ወለፈንዲ

በተወለድኩ በአርባኛው ዓመት በሠላሳኛው ቀን ለዘመናት ካሸለብኩበት ሞት አከል እንቅልፍ የመጀመሪያውን መንቃት ነቃሁ:: በዚህች መከረኛ ምድር ላይ እንደ ሲራራ ነጋዴ አርባ ዘመን ስመላለስ ህሊና የሚባለውን ብልት ለምን ፋይዳ አውለው እንደነበር ባላውቅም ያን ጊዜ ግን የእናቱ ማህፀን ውስጥ ተኝቶ እንደሚቃዥ የስምንት ወር ፅንስ ረፍት አሳጥቶ የሚያንፈራግጠኝ አዲስ ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ አፀድ ገባ::

በሠው ሰራሽ ቁስ እና ሕይወት ተከብቤ በህልቁ መካከል ብቸኝነት ጥላውን ጣለብኝ:: ጭው ያለ በርሃ ውስጥ የተገኘሁ ብቸኛ እሾሃማ ተክል የሆንኩ ያህል ወፍ ዘራሽነት ተሰማኝ:: በምድሩ ላይ አንድ ስንኳን ለምለምና ርጥብ ሕይወት የሌለበት ዘላለማዊ ሀሩር:: ዙሪያ ገባየን ቃኘሁ፤ በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን ቢሄዱት የማያልቅ ምዕራፍ አልባ መንገድ እስከ አፅናፍ ተዘርግቷል:: ከተማው እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ የአሸዋ ባህር ይመስላል:: ሰማዩ ሩቅ ነው:: መሬቱ እንደ ጥንት ግሪክ የሙታን ሀገር ሄዲዝ ስምጥ ነው:: ዓይኔን ሩቅ በላክኩት ቁጥር በግራም ሆነ በቀኝ የሚታየኝ አድማሱ ላይ የተበተነ እንደ መስታወት የሚያጥበረብር የብርሃን ፍህም ብቻ ነው:: ተራሮችና ዛፎች፣ ወንዞች እና ሸለቆዎች፣ ወፎች እና ለምለም ሳሮች፣ ሀገሮች እና ድንበሮች፣ ውሾችም ሰዎችም የሉም:: የምኖራትን ሕይወት ይህን በመሰለ የመጀመሪያው ‹‹ለምን›› ጠየቅኩ::

ለምን ወደዚህች ምድር መጣሁ?

በተወለድኩ በአርባኛው አመት በስድሳኛው ቀን ይኸው የብቸኝነት ስሜት ተመልሶ ጎበኘኝ:: እንደ ዘበት ጥቅጥቅ ያለ የሠው ልጆች ጫካ ውስጥ ተጥያለሁ:: እንስሳትም ሆኑ እፅዋት፣ ወንዞችም ሆኑ ሸለቆዎች፣ ተራሮችም ሆኑ ሜዳዎች፣ ውሾችም ሰዎችም አሉ:: ነገር ግን ዙሪያየን ከቦኝ እንደሚራወጠው ፍጡር ስበር፣ ስፈጥን ቆየሁና አንድ ቦታ ላይ ደርሼ ድንገት ለዘመናት ካሸለበበት እንቅልፉ የነቃው ህሊናየ ወዴት እንደምሄድ ሲጠይቀኝ መልስ በማጣቴ እግሮቼ መሬት ላይ ተቸንክረው ቀሩ:: ወደ ፊትም ሆነ ወደ ኋላ መንቀሳቀስ አልሆንልህ አለኝ:: በቆምኩበት እያለፈኝ የሚወጣውን እና የሚወርደውን የሠው ጎርፍ ተመለከትኩ:: ይሄ ሁሉ ፍጡር ከየት መጣ? ወዴትስ ነው የሚሄደው? ይተያያል እንጂ አይተያይም፣ ይነጋገራል እንጂ አይነጋገርም፣ ይስቃል ግን አይስቅም፣ ቢያለቅስም አያለቅስም:: ብቻ ይቸኩላል – ይፈጥናል – ይጣደፋል:: ወዴት? ምን ለማግኘት?

ምንም!

ከየት እና ምን ሊፈይድ እንደመጣ፣ ወዴትስ እንደሚሄድ የማያውቅ የሠው ልጅ ሕይወት እዚያ ከመንገዱ ዳር በሰላም ተኝተው እንቅልፋቸውን ከሚለጠልጡት የጎዳና ውሾች ሕይወት በምን ተለይቶ ሠው ራሱን ክቡር ፍጡር ነኝ አለ? የሠው ነፍስ ከትንኝ እና ከአባጨጓሬ ነፍስ ትረዝማለች ወይስ ትወፍራለችን?

በተወለድኩ በአርባኛው ዓመት በመቶኛው ቀን ህሊናየን ያስጨነቀውን እና አብዝቶ የሚፈታተነውን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ቤተ-መቅደስ አመራሁ:: በዚያም ጥምጥማቸው እንደ ደመና የተቆለለ አንድ ዓይና ቄስ እድሜየን ሙሉ ስሰማው የኖርኩትና ያን ጊዜ ግን በተለየ ተመስጥኦና ምርምር ያዳመጥኩትን ትምህርት ሲሰጡ ተደመምኩ::

የሠው ልጅ ከሞተ በኋላ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ይነሳል:: መላዕክትም ከስጋው የተለየች ነፍሱን በመንፈሳዊ ውትድርና ደንብ አጅበው ወደ ፈጣሪ ያቀርቧታል:: በዚያም ከራሱ ፍላጎት እና እውቅና ውጭ በተጣለባት ምድር በኖረበት ዘመን ሁሉ የፈፀመው ታይቶ ፍርድ ይሰጠዋል:: ፍርዱም ወደ ዘላለማዊ የሲኦል እሳት፣ አልያም ዘላለማዊ ምስጋና ወደሚፈስበት መንግሥተ ሰማይ መጣል ነው::

የገሃነም እሳት ዘላለማዊ ቅጣት ይሁን፤

ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እያሉ ዘላለማዊ ምስጋና ሲሰው መኖርስ የማያልቅ ባርነት አይደለምን?

የሰማሁትን ትምህርት መልሼ እየጠየቅኩና እያሰላሰልኩ ወደ ማደሪያየ ገባሁ:: እውን ገነትም ሆነ ሲኦል የሠው ልጆች ዘላለማዊ ቤት ሊሆኑ የሚገባቸው ናቸው? ነገር ግን ፈጣሪ የነገሩትን የማይረሳ፣ የጠየቁትን የማይነሳ ደግ አምላክ ነውና እኔም የምጠይቀውን አይነሳኝም የሚል ርግጠኝነት ወደ ህሊናየ ገባ:: ያን ጊዜ የሰማይና የምድር ጌታ የሆነውን ደግ አምላክ የሚከተለውን ውለታ ጠየቅኩት…

ጌታ ሆይ ነፍሴን ባርካት:: ስትባርካት ግን ከገነትም ከሲኦልም መሆን ለኔ መልካም አይደለምና ከሞትኩ በኋላ እንደ እሪያ በዚያው እንድቀርና ትንሳኤን እንዳልቀምሳት ፍቀድልኝ::

በዚያው ምሽት የመንደሬ ሰዎች ከተሰቀልኩበት ገመድ ላይ አንስተው በታላቅ አጀብ ቀበሩኝ::

ነገር ግን ይህ እግዚዓብሄር የሚሉት አምላክ የለመኑትን የማይነሳ፣ የነገሩትን የማይረሳ ሳይሆን ቀርቶ እነሆኝ የትንሳኤን ብርሃን አይቼ በመንግሥተ-ሰማይ እገኛለሁ::

በዚህ ወንዙ ወተት ያፈሳል፣ ገራም እንስሳትም፣ ክፉ አውሬዎችም ከሠው ልጆች ጋር ባንድነት እና በወዳጅነት ይኖራሉ፣ ሠዎች አይጋቡም አይዋለዱም፣ የገነትን አፀድ አጥረው የበቀሉት እፅዋትና ፅጌያት መልካም ፍሬን ያፈራሉ:: ሽቶ መዓዛን ይረጫሉ:: ፅርሃ አርያም ሰርክ በምስጋና ጠበል ትታጠባለች:: በዚህ ለህልውና ሲባል መጠፋፋት እና መገዳደል የለም:: ተኩላ እና በግ አብረው የጠዋት ፀሃይ ይሞቃሉ፣ አንበሳ እና ሚዳቋ ዘወትር የማይተጣጡ ጥብቅ ወዳጅ ናቸው:: ጅብ ከአህያ ጋር ቆሞ በምስጋና ይዘምራል:: የሠው ልጆች ህፃናት የአንበሶችን ጋማ ያበጥራሉ፣ የአናብርትን ጥፍር ይቆርጣሉ፣ በመላዕክት አክናፍ ላይ ይፈነጫሉ:: በዚህ እፅዋት የራሳቸው ሕይወት አላቸው እንጂ ለሠው ልጆችም ሆነ ለእንስሳት ደስታ እና ህልውና ሲባል መስዋዕት አይሆኑም:: ወይን እና ትርንጎዎች አይቀጠፉም፣ አደይ አበባ ከስሯ ተነቅላ የልጆች መጫወቻ አትሆንም:: በዚህ ለታቦት ተብሎ የሚቆረጥ የግራር ዘር የለም:: የዋንዛ እና የፅድ ዛፎች የገነት ቅፅር ጠባቂ ዘቦች እንጂ አልጋዎች እና ዱካዎች አይደሉም:: ዋርካዎች እና ዝግባዎች የጌታ መንበር መቀመጫዎች ናቸው::

ነገር ግን ቀን አይመሽም፣ ሌት አይነጋም:: በልግ አይበልግም፣ ክረምትም በዝናም አይረሰርስም፣ ፀሃይ እና ጨረቃ አይፈራረቁም፣ የሠው ልጅ በዚህም የሚደክምለት፣ የሚወጣ የሚወርድለት አንዳች ዓላማ የለውም:: ሕይወት በገነት ሰርክ ውሎ የማደር፤ ዘላለማዊ የምስጋና ድግግሞሽ ነው:: ውሃን ከመንፈስ ባህር እየቀዳ፣ ምግብን ከመለኮት ቃል እየሰዋ ብቻ ይኖራል:: በዚህ የተገኙ ፍጡራን ሁሉ እድሜያቸው ህልቆ መሳፍርት የለውም:: ርጉዝ ደመናዎች በአየሩ ላይ ሲንሳፈፉ አይታዩም:: የቀን ሐሩርና የሌሊት ቁር አይፈራረቁም:: ፈጣሪ ብቻ በዙፋኑ ላይ ነጭ የብርሃን ሸማ ተጎናፅፎ ያለ ማቋረጥ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እየተባለ የሚሰዋለትን ዘላለማዊ ምስጋና በለበጣ እየፈገገ ያዳምጣል::

የሆነው ሁሉ ሆኖ ከሁሉም በላይ በዚህ አንድ አስከፊ ሕግ አለ:: የሠው ልጅ ሕይወት ብትሰለቸው፣ ሰርክ ዕለት ወተት የሚያፈሰው የገነት ወንዝ ሬት ሆኖ ቢመረግገው፣ የእፅዋቱ እና ፅጌያቱ ጠረን ቢሰነፍጠው፣ የምስጋና ዘላለማዊ ድግግሞሽ አቅሉን አስቶ ቢያሳብደው፣ በዚህ የመፈጠሩን አንድ ምክንያት እና የሚኖርበትን ዓላማ ፈልጎ ቢያጣ፣ ምድራዊ ሕይወቱን በገዛ ጉልበትና ሥልጣኑ አልያም በተፈጥሮ ፍቃድ እንደሚደመድም ሁሉ ሰማያዊውን ወለፈንዲ ዓለም አልፎ መሄድ ቢያሰኘው ራሱን ሰቅሎ የመግደል ፍቃድ የለውም::

ሞትን ፈልጌ አጣሁት!

 እዩኤል ወርቁ

 አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2016 ዓ.ም

Recommended For You