣ ለጦም አዳሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን ማቅረብ ፤የታረዙትን ማልበስና ወላጅ አልባዎችን መጎብኘት በኢድ አልአድሃ የሚወደድ ተግባር ቢሆንም በሌሎችም ቀናት እነዚህ በጎ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ናቸው።

ማኅበረሰቡ በበዓል ወቅት ከመረዳዳት ባሻገር ሀገራዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጋራ መቆምም ይጠበቅበታል። ሰዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፤ ከአካባቢያቸው ሲፈናቀሉ፤ ሲራቡና ሲጠሙ ዝም ብሎ መመልከት ከእስልምና አስተምሮ አንጻር የሚያስጠይቅ ነው። በተለይም ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት በርካቶች ቤት ንበረታቸውን ጥለው የተሰደዱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህም የኢድ አልአድሃ በዓልን ስናከብር እነዚህን ወገኖች በመጎበኝነትና ወገናዊ ፍቅር በመስጠት ሊሆን ይገባል።

አሁን አሁን የድሆችን ቤት በማደስ፤ ማዕድ በማጋራትና የተጀመሩ ሥራዎች የሚያስደስቱ ናቸው። እስልምና በጣም የሚደግፋቸውና አብዝቶም የሚሠራባቸው ናቸው። ወቅቱ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ መረዳዳት የሚያስፈልግበት በመሆኑ የተለያዩ ድጋፎች ለተፈናቃዮችና ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ማድረስ የግድ ይላል።

በእርግጥ በአሁኑ የመተሳሰብ ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

በዝቅተኛ ኑሮ ሕይወታቸውን ሲገፉ የቆዩ ነዋሪዎችን ቤት በማደስ ዜጎች በተለይም በኋለኛ ዘመናቸው በተሻለ መጠለያ ውስጥ እንዲኖሩ የሚደረጉ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዛሬ የእኛነታችን መገለጫዎች እየሆኑ ነው።በየአመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግሥት፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው።

በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ጊዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው። በተለይም በበዓላት ወቅት አቅመ ደካሞች በዓላትን በእኩል ተደስተው እንዲያሳልፉ በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ሥራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የአይሁድ፤ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖቶችን ተቀብላ ያስተናገደችና ለዘመናትም በመከባበር ላይ እንዲኖሩ ያደረገች ሀገር ናት። በዚህ ረገድ እርስዎ ምን ይላሉ?

ሀጂ ጦሃ ሀሩን ፤ ኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ በርካታ አኩሪ እሴቶች አሏቸው። ከእነዚህ ውስጥ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴቶቻችን በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ መሰናክሎችን በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን ከማዳበራቸውም በላይ ለተበደሉት መሸሸጊያ፤ ለተሰደዱት መጠለያ ሆነው ዘልቀዋል።

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የታለበሱ ሕዝቦች ናቸው። በርሃብም ሆነ በድርቅ፤ በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን የእምነት ልዩነት ሳይበግራቸው ደስታንም ሆነ ኀዘንን በጋራ ያሳልፋሉ። የሀገራችውንም ዳር ድንበር ይጠብቃሉ፤ ወራሪን በጋራ ድል ይመታሉ፤ በልማት ይሳተፋሉ ፤ ሀገራቸውን ጥሪ ስታደርግላቸው ያለምንም ማመንታት ከጎኗ ይቆማሉ። ይህ አንድነታቸውን አብሮነታቸውም ከበርካታ የዓለም ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብርና ግርማ ሞገስ አጎናጽፏቸዋል። በአርአያነትም እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል።

ኢትዮጵያውያን ዘር ፤ ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤ የተራበን ማብላት፤ የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል። እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፤ ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ሕዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው።

ኢትዮጵያውያን ከመካ የተሰደዱ የነብዩ መሃመድ ተከታዮችንና ቤተሰቦችን ተቀብላ በማስተናገድና በማኖርና የጎላ ታሪክ ያላትና ለእስልምና ኃይማኖትም ባለውለታ ተደርጋ የምትቆጠር ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ይህ አኩሪ ታሪክ ሺ ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተቀብላ በእንክብካቤ የምታስተናግድ ሀገር ነች።

ሀገሪቱ ውስጥ አይሁድ ነበሩ አሁንም አሉ ይባላል፤ ክርስትናም ቀድሞ የነበረ ሲሆን እስላም ደግሞ ከ አንድ ሺ አራት መቶ አርባ አራት አመተ ሂጀራ በፊት ነበረ የመጣው። እንግዲህ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ኃይማኖቶች አብረው ኖረዋል። በእርግጥ አብረው ይኑሩ እንጂ የሚበላለጡ ነገሮች ነበሩ። መንግሥታት ሲቀያየሩ ከፍና ዝቅ የሚያስበሉ ነገሮች ነበሩ። ሕዝብ እንደ ሕዝብ ግን በአብሮነት ተቻችሎ ተከባብሮ አብሮ መአድ ቆርሰው አብረው ኖረዋል። አሁን ግን በሀገራችን ኃይማኖቶች እኩል መብት አግኝተዋል ብዬ አስባለሁ። ሁላችን በጋራ በመሆን የኃይማኖቶች ጉባዔ ላይ አብረን እየሠራን ነው።

ሕዝቡ የእስልምና ኃይማኖት በአል ሲመጣ እንደ አንድ ሰው ሆኖ በአብሮነት ተከባብሮ ተደጋግፎ መአድ የሚቆርስበት ሁኔታ ነው ያለው። ሀገራችን ከዚህ ረገድ የዓለም ምሳሌ የምትሆን ሀገር ናት። ሕዝቡ ውስጥ ያለው መከባበርና መቻቻል በየትኛውም ሀገር የሚታይ አይደለም። ሕዝቡ ቀድሞ የነበረውን ሁኔታ ማስቀጠል ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡- የቀደሙ የሀገር እሴቶችን አስከብሮ ከማስቀጠል አንፃር ከሕዝበ ሙስሊሙ ምን ይጠበቃል?

ሀጂ ጦሃ ሀሩን ፤ እኛ ለሕዝበ ሙስሊሙ እያስተላለፍን ያለው መልእክት ሀገራችን በተለይም በዚህ ጊዜ ሁሉም የኃይማኖት አባል ችግሩንም ደስታውን በጋራ እየተቀበለበት ያለበት ሁኔታ መኖሩን ነው። ሁላችንም የግል ኃይማኖት ቢኖረንም ሀገራችን ግን አንድ ናት፤ ይህችን ሀገር ደግሞ ሰላሟን መጠበቅ፤ ልማቷን ማስቀጠል፤ ከዚህ በፊት ይዘነው የመጣነውን የአብሮነት ባህል ማሳደግ ይኖርብናል።

ከበፊቱ የበለጠ መቻቻል ከሚለው እሳቤ ወጥተን መደጋገፍና መተባበር መፈቃቅር ሕዝቡ መገለጫው እንዲሆን መሠራት ይኖርበታል። የነበረን እሴት አሳድገን እጅ ለእጅ ተያይዝን ማደግ ማለፍ ይኖርብናል እላለሁ። በዓሉ የመረዳዳት በዓል በመሆኑ ያለው ለሌለው ያካፍልበታል፤ ያግዝበታል፤ የፈጣሪውን ትዕዛዝ ይፈጽምበታል ብለዋል።

አዲስ ዘመን፡- ሰላም የሁሉም ኃይማኖቶች አስተምህሮ ነውና በሰላም ችግሮችን ከመፍታት ረገድ አማኞችም ሆኑ የሃይማኖቱ መሪዎችም ምን ማድረግ አለባቸው?

ሀጂ ጦሃ ሀሩን ፡– ሁሉም ሃይማኖቶች፤ ሰላምን ፍቅርን አብሮነትን ይሰብካሉ። ያንን አስተምህሮ ደግሞ ወደ ኽዝቡ የሚያስተላልፉት የተማሩ የበቁ አባቶች ናቸው። እነዚህ አባቶች በመመሪያ ውስጥ ያለውን ነው ሕዝቡ ጋር የሚያደርሱት።

እርግጥ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የፖለቲካ አካላት ሰላምን የማይፈልጉ ጥላቻን የሚዘሩ ከሌላ በኩል አልሳካ ሲላቸው የመጣላት ጥላቻን የመዝራት ሁኔታዎች ይታይባቸዋል። እኛ ግን እንደ ኃይማኖት አባት ኃይማኖት የግል ነው ፖለቲካ አይግባ በማለት ሕዝቡን ንፁህ የሆነ መንፈሳዊ አስተምህሮ ማስተላለፍ ይኖርብናል። የኃይማኖት አባት እንደ ስሙ የኃይማኖት አባትነቱን ተርድቶ ከፖለቲካና ከሌሎች ዓላማዎች ማስፈፀሚያ ከመሆን ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።

ሕዝቡም ባለችው አንድ ሀገር እምነቱን በተገቢው መልኩ ለማስፈፀም የሀገር ሰላም ላይ ትኩረት ሰጥቶ በአብሮነት መሥራት ይጠበቅበታል። ለመኖርም፤ በነፃነት ኃይማኖቱን ለማምለክም ቅድሚያ ሀገር መኖር ይኖርባታል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን አሁን ይህንን የቆየ የመከባበር ባህል ለመበረዝ የሚሞክሩ አልጠፉም። ለእነዚህ ሰዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው ?

ሀጂ ጦሃ ሀሩን፡– እኛ የምናስተላልፈው መልእክት ሃይማኖታዊ ነው። የፖለቲካ ችግራችሁን ሌሎች ጥያቄዎቻቸሁን ወደ ኃይማኖታችን አታምጡብን እያልን ነው መልእክት የምናስተላልፈው። በአላህ ፀሎት አድርገን አደብ እንዲሰጣቸው ዱኣ ነው የምናደርገው።

እኛ በእድሜያችን ብዙ መንግሽታትን አይተናል። ብዙ የፖለቲካ አስተሳሰብ የነበራቸውን መንግሽታትን ተመለክተናል። ሁሉም በጊዜ ሂደት አልፏል። የማያልፈው ሕዝብ ነው፤ የማይጠፋው ሀገር ነው፤ የማይጠፋው ኃይማኖት ነው ይሄንን ሕዝቡ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል፤ ሁሉንም ነገር በሰከነ አእምሮ መመልከት ተገቢ ነው።

አዲስ ዘመን – ሀገራችን ብሄራዊ ምክክር እያካሄደች ነው።ይህ ምክክር እንዲሳካ ከኃይማኖት አባቶች ምን ይጠበቃል ?

ሀጂ ጦሃ ሀሩን ፡– ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የእስልምና ኃይማኖትም ችሮችን በምክክር መፍታትን አጥብቆ ይደግፈዋል። ሰዎች በትንሽ በትልቁ ከሚጣሉ ይልቅ በንግግር እና በውይይት ቢፈቱ የተሻለ ነው። ውጤትም የሚያመጣው እሱ ነው። ንትርክና ጭቅጭቅ የሰይጣን መንገድ ነው። ስለዚህም ይህንን መጥፎ መንገድ መዝጋት አለብን። በግለሰብም ይሁን በሀገር ደረጃ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው በምክክር እና በውይይት ብቻ ነው። ከዛ ውጪ ያለው መንገድ አክሳሪ ነው።

በሀገራችን ውይይት እና ምክክር መጀመሩ በጣም የምደግፈው ነው። ከወዲሁ እንኳን በርካታ ችግሮችን እየቀረፍን መጥተናል። በቀጣይም ብዙ መፍትሄዎች ይመጣሉ ብዩ አስባለሁ።

ይህ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ የኃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው። የኃይማኖት አባቶች ሲናገሩ ሁሉም ስለሚሰማቸው በአግባቡ እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል። ሆኖም እኔን ጨምሮ በርካታ የኃይማኖት አባቶች በምክክሩ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ አለመሆናችን አግባብ አይደለም። ይህ በቀጣይ ሊታሰብበት የሚገባው ነው።

አዲስ ዘመን – ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።

ሀጂ ጦሃ ሃሩን – እኔም አመሰግናለሁ።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You