«ወለጋ ላይ የሚመረተው ምርት ለሀገርም የሚበቃ ነው» – የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ

ኢትዮጵያ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ አየር ጸባይና ለም አፈር ባለቤት ነች። በዚህም በአሁኑ ወቅት 120 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝቧን የምትመግበው ከግብርና ከሚገኝ ምርት ነው። ግብርና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ መሠረት ነው። ከምግብ አቅራቦት ባሻገር ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል። እንደሀገርም የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው።

በግብርና ምርታማ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ የኦሮሚያ ክልል ሲሆን ክልሉ ያለውን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ቁጥር በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሚሆኑ የግብርና ውጤቶችን በማምረት ሀገርንም፤ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልል ክልሉ እያደረገ ያለው ግብርና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የተገኙትስ ውጤቶች እንዴት ይገለጻሉ? ሲል ከኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ከአቶ ጌቱ ገመቹ ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን – የኦሮሚያ ክልል ትኩረት አድርጎ እየሠራባቸው ያሉትን የግብርና ዘርፎች ቢጠቅሱልን?

አቶ ጌቱ ገመቹ- በአጠቃላይ እንደ አሮሚያ ግብርና ቢሮ ከግብርና ሥራዎቻችን አንዱና ትልቁን አድርገን በትኩረት እየሠራንበት ያለው በጋ ላይ የተፋሰስ ልማት፣ ክረምት ላይ ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራው ሥራ ላይ ነው። ይህንኑ ለማሳካትም በጋ ላይ አርሶአደሮቻችን እና አርብቶ አደሮቻችን ትልቅ ትንሸ ሳይቀር በነቂስ ወጥቶ የመሬት ዝግጅት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። ባለፉትዓ በአከባባ ጥበቃ ሥራዎችና በአረንጓዴ ዐሻራ በርካታ ትሩፋቶች ተገኝተዋል።

በዚህ ረገድ የሀረማያ ሀይቅ ብዙ ጊዜ በምሳሌነት ይጠቀሳል። ጠፍቶ የነበረው የሀረማያ ሀይቅ አርሶአደሮቻችን በጋ ላይ በመንከባከብ እና በመሥራት የአረንጓዴ ዐሻራውን ሥራም ጨምረውበት ይሠሩ ስለነበረ ሀይቁ እንደገና ተመልሷል። በየቦታውም ኩሬዎች የሚመነጩበት፣ በየቦታው ትናንሽ የውሃ አውታሮች የተገኙበት፣ አርሶአደሮቻችን ደግሞ ከዚያ መጠቀም የጀመሩበት፣ እዛው ከብቶቻቸውን እያደለቡ፣ የወተት ላሞችን እየተንከባከቡ፣ እዛው ንብ እያነቡ ማር የሚያገኙበት እና ትልቅ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በተጨማሪም በጋ ላይ የምንሸራው የስንዴ ልማት ከላይ የተፋሰስ ልማቱን (የውሃ ሼዱን) ስለምንንከባከብ በቂ ውሃ ክምችት እንድናገኝ አድርጎናል። በአጠቃላይ በጋ ላይ የምንሠራቸው ሥራዎች በዚህ ሀገር ላይ በጣም ትልቅ ልዩነት እያመጣ ይገኛል። ይህም በጋ ላይ ብቻ ሳይሆን በአረንጓዴ ዐሻራው ላይም ርብርብ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር እኒሺየቲቭ አድርገው ካስቀመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ በደስታ ይሄንን ሥራ በነቂስ ወጥቶ እየሠራው ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልልም በየዓመቱ በደን የሚሸፈነው የመሬት መጠን፣ የምናዘጋጀው ችግኝ በተመሳሳይ እየሰፋ መጥቷል። ለምሳሌ የዘንድሮው ብቻ ሲታይ ወደ አምሰት ነጥብ አምስት (5.5) ቢሊዮን ችግኝ ነው ለመትከል አቅደን እየሠራን ነው። በእቅዳችን መሠረትም አምስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ በየቦታው ዝግጁ አድርገናል።

ከዚያም በላይ ዘንድሮውን ለሰው ምግብነት የሚውሉ ችግኞች ላይ ትኩረት አድገናል። ለምግብነት የሚውሉ 500 ሚሊዮን ችግኝ ለማዘጋጀት አቅደን ሠርተን እስካሁን ወደ 490 ሚሊዮን ችግኞችን አዘጋጅተናል። በአጠቃላይም አረንጓዴ ዐሻራው ከምንተክላቸው ችግኝ 11 በመቶውን ለሰው ልጅ ምግብነት የሚሆነውን እንተክላለን ብለን አቅደን እየሠራን ነው ያለነው።

እንደአጠቃላም አረንጓዴ ዐሻራን በተመለከተ ዘንድሮ ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ላይ እንተክላለን ብለን ነው አስበን እየተንቀሳቀስን ያለነው። እስካሁን ድረስ ከ680 ሺህ ሄክታር በላይ ፖሊጎኑ ታስሮለት በጂፒኤስ ጂአይኤስ ተወስዶ የት ምን መተከል እንዳለበት ተለይቷል። ከወዲሁም በአንድ ቀን ተከላ ላይ ማን ምን አይነት ችግኝ የት ቦታ ላይ ይተከላል፣ ምን ያህል ሕዝብ እዛ ቦታ ላይ ይሳተፋል፣ የሚለውን ጭምር ለይተን ተቀምጠናል።

እንደ ኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ የራሳችንን ሪከርድ እንዲሁም የሌሎች ክልሎችንም ሪከርድ እንሰብራለን ብለን እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተናል። ለዚህ ደግሞ የኛ አርሶአደሮች እና አርብቶ ለችግኝ ትልቅ ቦታ የሚሰጡ በመሆኑ ያሰብነውን እናሳካለን በለን እናምናለን። በምንሠራባቸው ሥራዎች ልምድ እያገኘንባቸው የመጣንባቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ የሞሪንጋ ወይም በተለምዶ ሽፈራው የሚባለው ተክል በተለይ በደቡብ ክልል አካባቢ በስፋት ይታወቃል። ለምግብነት እና ለመድሃኒትነትን ፍቱንነት እንዳለው የሚመሰከርለት ተክል አሁን አረንጓዴ ዐሻራው አካል ነው።

የዘንድሮ ክረምትም ዝናቡ ጥሩ ጊዜ የጀመረበት ነው። የሚዎትሮሎጂ ትንበያ እንደሚያሳየው የዝናብ እጥረት እንደሌለ ገልጸዋል። ስለዚህም እንደ ክልልም ሆነ እንደሀገር ውጤት እናመጣለን ብለን እናስባለን።

በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት ያደረግነው የፍራፍሬ ልማት ነው። በክልሉ ከግብርና ሥራዎች መካከል በትኩረት እየተሠራባቸው ያለው አንዱ ዋናው የፍራፍሬ ልማት ነው ። ከፍራፍሬዎች ደግሞ በጣዕም የተሻሉ እና ወደ ውጭ ኤክስፖርት ሊደረጉ የሚችሉ ፍራፍሬዎች ላይ ነው ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው።

ከዚህ በፊት እንደሚታወቀው እህልን በክላስተር ነው እየሠራንበት ያለነው። እህልን በክላስተር እንደምሠራው ሁሉ ፍራፍሬ ላይም በክላስተር አድርገን መሥራት እንዳለብን አስበን እየተንቀሳቀስን ነው። ክልሉ ላይ ብዙ አይነት ፍራፍሬዎችን ማልማት ይቻላል። ነገር ግን ለአርሶአደሮቻችን ገቢ ሊያመጡ የሚችሉ፣ የምግብ ይዘታቸው ጥሩ የሆነ፣ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኙ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን። ከዚህ ውስጥ አንዱ አቮካዶ ነው።

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች አቮካዶን መትከል እና ማምረት ይቻላል። አቮካዶ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚደርስ የፍራፍሬ ተክል ስለሆነ ሳይንሱን ተከትለን የምንሠራ ከሆነ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንችላለን። ይህንኑ መሠረት አድርገንም በክላስተር አድርገን ሰፊ ሥራዎችን እየሠራን ነው ያለነው።

በየዓመቱ በአቮካዶ የሚሸፈነው የመሬት መጠን ሆነ ከአቮካዶ የምናገኘው የውጭ ምንዛሪም በየዓመቱ እየጨመረ መጥቷል። በዘንድሮ 2016 ዓመት በክረምት ችግኝ መትከያ ጊዜ 10 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ የአቫካዶ ችግኝ አዘጋጅተናል። በዚህ ዓመት 30 ሺህ ሄክታር መሬት በአቮካዶ እንሸፍናለን ብለን አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው። በብዛት እየተከልን ያለነው የሀገር ውስጡን አቮካዶ ሳይሆን የተዳቀለውን አቮካዶ ነው ።

 

ሃስ ቫራይቲ (የሀገር ውስጥና የውጭ ዝርያው የተዳቀለበት) አቮካዶ በውጭው ገበያ ጭምር ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ነው። ይሄንን በየዓመቱ ወደ አረብ ሀገር እና አውሮፓ ኤክስፖርት እያደረግን ነው ያለነው። ይሄንን በስፋት አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን – በክልሉ በሩዝ ምርት ላይ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ጌቱ ገመቹ -ሩዝ ኦሮሚያ ላይ ከዚህ በፊት ብዙም አይታወቅም ነበር። ሰብሉ ከኦሮሚያ ይልቅ በአማራ ክልል ፎገራ በሚባለው አካባቢ የበለጠ ይታወቃል። አምና ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ሩዝ ለማልማት አቅደን አንድ ሚሊየኑን ሄክታር በሩዝ አለማንና ወደ 32 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ ልናገኝ ችለናል።

ሩዝ ማምረት ቀላል አይደለም። የተለያዩ ማሽነሪዎች ይፈልጋል። ይህንንም እውን ለማድረግ ወጣቶችን አደራጅተን እንደዚሁም ደግሞ ባለሀብቶችን በዚህ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ውጤት ለማግኘት ተሞክሯል። አሁን ቄለም ወለጋ ላይ ያያችሁት አይነት በሶስት ፤ በሶስት ኪሎ ታሽጎ ለገበያ እየቀረበ ያለው የዚህ ውጤት ነው።

ክልል ሩዝ የማምረት አቅም አለው። ይሄንን አቅም ለመጠቀም በርካታ ርብርቦሽ እያደረግን ነው። በተለይ በዚህ ረገድ ምዕራብ ኦሮሚያ በጣም ትልቅ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው ያለው። በተለይ በመኸር ወቅት ላይ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው ያሉት። ይሄንን ርብርብ በየቦታው ያለው ህብረተሰብ እና ባለሙያ እየደገፈ ከሄደ ብልፅግና ብለን ያስቀመጥነውን ርዕይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን እንደምናደርግ እርግጠኛ ነኝ።

አዲስ ዘመን – በክልሉ ቡና ረገድ ያለው ውጤት ምን ይመስላል

አቶ ጌቱ ገመቹ – እንደ ክልል ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቡና ልማት ነው። የቡና ልማት የአሲዳማ አፈርን የሚቋቋም ስለሆነ እዛ ላይ ሰፊ ሥራ በኢኒሽየቲቭ የሚሠራበት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የቡና ምርታችንን ለማስፋተ ብለን በትኩረት እየተንቀሳቀስን ነው።

እንደ ክልል ቡና ምርቱ ብቻ ሳይሆን ጥራቱ ም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታን እናያለን። በዘንድሮው ዓመት 11 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ያህል ኩንታል ማምረት ችለናል። ይህም ትልቅ እርካታ ነው።

በሌላ በኩል በጥራት ላይ ትኩረት አድርገን በመሥራታችን ሰፊ ውጤት እያገኘን ነው። ከዚህ በፊት ወደ ውጭ የሚላከው ጥራቱን ያልጠበቀ ቡና ነበር። ብዙ ጊዜም ውድቅ ሆኖ ይመለስ ነበር። ዘንድሮ ግን የቡና ጥራት በመጨመሩ ወደ ውጭ የምንልከው የቡና መጠናችንም ጨምሯል። በውጭ ሀገር ያለው ተቀባይነትም በዚያው መጠን ጨምሯል።

የኛ ቡና ደን አካባቢ ላይ እየተመረተ የሚገኝ ቡና ስለሆነ በኦርጋኒክ ቡናነቱ ነው የሚታወቀው። ከዚህ የተነሳም ቡናው በጣም ተፈላጊ ነው። እኛ ደግሞ ኦርጋኒክነቱን በማስቀጠል ለመሥራት ሰፋፊ ሥራዎችን እየሠራን ነው ያለነው።

አንዱና ዋናውም ችግኝ ጣቢያዎች ለይ የሚሠሩትን ሥራዎች በስፋት መሥራት ነው። ከኬሚካል ንክኪ ነፃ እንዲሆን ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው። ዘንድሮም ወደ ሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ በችግኝ ጣቢያዎች ላይ ለማፍላት አቅደን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት ችለናል። ይህም ለዘንድሮው ክረምት አረንጓዴ ዐሻራ ለተከላ ይደርሳል።

ላሎ ቅሌ ወረዳ ላይ እንደሚታየውም ሰፊ ቦታ የሸፈነ በርካታ የነርሰሪ ሳይቶች አሉ። ይህም ለዚህ ክረምት የሚደርስ ነው። ይሄንን ስናደርግ በቡና የሚሸፈነውን የመሬት መጠንንም በዚያው ልክ እንጨምራለን ማለት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የምርቱንም መጠን በዚያው ልክ እንጨምራለን ማለት ነው። ስለዚህ በሚመጣው ዓመት ላይ ከ12 ቢሊዮን ቶን በላይ ቡና ለማምረት አቅደናል። በዚህም ለሀገር ውስጥም ለውጭ ገበያም በበቂ መጠን እናቀርባለን ማለት ነው።

አዲስ ዘመን ፡- በክልሉ በአሲድ የተጠቃ አፈርን ለማከምና ምርታማነት ለመጨመር የሚደረገው ጥረት ምን ይመስላል?

አቶ ጌቱ ገመቹ ፡-የአሲዳማ አፈር መስፋፋት አንዱ የክልላችን ችግር ነው። በምዕራብ ወለጋ ችግሩ የባሰ ነው። በምስራቅ ወለጋም ቢሆን ችግሩ አለ። በምዕራብ ወለጋ በተለየ መነሲቡ ወረዳ በአሲድ ክፉኛ ተጠቅቷል።አሲድ ብቻ ሳይሆን ምስጥም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል። እነዚህ ሁለት ነገሮች የመሬትን የምርታማነት መጠን እየቀነሱት መጥተዋል ። አንዳንድ ቦታ ላይ ሙሉ ለሙሉ ምርት የማይሰጥ ቦታ አለ። ቀይ አፈር ሆኖ ሳር እንኳን ማብቀል ያልቻለ ቦታ አጋጥሞናል ።

ስለዚህም የአፈርንም ምርታማነት ማሳደግ ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አይደለም። በተለይ ምዕራብ ወለጋ ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው። ይሄ አካባቢ የቡና ምርትም የሚገኝበት በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን መሥራት አለብን። አንዳንድ ተክሎች አሲዳማነትን የመቋቋም ባህሪ ስላላቸው እነሱን በስፋት የመትከል እቅድ አለን። አሲዳማነት የመቋቋም ባህሪ ካላቸው ተክሎች አንዱ ቡና ነው። ሻይ የአሲዳማነት ባህሪን የመቋቋም ባህሪ አለው፣ አቦካዶም እንዲሁ አቅም ያለው ተክል ነው።

በአሲዳማ አፈር አካባቢ የተተከለው አቮካዶ የተራቆተውን አፈር በአረንጓዴ ቀይሮ አንድ ሄክታር ከማይሞላ ቦታ ሁሉ ወደ 60 ኩንታል ያህል ወደ ውጭ መላከ የተቻለበት አንዱ ማሳያ ነው። የዚህ አካባቢ አፈርን ለማከም ከተፈለገ አቮካዶ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል።

እንደ ኦሮሚያ ክልልም ዓይናችንን ወደ ዚህ ማዞር አለብን ብለን ነው የያዝነው። አሁን ባየነውም በፊትም ባለን መረጃ መሠረት እዚህ አካባቢ ላይ ሰፊ ሥራ መስራት የምንችለው አቮካዶ ላይ ነው። አቮካዶ ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥተን ከሠራን ይሄ መሬት ይታከማል። ይህም ሌላ መረጃ ማምጣት ሳያስፈልግ በተግባር የታየው ነው።

ስለሆነም አርሶ አደር ጋር የአቮካዶ ችግኝ በሰፊው ካቀረብንለት አርሶአደሩም ያንን ተጠቅሞ መሬቱን ያክማል ማለት ነው። አርሶ አደሩ ባዶ በነበረው መሬት ላይ አቮካዶ ከተከለ ከሶስት ዓመት በኋላ የአቮካዶ ምርትን ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ መላክ ይችላል ማለት ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ደግሞ አርሶ አደሩ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ የሚገባበትን መንገድ እያመቻቸን እንሄዳለን። በዚህም ላይ የተሠማሩ ባለሀብቶች በመንግሥት በኩል ማበረታቻ እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- በጸጥታ ችግር ውስጥ የነበሩት የምዕራብ ወለጋ ዞኖች አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

አቶ ጌቱ ገመቹ ፡- የምዕራብ ወለጋ ዞን ወዳዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ከመልማት ተከልክለው የቆዩ ናቸው። የፌዴራልና የክልል መንግሥት በተሰጠ አቅጣጫ መሠረት በተለይ የግብርና ቢሮ ከምዕራብ ወለጋ ዞን ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ይገኛል ። አቮካዶ እና ሙዝ ወደ ውጭ መላክ የተጀመረ በመሆኑ በወረዳዎቹ የሚደረገው የልማት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት አለን። የተለያዩ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም ከተሟሉ ምርቶቹን ተከትለው ወደ አካባቢው ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን።

ባሳለፍነው ስድስት ቀናት ወለጋ ላይ ያለውን የልማት አቅም ያየንበት ሁኔታ ነው ያለው። ይሄ አካባቢ ትልቅ የልማት አቅም ያለው አካባቢ መሆኑን የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ ሁላችንም በአካል በመገኘት ያየነው ነው። እዚህ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ለልማት ትልቅ ተነሳሽነት ያለው ህብረተሰብ እና ልማት ላይ እየተሳተፈ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በተለይም በዚህ በመኸር ወቅት አርሶ አደሩ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ታዝበናል።

አጠቃላይ በወለጋ አካባቢ ላይ በተደረገው የሥራ ጉብኝት ህብረተሰባችን በሁሉም ቦታዎች ላይ ያለውን የልማት ጥማት ተመልክተናል። የልማት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በትክክልም ሥራ ውስጥ ገብቶ እየሠራ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሕዝቡ ተነቃቅቶ ወደ ልማት ወደ ሥራ ገብቷል ። በሁሉም ዞኖች አመርቂ ሥራዎች እየታዩ ነው። ለአብነትም የታጣቂዎች መፈንጫ የነበረው የቄለም ወለጋ ዞን የታየው ልማት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው።

በሌማት ትሩፋቱም ጥሩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት። የቡና ተከላ ጅማሬውም የሚያስደስት ነው፤ ለወደፊቱም የህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል። በአጠቃላይ ወለጋ በልማት ላይ ነው ያለው፤ ወለጋ ልማትን እየተጠማ ሕዝብ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተአምራዊ ለውጥ እንደሚያመጣ እርግጠኛ ነኝ። በተለይም በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር አካባቢውን ከደገፈው ለሌሎችም ዞኖች የሚተርፍ አቅም እንዳለው ተገንዝበናል።

ወለጋ ላይ ያለውን የአየር ንብረት ከተጠቀምንበት እና የግብርና ሥራውን በሚገባ ከደገፍነው ወለጋ ላይ የሚመረተው ምርት ብቻ ለሀገር በቂ ነው። ይህም ለንግግር ብቻ ሳይሆን በአካል ማንኛውም ሰው መጥቶ ሊያረጋግጠው የሚችለው ነው። ወለጋ ላይ አንድ ነገር ተተክሎ ወዲያው የሚበቅልበት፣ የሚያደግበት አፈር ነው ያለው። በአንድ በኩል ከዝናብ መብዛት ጋር ተያይዞ አሲዳማነት ቢያጠቃቸውም በሌላ በኩል ደግሞ በጣም ለም አፈር እንዳለ በዚህ ዙሪያ ላይ ለመመልከት ችለናል።።

ስለዚህም ወለጋ ውጤታማ እንዲሆን ሌሎች ሴክተሮችም ዓይናቸውን ከዚህ አካባቢ መንቀል የለባቸውም። ሕዝቡም ወደ ልማተ እየገባ ስለሆነ ሕዝብ የበለጠ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውጤት ይመጣል፤ እንደሀገርም ተጠቃሚ እንሆናለን።

አዲስ ዘመን -ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ

አቶ ጌቱ ገመቹ – እኔም አመሰግናለሁ

በሀይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You