አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዘመን መስታወት ነው፡፡ የዘመን መስታወት ነው ማለት በየዘመኑ የነበሩ ሁነቶችን ያሳየናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ‹‹ሳምንቱ በታሪክ›› በተሰኘው ዓምድ እንኳን ብዙ ታሪኮችን አይተንበታል፡፡
ዛሬ ደግሞ የራሱን ታሪክ ልናይ ነው፡፡ የዘመን መስታወት የሆነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ መታተም የጀመረው ከ83 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ነው። የጋዜጣው 83ኛ ዓመት ባለፈው አርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ነበር፡፡ ይህ የዜናም የታሪክም ነጋሪ የሆነ ጋዜጣ እስኪ ዛሬ የራሱን ታሪክ እናስታውስለት፡፡
ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት የታሪክ ክስተቶችን በጥቂቱ እናስታውስ፡፡
ከ24 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም ‹‹የፊደል ገበታ አባት›› በመባል የሚታወቁት ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ (ዘብሔረ ቡልጋ) ተወለዱ፡፡
ከ251 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 27 ቀን 1765 ዓ.ም፤ ቁንጅናቸው፣ በባልትና ሙያቸው፣ በፖለቲካ ብቃታቸው ተደናቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸው ጎላ ብሎ ከሚጠቀሱ እንስቶች መካከል አንዷ የሆኑት እና የአጼ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ አረፉ፡፡
ከ33 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 27 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ልክ በሳምንቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ፍንዳታ ተከሰተ፡፡ ፍንዳታው የተከሰተው ጎተራ በሚገኘው የጦር መሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤት ሲሆን፤ መላው አዲስ አበባን ያናወጠ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እና በርካቶችን ያቆሰለ ክስተት ነበር፡፡ በዚሁ ፍንዳታ ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ ቁርኝት የነበረው ታዋቂው ኬንያዊ የፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን በፍንዳታው አንድ እጁን አጥቷል፡፡ ጆን ማታይ የተባለው ባልደረባው ደግሞ ለሕልፈት ተዳርጓል፡፡ የወቅቱ ጊዜያዊ አስተዳደር (ኢህአዴግ) ድርጊቱን የፈፀሙት ‹‹የደርግ ርዝራዦች ናቸው›› ሲል ‹‹ኢህአዴግ ራሱ ነው›› የሚሉ ወገኖችም ነበሩ፡፡ ያም ሆነ ይህ ከደርግና ከኢህአዴግ የግንቦት ወር ክስተቶች አንዱ ሆኖ በታሪክ ይታወሳል፡፡
ከ24 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 27 ቀን 1992 ዓ.ም በኢትዮጵያ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው፣ በ24 ሰዓት ሥርጭት የመጀመሪያ የሆነው ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሥርጭቱን ጀመረ፡፡ በዚህ ዓመት 24ኛ ዓመቱን ሲያከብር ‹‹ለተሻለ ነገ እናንብብ›› በሚል መሪ ሃሳብ የ100 ቀን ልዩ የንባብ ዘመቻ አካሂዷል፡፡ በዚህም 99 ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲዎችና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች መጻሕፍትን ሲጠቁሙ ቆይተው በመጨረሻም በ100ኛው ቀን በውይይት፣ በመጽሐፍ ዓውደ ርዕይና ሽያጭ ተጠናቋል፡፡
ከ80 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 28 ቀን 1936 ዓ.ም ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍን በመተረክ የሚታወቀው ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ተወለደ፡፡ የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ስለወጋየሁ ንጋቱ ተጠይቀው ‹‹ፍቅር እስከ መቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ከ32 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም የጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ ሕይወት አለፈ፡፡ ጳውሎስ ኞኞ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥብቅ ቁርኝት ስላላቸው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር አያይዘን እናነሳዋለን፡፡ በዚሁ ወደ ታሪክ ነጋሪው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ታሪክ እንለፍ፡፡
ከታሪክ መጻሕፍት ጀርባ ማጣቀሻ ሆኖ እናገኘዋለን። የታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪክ ሲጻፍ ምንጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ የታላላቅ ደራሲዎችና ፖለቲከኞች ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ ወደ አንድ ምዕተ ዓመት የተጠጉ ሁነቶች ተሰንደው ይገኙበታል። ከ80 ዓመታት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ጥበባዊ ሁኔታዎች ይገኙበታል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ!
በዚህ ‹‹ሳምንቱ በታሪክ›› በሚለው ዓምድ ሥር ከብዙ ዓመታት በፊት በሳምንት ውስጥ የተከሰቱ ክስተቶችን የምናስታውሰው እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያሉ አንጋፋ ታሪክ ሰናጆች ባስቀመጡት ሰነድ ነው፡፡ የሌሎችን ክስተቶች ታሪክ ሲናገር የኖረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የራሱ ታሪክ በጣም ሰፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ እነሆ ለ83 ዓመታት የሀገሪቱ ብቸኛ ዕለታዊ ጋዜጣ በመሆን የአራት ሥርዓተ መንግሥታትን (የአሁኑን ጨምሮ) ምንነት ሰንዶ አስቀምጧል፤ እያስቀመጠ ነው። የእነዚህ መንግሥታት ባህሪም የሚታወቀው በዚሁ ጋዜጣ ነው፡፡
አሁን ላይ ያለ ወጣት ንጉሣዊ ሥርዓቱ ምን አይነት እንደነበር አያውቅም፡፡ ቤተ መጻሕፍት በመግባት ግን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማግኘት ይችላል፡፡ የጋዜጣ ሰነድነት ከመጻሕፍትና ከሌሎች ሰነዶች ይለያል፡፡ ምክንያቱም ዜናዎች አሉበት፡፡ ዜና በወቅቱ ዜና ይሁን እንጂ ከዘመናት በኋላ ግን ታሪክ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የመንግሥታት ዕለታዊ ክንውኖች ስለሚጻፉበት ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስሙ ከታላላቅ ደራሲዎች ጋር ይነሳል፡፡ የእነዚህ ደራሲዎች ስም ሲነሳ አዲስ ዘመን፣የአዲስ ዘመን ስም ሲነሳ የእነዚህ ደራሲዎች ስም ተያይዞ ይጠራል። በተለይ የበዓሉ ግርማ እና የጳውሎስ ኞኞ ግን ይደጋገማል። ምክንያቱም እነዚህ ደራሲዎች በታሪክ እና በፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለፈጠሩ ነው፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን እና ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የሰሩ ታላላቅ ደራሲዎች ናቸው፡፡ ብርሃኑ ዘሪሁን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ ሌሎች አንጋፋና ወጣት ደራሲዎችም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በቋሚ ተቀጣሪነትም በፍሪላንሰርነትም፣ በውጭ ፀሐፊነትም የሰሩ ብዙ ናቸው። እነ ማዕረጉ በዛብህ፣ ደራሲ ዘነበ ወላ፣ አንተነህ ይግዛው…. ይጠቀሳሉ፡፡ እስኪ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታሪክ ጋር ስማቸው የሚነሳውን ታላላቅ ደራሲዎች እና የአዲስ ዘመን ጋዜጣን የታሪክ፣ የጋዜጠኝነትና ስነ ጽሑፍ ትዝታዎች እናስታውስ፡፡
በዓሉ ግርማ
በዓሉ ግርማ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ እና የስነ ጽሑፍ አርበኛ ነው፡፡ በዓሉ ግርማ በተለይም ‹‹ኦሮማይ›› በተሰኘው መጽሐፉ ጋዜጠኝነትንም ስነ ጽሑፍንም አሳይቷል።
መጽሐፉ ጋዜጠኝነትንና ስነ ጽሑፍን የያዘ ነው፡፡ እንደ ጋዜጠኛ ያየውንና የሰማውን ጽፏል፡፡ የጋዜጠኛን ድፍረት አሳይቷል፡፡ ጋዜጠኛ አድርባይ፣ ወላዋይና ፈሪ መሆን እንደሌለበት አሳይቷል፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ህይወትን እስከማጣት መስዋዕትነት የሚከፈልበት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡
እንደ ስነ ጽሑፍ ካየነውም፤ እነሆ መማሪያ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ለብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ምንጭ ሆኗል፡፡ በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤትም በስነ ጽሑፍ ትምህርት ቤትም ማነፃፀሪያ ተደርጓል፡፡ የስነ ጽሑፍ አላባውያን ለሚባሉት መሰረት ሆኗል፡፡ በየስነ ጽሑፍ ውይይቱ የበዓሉ መጽሐፎች ስም ይነሳል፡፡ አገላለጾቹ ስነ ጽሑፋዊ ውበት ያላቸው ናቸው፡፡ ረቂቅ አገላለጽ ይጠቀማል። ተምሳሌታዊ ትርጓሜን አሳይቷል፡፡ ፍቅርን አሳይቷል፡፡
ለህይወቱ መጥፋት ምክንያት ስለሆነ እና ፖለቲካዊ ይዘት ስለሆነ ‹‹ኦሮማይ›› ተደጋገመ እንጂ ሌሎች መጽሐፎችም አሉት፡፡ የቀይ ኮከብ ጥሪ የሚለው መጽሐፉም እንዲሁ ፖለቲካና ስነ ጽሑፍን የያዘ ነው፡፡ ከአድማስ ባሻገር በብዛት የሚደጋገመው በስነ ጽሑፍ ሰዎች ዘንድ ነው፡፡ ሀዲስ፣ ደራሲው እና የህሊና ደወል የሚሉትም ቢሆን ተደጋግመው የተነበቡ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዓሉ ግርማ ለስነ ጽሑፍና ለጋዜጠኝነት ሙያ መስዋዕት የሆነ ሰው ነው፡፡ እንደ ታሪክ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን ክስተት አሳይቷል፡፡ ስለዚህ የበዓሉ ግርማ እና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታሪክ የጋዜጠኝነትም ታሪክ ነው፡፡
ጳውሎስ ኞኞ
ጋዜጠኛ የሆኑም ያልሆኑም ሰዎች ስለ ጳውሎስ ኞኞ እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ነገር ያውቃሉ፡፡ ይሄውም ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› የሚለው የጳውሎስ ኞኞ ጽሑፍ ነው። የትም ቦታ የጳውሎስ ኞኞ ስም ከተነሳ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የነበረው ይሄ ዓምዱ ይጠቀሳል፡፡ ጳውሎስን ለማስታወስ ሲባልም የሬዲዮ ፕሮግራም እና የህትመት ዓምዶችም ወጣ ገባ እያሉ ተሰይመዋል፡፡ በኩረጃ ሳይሆን እሱን ለማስታወስ መሆኑን እየጠቀሱ ማለት ነው፡፡
ስለጳውሎስ ኞኞ የጋዜጠኝነት ፍቅር አንድ ጓደኛው የነበረ ሰው በሬዲዮ ሲናገር የሰማሁትን ገጠመኝ ላካፍላችሁ፡፡
ጳውሎስ ታሞ ተኝቶ ነው፡፡ ጓደኞቹ ሊጠይቁት ከቤቱ ይሄዳሉ፡፡ ሲሄዱ በፀና ታሞ ተኝቷል፡፡ ብዙም አያናግራቸውም፤ በህመም ላይ አናጨናንቀውም ብለው ዝም ብለዋል፡፡ በቤቱ ውስጥ የተከፈተው ሬዲዮ እያወራ ነው፡፡ ጋዜጠኛው አንድ ስህተት ይሳሳታል፡፡ ይህኔ ጳውሎስ ‹‹አይ! አዳምጡትማ ይሄን ጋዜጠኛ…›› ብሎ የጋዜጠኛውን ስህተት አስተካክሎ ነገራቸው፡፡ በህመም ላይ ያለ ሰው፤ እንኳን ስህተትን ነቅሶ ማውጣት ስለምን እየተወራ እንደሆነ ራሱ ልብ አይልም ነበር፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ግን በህመም ውስጥ ሆኖ እንኳን መረጃን እያጣራ ይሰማ ነበር ማለት ነው፡፡
ስለ ጳውሎስ ኞኞ የሚነገር ሌላ አንድ አስቂኝ ገጠመኝ ደግሞ አለ፡፡ ለስታዲየም መስሪያ ተብሎ መዋጮ እየተዋጣ ነው፡፡ የኳስ ነገር ያልጣመው ጳውሎስ ‹‹ኧረ ይሄ ነገር ይቅር›› ይላል፡፡ በጣም ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሲነግሩት ‹‹አሥራ አንድ ጅሎች አንድ ቅሪላ ሲከታተሉ ለማየት አላዋጣም›› ብሎ የተሰበሰበው ብር ለሆስፒታል ግንባታ መዋል እንዳለበት ተናግሯል፡፡
ጳውሎስ ኞኞን የሚያውቀው ሁሉ አንድ የሚያውቀው ታሪኩ ደግሞ በመደበኛው ትምህርት ከ4ኛ ክፍል በላይ ያልተማረ ምሁር መሆኑ ነው፡፡ የታሪክ ተመራማሪ ነው። በኢ-መደበኛ ትምህርት እና በጥልቅ ንባብ ምሁር መሆን እንደሚቻል ያሳየ ሰው ነው፡፡ ‹‹የሴቶች አምባ፣ አጤ ምኒልክ፣ አጤ ቴዎድሮስ ፣ አስደናቂ ታሪኮች ፣ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ፣ አራዳው ታደሰ ፣ የኔዎቹ ገረዶች ፣ የጌታቸው ሚስቶች ፣ ምስቅልቅል፣ እንቆቅልሽ ፣ አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች›› የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፎች ናቸው፡፡ ይሄ ሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የታሪክ ተመራማሪ ብቻ አልነበረም፡፡ በእርሻ ሚኒስቴር (ለዚያውም ገና በ17 ዓመቱ) የእንስሳት ሐኪም ሆኖም ሰርቷል፡፡
ጳውሎስ በጋዜጠኝነት ዘርፍ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለአመታት መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት ህዝብን በማንቃት በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፏል።
ጳውሎስ ኞኞን ዛሬ የምናስታውሰው ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባለው ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ የራሱ የሕይወት ታሪክም በዚህ ሳምንት ስለሚታወስ ነው፡፡ ጳውሎስ ኞኞ ህይወቱ ያለፈው ከ31 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ነው፡፡ ከአዲስ ዘመን ጋር ያላቸውን ቁርኝት የሥራ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ታሪኩም አቀራርቦታል ማለት ነው፡፡ እነሆ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይውልና ሲወደስ ይኖራል፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን
ዕውቁ የስነ ጽሑፍና የታሪክ ሰው ብርሃኑ ዘሪሁን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ እያለ ከመንግሥት ጋር ይጋፈጥ እንደነበርም ይነገራል፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ውስጥ ትልቅ አሻራ አስቀምጧል፡፡ ለታሪካዊ ልቦለድ አጻጻፍ ፈር ቀዳጅ ሆኗል፡፡ የተውኔት ሥራዎችን እና የታሪክ ምርምሮችን ሰርቷል፡፡
‹‹የቴዎድሮስ እንባ፣ የታንጉት ምስጢር፣ ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ ማዕበል የአብዮት መባቻ፣ ማዕበል የአብዮት ማግስት፣ ጨረቃ ስትወጣ››፣ አማኑኤል ደርሶ መልስ፣ የእንባ ደብዳቤዎች፣ የበደል ፍፃሜ›› የሚሉት መጻሕፍት ሲሆኑ፤ ‹ባልቻ አባነፍሶ፣ ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ፣ የለውጥ አርበኞች፣ ሞረሽ…›› የተሰኙ ተውኔቶችን ጽፏል፡፡
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታሪክ ሲነሳ የእነዚህ ሁሉ ሰዎች ታሪክ ነው የሚነሳው፡፡ ለዚያውም ትልልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሳይዳሰሱ ማለት ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ እንኳን የአዲስ ዘመን ጋዜጣን ስም የሚያስጠሩ ብዙ ታላላቅ ሰዎች አሉ፡፡
በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ንጉሣዊ ሥርዓቱ ምን እንደነበር፣ በወቅቱ ምን አይነት ዜናዎች ይሰሩ እንደነበር፣ ምን አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ይደረጉ እንደነበር ይነግረናል፡፡ በወታደራዊው የደርግ መንግሥትም ሆነ በአብዮታዊው ኢህአዴግ ዘመን የነበሩ ሁነቶችን ሁሉ ከዚሁ ጋዜጣ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ እነሆ በአሁኑ የብልጽግና አስተዳደርም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዕለታዊ ሁነቶችን እየዘገበ ዛሬን ለነገ እያስቀመጠ ነው፡፡
ጋዜጣው ‹‹አዲስ ዘመን›› የሚለውን ስያሜ እንዴት አገኘ? የሚለውን እና የመጀመሪያው ዕትም ላይ የወጡ ጽሑፎችን እናስታውሳችሁ፡፡
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ ሲገቡ ለሕዝቡ ባደረጉት ንግግር ‹‹… ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል …›› ብለው ስለነበር ጋዜጣውም ‹‹አዲስ ዘመን›› ተብሎ ተሰየመ፡፡
በጋዜጣው የመጀመሪያ ዕትም የመጀመሪያ ገጽ ላይ ንጉሰ ነገሥቱ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ምክንያት ከአምስት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባ ሲገቡ የሚያሳየውን ፎቶግራፍ እና ስለጋዜጣው ዓላማ የሚገልፅ ጽሑፍ ወጥቶ ነበር፡፡
‹‹ … ይህ አዲስ ዘመን ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረዳትነቱን ስራ ይሰራ ዘንድ ተመሰረተ፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ አዲስ በሆነው ዘመን ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የሚያስፈልገውን ስራ ሁሉ እያመለከተ፤ ይልቁንም ሕዝብ ለሀገሩ ለመሪውና ለንጉሰ ነገሥቱና ለንጉሰ ነገሥቱም መንግሥት ማድረግ የሚገባውን እየገለፀ የበጎን ስራ መንገድ የሚመራ እንዲሆን ይህ ጋዜጣ በግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ተመሰረተ፡፡
ስራውም በሦስት ቃሎች ይጠቀለላል፡፡ እውነት፣ ረዳትነትና አገልግሎት፡፡ እውነት ስንል በዚህ ጋዜጣ የሚነገረው ነገር ሁሉ መሰረቱ በፍጹም እውነትን እየተከተለ ለአንድ ጥቅም ብቻ ያልሆነና ለመላው ጥቅም የሚሰራ እንዲሆን ነው። አገልግሎት ስንል የኢትዮጵያን ነፃነት ለመመለስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የራሳቸውን ጥቅም ሁሉ አስወግደው ለሕዝባቸውና ለሀገራቸው ሲሉ የሰው አቅም ሊሸከመው የማይቻለውን ድካም ተቀብለው ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ያልተቻለውን በኢትዮጵያ ሕይወት ውስጥ እስከዛሬ ድረስ ያልታየውን ስራ ከፍፃሜ ላደረሱ ለተወደዱ ንጉሰ ነገሥታችንና ላቆሙት መንግሥት የሚያገለግል እንዲሆን ነው…›› የሚል ነበር፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዕለታዊ ሁነቶችን እየዘገበ እነሆ 83 ዓመታት ተጓዘ፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም