የኮከቧ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ውጥን

የአትሌቲክሱ ዓለም ከዋክብት የውድድሮችም ድምቀት ከሆኑ የዘመኑ ድንቅ አትሌቶች መካከል አንዷ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ ናት፡፡ በወጣትነት ዕድሜዋ በርካታ ስኬቶችን የተቀዳጀችው ወጣት ኮከብ አትሌት የአንጋፋዎቹን ፈር ከመከተል አልፋ ለተተኪዎች መንገድ በመክፈት ምግባረ ምስጉን ናት፡፡ እየተቀዛቀዘ ባለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስኬት ውስጥ እየበራች ተስፋነቷን ስታስመሰክርም ቆይታለች፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ በከበሩበት ታላቅ የውድድር መድረክ ሌላ ክብርን ለመቀዳጀት እየተጋች ትገኛለች፡፡

ከትግራይ ክልል የተገኘችው ጉዳፍ አትሌቲክስን የተቀላቀለችው ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ እለኸኛዋና ጠንካራዋ አትሌት ሀገሯን የወከለችው ገና በልጅነቷ ሲሆን፤ እአአ በ2014 በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ16 ዓመቷ በ1ሺ 500 ሜትር ርቀት በመሳተፍ 9ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡ በዚያው ዓመት አሜሪካ ዩጂን ላይ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናም በድጋሚ ኢትዮጵያን ወክላ ከእድሜ እኩዮቿ ጋር በመፎካከር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላለች፡፡

ከሁለት ዓመት በኋላ ዳግም በወጣቶች ቻምፒዮና ላይ ስትሳተፍም በሀገሯ ልጅ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ተይዞ የቆየውን ፈጣን ሰዓት በ10 ሰከንዶች በማሻሻል በዚህ የእድሜ ገደብ የ1ሺ500ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ ይህም በድጋሚ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ሲያሳጫት ፓርትላንድ ላይ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ለሀገሯ የነሃስ ሜዳሊያን አስገኝታለች፡፡ ተስፈኛዋ አትሌት 20 ዓመት ባይሞላትም የነበረችበት አቋም በዚያው ዓመት በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ በ800 ሜትር ርቀት ተሳታፊ እንድትሆንም አስችሏታል፡፡ ቀጣዩ የለንደን ዓለም ቻምፒዮናም አትሌቷን በድጋሚ ሀገሯን እንድትወክል ኃላፊነት ያሰጣት ቢሆንም ውጤታማ ግን አልነበረችም፡፡

ጠንካራ ስራ መታወቂያዋ የሆነው ጉዳፍ በድጋሚ ወደ አቋሟ ተመልሳ በዳይመንድ ሊግ ውጤታማነቷን በማስመስከር፤ በኳታሩ የዓለም ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝርዝር ውስጥ ልትካተት ችላለች፡፡ በቻምፒዮናው ያጠለቀችው ሜዳሊያ ደግሞ ለቶኪዮው ኦሊምፒክ እንድትመረጥ አስችሏታል፡፡ ጉዳፍ በዚህ ኦሊምፒክ ከምትታወቅበት ርቀት ውጪ በ5ሺ ሜትር የተካፈለች ሲሆን፤ በተከታታይ ዓመት ለሀገሯ ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች፡፡ በባለቤቷ ህሉፍ ይህደጎ አሰልጣኝነት ስኬታማ ዓመትን ያሳለፈች ሲሆን፤ ሌቪን ላይ በ1ሺ 500 ሜትር የዓለምን ክብረወሰን በመጨበጥ ጭምር የአትሌቲክስ ስፖርት ፈርጥ መሆኗን አሳይታለች፡፡

እአአ 2022 ደግሞ ኢትዮጵያን ወክላ በዓለም እና በቤት ውስጥ ቻምፒዮና እና 2 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችበት ነበር፡፡ ሀገር ወዳዷ ጉዳፍ በወቅቱ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከቤተሰቦቿ የመራራቅ አጋጣሚ ሳትረታ ኢትዮጵያን በማስቀደም ለባንዲራ ሲታገሉ ከነበሩት መካከል አንዷ ናት፡፡ በዚህ ባህሪዋ ለበርካታ ወጣት አትሌቶች ተምሳሌት የምትሆነው ጉዳፍ ያለፈውን ዓመት በድንቅ አቋም የግል እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሸፍናለች፡ ፡ በቡዳፔስቱ የዓለም ቻምፒዮና 10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ስታጠልቅ በዳይመንድ ሊግ እና በቤት ውስጥ የቱር ውድድሮች ስኬትን ልትቀዳጅ ችላለች፡፡ ዓመቱን ያጠናቀቀችውም በዓለም ቻምፒዮና ሁለት ሜዳሊያዎችን የማጥለቅ ቁጭቷን በዩጂን ዳመንድ ሊግ በመወጣት ሲሆን፤ የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን ወደ ኢትዮጵያ መልሳ የክብር ባለቤት መሆኗ የሚታወስ ነው፡፡

ያለፈውን ዓመት በአስደናቂ ብቃትና ስኬት ያጠናቀቀችው አትሌቷ በተያዘው ዓመት በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት እንድትጠበቅ አድርጓታል፡፡ የኦሊምፒክ ዓመት እንደመሆኑ በታላቁ የውድድር መድረክ የምታስመዘግበው ድል ከወዲሁ አጓጊ ነው፡፡ በእርግጥ የውድድር ዓመቱን በቤት ውስጥ ቻምፒዮና የጀመረች ሲሆን በ3 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች። በዳይመንድ ሊጉ ጎን ለጎን በ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰንን ለመስበርም ሙከራ ላይ ነበረች፡፡ የዚህ ዓመት ግቧ ግን ኦሊምፒክ በመሆኑ ዛሬ ላይ 47 ቀናት ብቻ ለቀሩት የፓሪሱ ኦሊምፒክ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡

በእርግጥም በወጣቶች ቻምፒዮና፣ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና፣ በዳይመንድ ሊግ እና የዓለም ቻምፒዮና መድረኮች ተሳትፎ ባስመዘገበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት የተንቆጠቆጠው መደርደሪያዋ በኦሊምፒክ መድረክ ግን በአንድ ነሐስ ብቻ የተገደበ ሆኗል፡፡ ስለዚህም ፓሪስ ላይ አዲስ ታሪክ ለማጻፍ ወጥናለች፤ ይህንንም ‹‹ሀገሬን በዚህ መድረክ መወከል መቻሌ የሚሰጠኝ ስሜት ከፍተኛ ነው፤ ሕዝቡ ሁሌም ሜዳሊያ እንድናስመዘግብ ይጠብቃል፡፡ ቀደምት አትሌቶችም ይህንኑ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን የእኔ ግብ ሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ ነው፡፡ ሀገሬን ስወክል ሁሌም ኃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል›› ስትል ትገልጻለች፡፡

ከዓለም አትሌቲክስ ጋር አጭር ቆይታ የነበራት የ27 ዓመቷ አትሌት ጉዳፍ ‹‹ኦሊምፒክ ትልቅ የውድድር መድረክ በመሆኑ የምንጊዜም ህልሜ ነው፡፡ በአትሌቲክስ የማስበውን ሁሉ ማሳካት ብችልም በኦሊምፒክ ወርቅ ማግኘት ግን ይቀረኛል፤ በመሆኑም ቀጣዩ ግቤ ይህ ነው›› ስትልም አጽንኦት ትሰጣለች፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You