ሰማዕታት ጎዳና ገና ጎህ ሲቀድ ነበር ህዝብ የሞላው ‹‹ ጀግና ታሪክ ይሰራል እንጂ አይኖርም››፣ ‹‹ጀግኖቻችን ቢገደሉም አንንበረከክም›› የሚሉና በርካታ መልዕክቶችን ያሰፈሩ ባነሮችን መፈክር የሚያሰሙ ወጣቶች ከዓይናቸው ጭስ ሲንቦገቦግ ይታያል። ከወዲያ እናቶች በመሪር ሀዘን ጎንበስ ቀና እያሉ ያነባሉ። ሌሎች በሀዘን ድንጋጤ እራሳቸውን ስተው በእቅፍ ወደ ዳር ይወሰዳሉ።
ከመቐለ ከተማና ከዙሪያዋ ከሚገኙ አካባቢዎች በሰልፍ ማልደው የወጡት ነዋሪዎች ፣የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ምስል የታተሙባቸው ቲሸርቶችን ለብሰው ወደ ‹‹ የሰማዕታት ሀውልት›› ያቀኑ ጀመር:: በስፍራው የጀግኖቹን አስክሬን ሲሰናበቱ በታላቅ ለቅሶና ቁጭት ነበር ።
አንድ ህዝብ ሆኖ ወንድም ወንድሙን በጥይት መግደሉ ከሁሉ በላይ ሁኔታውን አሳዛኝ ያደርገዋል በማለት የገለጸው የመቐለ ከተማ ነዋሪ ወጣት መዓዛ ሕሉፍ ነው ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱ ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎች ህይወታቸውን በግፍ እየተነጠቁ እንደሆነ በመግለጽ ለችግሩ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል። በተለይ ከዚህ ቀደም ታስረው የነበሩ ግለሰቦችን ከእስር ፈትቶ ይህን መሰል ድርጊት እንዲፈጽሙ ምክንያት መሆኑንም ተናግሯል። በቀጣይም ህዝቡ ልማቱን እንዳያቋርጥና ሰላሙን በአንድነት መጠበቅ እንዳለበት መልዕክቱን አስተላልፏል።
ታጋይ ወይንሸት ገብረኢየሱስ ፤ ሰላም ላመጡና ሀገርን ከነበረበት አስከፊ መንግሥታዊ አገዛዝ ነጻ ላወጡ ጀግኖች የማይመጥን እኩይ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።ድርጊቱ የተቀነባበረ ነው። ሆነ ተብሎ የሀገሪቱ መከላከያ እንዲበታተን ብሎም ህዝቡ ብሄር ከብሄር እንዲጋጭ የተደረገ ነው ሲሉ ኮንነውታል። በመሆኑም መንግሥት ጉዳዩን በአጽንኦት እንዲያይና በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ይህን እኩይ ሴራ የሚደግፉ ካሉ እራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን እንደተናገሩት ፤ ሁለቱ ጀግኖች በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ላለችበት ሰላምና የልማት ብርሀን ወጋገን ያሳዩ ነበሩ፡፡ እድሜያቸውን ሙሉ ለህዝብ ጥቅም ሰጥተው ለዚህ ከደረሱ በኋላ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መገደላቸው ልብን ይሰብራል፡፡
በአሁኑ ወቅት ትልቅ የፖለቲካ ችግር እየታየበት ያለ ምዕራፍ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡ ትምክህት ጫፍ የደረሰበት፣ በየቦታው የጎበዝ አለቃ የበዛበት፣ ህግ የማስከበር ክፍተቶች የሚታዩበት መሆኑንና ችግሩ በእንጭጩ ባለመቋጨቱም ዋጋ እያሥከፈለን ይገኛል፡፡ ችግር ሲኖር በጋራ መነጋገርን መፍትሄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ መንግሥትም ህዝብን ማድመጥ አለበት፡፡ የተከሰተው እኩይ ድርጊትም የመጨረሻው ሊሆን ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡
ሀዘኑ የመላው ኢትዮጵያ ቢሆንም በትግራይ ግን እንኳን ሰው መሬቱም እሳት ሆኗል ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ናቸው፡፡ በተለይም ማርከናቸው ‹‹ይቅርታ አይለመደንም ብለው›› በማርናቸው ሀይሎች መገደላቸው ድርጊቱን እጅጉን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ጀነራሎቹ ከሀገራቸው አልፈው የጎረቤት ሀገር ሰላምንም በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው አፈ ጉባኤዋ አስታውሰዋል፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በኋላቀር አመለካከት በመሆኑ ሁሉም በጋራ ሊታገለውና ሀገርን የመበታተን አጀንዳ ያነገቡ አካላት ሀይ ሊባሉ ይገባዋል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በትናንትነው ዕለት የጀነራል ሰዓረ መኮንንና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ግብዓተ መሬት በመቐለ ከተማ እንዳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን የትግል ጓዶቻቸው የተለያዩ ሀገራት ጀነራሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ፣ የሀይማኖት አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በማርሽ ባንድ ታጅቦ ተፈጽሟል፡፡
የጀነራሎቹ አስክሬን ከነበረበት የሰማዕታት ሀውልት የቀብር ስነስርዓቱ ወደሚፈጸምበት ቤተክርስቲያን ሲያመራ በዋና በዋና እና በመጋቢ መንገዶች ሁሉ ሲቃና የወጣቶች መፈክር ይሰማ ነበር፡፡ ከቀብር ስነስርዓቱ መልስም የሰማዕታቱን ቤተሰብ የማጽናናትና የሻማ ማብራት መርሐግብሮች ተካሂደዋል፡፡
በባህር ዳር ደግሞ የዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የአቶ ምግባሩ ከበደና አቶ እዘዝ ዋሴ ምስሎች በለቀስተኛው እጅ ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ አስክሬናቸው ወደ ስቴድየም በሚወሰድበት ጊዜ የአባቶች ቀረርቶና ሽለላ፣እናቶች ደግሞ በሙሾ ደረታቸውን እየደቁ ነበር ሀዘናቸውን የገለጹት፡፡
የኃይማኖት አባቶችም ህዝቡን በማጽናናት ኃይማኖታዊ ተልዕኮአቸውን ሲወጡ ነበር፡፡ የኃይማኖት አባቶች በማጽናናት መልዕክታቸውም ወንድም መድሙን በመግደል የሚገኝ ትርፍ እንደሌለና እንዲህ ያለው የግፍ ተግባር ተወግዶ አንድነት፣ ፍቅር፣ መደማመጥና መተሳሰብ ሊጎለብት እንደሚገባ አስተምረዋል፡፡ አባቶች የተፈጸመው ተግባር ከባድ ቢሆንም በፈተና መጽናት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
አስክሬኑ ስቴድየም የደረሰው የፖሊስ ማርሽ ቡድንም በማጀብ ነበር ፡፡አስክሬኑ በስፍራው ከደረሰ በኋላም በተለያዩ ሰዎች አመራሮቹ በህይወት ዘመናቸው ስለነበራቸው ሰብዕናና ታታሪነታቸው፣እንዲሁም ለሀገራቸው ስላበረከቱት አስተዋጽኦ በርካታ በሀዘን የተሞሉ ንግግሮች ተደምጠዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የሟቾቹ ልጆች ንግግር ስሜትን የሚይዝ ነበር፡፡
ፊቷ በእንባ እየታጠበ ስለአባቷ የተናገረችው የዶክተር አምባቸው መኮንን ልጅ መአዛ አምባቸው ‹‹ዛሬ የአባታቸው ልጅ መባል ቀረና የሟች ቤተሰብ ለመባል በቃን፡፡ አባቴ ቅን፣ ሰው አማኝ የዋህና ለሰው አሳቢ ነበር፡፡ ጓደኞቹንና የሥራ አጋሮቹን እንኳን ወንድምዓለም እያላቸው ነው የሚጠራቸው›› በማለት አባቷ የረገጠውን መሬትና የወጣበትን አካባቢ የማይረሳ ይልቁንም ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሲል ቤተሰቡን ትቶ ለህዝብ ጥቅም የደከመ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ልጆቹንም በእኩል የሚያይ፣ ሀገሩን የሚያስቀድም፣ ታታሪና ኢትዮጵያዊነትን በልጆቹ ልብ ውስጥ ያተመ አባት እንደሆነም ስለአባቷ ገልጻለች፡፡ አባቷ የጀመሩት ጉዞ ከህዝብና ከመንግሥት ጋር በመሆን ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኗንም ተናግራለች፡፡
የአቶ እዘዝ ዋሴ ልጅ ፍሬ እዘዝ በበኩሉ የተፈጸመው ድርጊት ለእርሱ አባት ብቻ ሳይሆን ለጠላትም የሚገባ እንዳልነበር ጠቅሶ፣ ለቤተሰቦቻቸው ጊዜ ሳይሰጡ ህዝባቸውን ያገለገሉ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ሞታቸውንም እንደ መስዋእት እንደሚያየው ተናግሯል፡፡
ስለአባቷ መልካምነት የተናገረችው የአቶ ምግባሩ ልጅ ስነ ምግባሩ ደግሞ ‹‹ አባቴ አንድም ቀን ለራሴ ሳይል ህዝብን ሲያገለግል ለመስዋዕትነት በቃ›› ስትል በመሪር ሀዘን ገልጻለች፡፡ የአባቷ ጉዞ በመሪር ሀዘን ቢቋጭም የተሰዋለት ዓላማ እንዲሳካ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቃለች፡፡
እንባ እየተናነቃቸው የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም፣ የሞቱት አመራሮች ሙሉ ጊዜያቸውን ለህዝብ የሰጡ በተለይም የህዝብ በደልን ለማስቀረት እና ብዙዎችም ከእስርቤት እንዲለቀቁ በማድረግ ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ብርቱ የነበሩ መሪዎችን ማጣትም እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተፈጸመባቸው ተግባር እነርሱን የማይመጥን አረመኔያዊ ተግባር ነው፡፡ ሁሉም ሊኮንነው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
መንግሥትም ከህዝብ ጋር በመሆን የታገሉለትን ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ይሰራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለውጡ የሚፈልገውን የህግ የበላይነት ለማስከበር፣ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን፣የኢኮኖሚ ማነቆዎችን ለመፍታት ይሰራል፡፡ ምክንያታዊነትንና አርቆ አሳቢነትን እንዲሁም የሌሎችን ሀሳብ አክብሮ መጓዝም ከመንግሥት ይጠበቃል ብለዋል። መስዋዕት ለሆኑ የአመራሮች ቤተሰቦችም መንግሥት ከጎናቸው በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2011
ፊዮሪ ተወልደ እና ወንድወሰን ሽመልስ