የምልክት ቋንቋ መስማት ከተሳናቸው ባለፈ

የተለያዩ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም ተብለው በተደጋጋሚ ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። የጉዳት ዓይነታቸውን ያማከለ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በስፋት ባለመኖራቸው እንደዜጋ ማግኘት ያለባቸውን ግልጋሎት ሳያገኙ ይቀራሉ። በዚህ ምክንያት ከማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ከሌሎች ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ተሳትፏቸው አናሳ ሆኗል።

የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ችግራቸውን ሊያቃልል የሚችል እና የተቋሙን ጥረት በዚሁ ይቀጥል የሚያስብለውን ሥራ ከሰሞኑ ሠርቷል። አገልግሎቱ ‹‹ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት›› ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን ለአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞቹ መሠረታዊ የምልክት ቋንቋ ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል።

የአገልግሎቱ የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሳሁን እንደሚገልጹት፤ ተቋሙ መስማት የተሳናቸውን ጨምሮ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች አካታች የሆነ አገልግሎት በስፋት እየሰጠ ነው ለማለት ያዳግታል። ከዚህ ቀደም ለዓይነ ሥውራን ብቻ የተዘጋጀ ቦታ የነበረ ቢሆንም አገልግሎቱ አካታች ነው ከመባል ይልቅ አግላይነት የታየበት በመሆኑ ሊታረም ችሏል። በአሁኑ ወቅት አካታች የሆኑ ሥራዎችን ለመሥራት ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። ተቋሙ አሁን የጀመረው መልካም ተግባር እንደ ተቋም ለብዙ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ለመድረስ ዕድል የሚሠጥ ነው። ለሰልጣኞችም ተጨማሪ እውቀት እና የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል።

በተለያዩ ተቋማት ላይ በምልክት ቋንቋ አገልግሎት መስጠት ቢቻል ጥቅሙ ብዙ ነው። ለአብነት የሕክምና ተቋማት እና መሰል ተቋማት የግድ የምልክት ቋንቋ የሚችሉ ባለሙያዎች ያስፈልጋቸዋልና፤ እንዲህ ያለው ተስፋ ሰጪ ሥራ ቀጣይነት ቢኖረው ብዙ ችግሮችን ማቅለል ይቻላል። ሌሎች ተቋማትም እንዲህ ባለው ሥራ በመሳተፍ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ ቢደረግ የሚያበረታታ ነው።

የብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀገሬ መኮንን በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ተቋሙ መሠረታዊ የምልክት ቋንቋ ትምህርትን ለሠራተኞቹ በመስጠት ለሌሎች ተቋማት አርዓያ የሚሆን ተግባር አከናውኗል። ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በተገቢው መንገድ የሚያገለግልና በምልክት ቋንቋ በሚገባ ማስረዳት እና መግባባት የሚችል ሠራተኛ ያስፈልጋቸዋል።

አገልግሎቱ ላለፉት ሰማንያ አንድ ዓመታት ንባብ እንዲስፋፋ እየተጋ ያለ ተቋም ነው። አገልግሎቱን ለመስጠት ግን ዋናው ነገር መግባባት ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ በየጊዜው የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በተለይም ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ብዙ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በቀጣይም ተቋሙ ከብሔራዊ ቴአትር ሠራተኞች ጋር አብሮ በመሥራት ቴአትሮችን በምልክት ቋንቋ እንዲተረጎሙ አድርጎ ለዕይታ እንዲበቃ አስቻይ ሁኔታዎች ይመቻቻል።

የ‹‹ኢትዮጵያን ሴንተር ፎር ዲስኤቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ECDD) ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በዓለም ጤና ድርጅት እና በዓለም ባንክ እ.ኤ.አ በ2011 በተጠናው ጥናት መሠረት በዓለም አቀፍ ደረጃ 15 በመቶ ወይም አንድ ቢሊዮን ሰዎች፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው እንደሆኑ ጥናቶቹ ይፋ አድርገዋል። እነዚህ አካል ጉዳተኞች አብዛኞቹ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ፣በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና በሌሎች ችግሮች የተገደቡ ናቸው። ይባስ ብሎም ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች በመሥሪያ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ይሁኑ እንጂ ሥራ የሌላቸው በመሆኑ የችግሩን አሳሳቢነት ያሳያል።

መንግሥት እነዚህን የኅብረተሰቡ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ አሉታዊ አመለካከቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። አካል ጉዳተኞች ልክ እንደ ጉዳት አልባ ዜጋ በልማት እና በሌሎች ፕሮግራሞች ተካታች እንዲሆኑ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል።

ከዚህ ባለፈ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ ፖሊሲዎች፣ አስቻይ ሕጎች እና የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ያሉትን ፖሊሲዎችና ሕጎች ተግባራዊነታቸው እንዲረጋገጥ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቀማት እና ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ።

አካል ጉዳተኞች የማኅበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት የተጀመረው መልካም ጅማሮ በፍትህ ተቋማት፣ በህክምናው እንዲሁም እንደ ማኅበረሰብ እያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ የመግባቢያ ምልክቶች በተገኘው አጋጣሚ መማር እና ልዩ ፍላጎት ካላቸው ዜጎች ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ተግባቦት ላይ አብሮ መሥራት ያስፈልጋል ።

የአገልግሎቱ ሠራተኞች የምልክት ቋንቋ ሰልጥነዋል። ባገኙት እውቀት እና ክህሎት አካታች የሆነ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችልና ባለሙያዎቹ መስማት ከተሳናቸው ተጠቃሚዎች ጋር እንዲግባቡ ብሎም መረጃ እንዲለዋወጡ ያስችላቸዋል። እንዲህ ያለውን በጎ ጅምር ሌሎች ተቋማት እንደ አርአያ ወይም ምሳሌ በማድረግ ለብዙዎች መድረስ እንዲችሉ ያግዛቸዋል።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You