ድጋፍ የሚሻው የልብ ሕሙማን መርጃ

በሕይወት ውጣውረድ ውስጥ ቤተሰብ በብዙ መልኩ ይፈተናል:: ገንዘብ አጥቶ የሚልሰው፤ የሚቀምሰው ያጣል:: መጠለያ ተቸግሮ ጎዳና ላይ ይወጣል:: ችግሮች ይበልጥ ከበረቱ ደግሞ እስከመበተንም ይደርሳል:: ጤናው ሲቃወስም እንደዛው:: የወይዘሮ ትዕግስት መርሻ ቤተሰብም በልጃቸው ጤና መታወክ ምክንያት በብርቱ ተፈትኗል:: ግራ ተጋብቷል:: የሚይዘው የሚጨብጠውን አጥቷል::

ወይዘሮ ትዕግስት መርሻ የሚኖሩት በቢሾፍቱ ከተማ ነው:: ልጃቸው ተወልዶ አንድ ወር እንደሞላው ነበር ጉንፋን ይዞት ወደ ክሊኒክ የወሰዱት:: ሀኪሞች ሲመረምሩት የሳምባ ምች ነው ብለው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ፃፉላቸው:: ወደሆስፒታሉ መጥተው ልጃቸውን ሲያስመረምሩ የሳምባ ምች መሆኑን ሃኪሞች በድጋሚ አረጋግጠውላቸው፣ መድሃኒት እንዲጀምርም አዘዙ:: መድሃኒቱን ቢወስድም የልጃቸው ጤና ግን ሊመለስ አልቻለም:: እንደገና ተጨማሪ ምርመራ ሲደረግለት የልብ ታማሚ መሆኑ ተረጋገጠ::

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ፅፎለት ወደ ኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህፃናት መርጃ ማእከል እንዲመጣ ተደረገ:: ከዛም በየሶስት ወሩ ክትትል ማድረግ ጀመረ:: በመጨረሻም መስከረም 2015 ዓ.ም የልብ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ ከማእከሉ ተደውሎ ተጠራ:: የቀዶ ሕክምናውንም በተሳካ ሁኔታ አደረገ:: አሁን ልጃቸው የጤና ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል:: የጤና ሁኔታውንም በየግዜው ወደ ማእከሉ እየመጣ ይከታተላል:: በዚህም ወይዘሮ ትዕግስት ደስተኛ ሆነዋል:: ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበትም ነው ወይዘሮ ትዕግስት በዚህ አጋጣሚ መልእክታቸውን የሚያስተላልፉት::

ወይዘሮ ትዕግስት ልጃቸውን ሊያሳክሙ የቻሉት ለበርካታ ግዜ ወረፋ ሲጠባበቁ ከቆዩ በኋላ ነው:: እርሳቸው በጣም እድለኛ ናቸው:: ምክንያቱም ወረፋ እየተጠባበቁ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ ልጆቻቸው ያረፉባቸው ወላጆች ጥቂት አይደሉምና::

በኢትዮጵያ እንደልብ ካልተስፋፉና ከፍተኛ ችግር ከሚታይባቸው የሕክምና ዘርፎች ውስጥ አንዱ የሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና ነው:: የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ከተቋቋመ ሰላሳ አምስት ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም በእነዚህ ጊዚያት ውስጥ ከዚህ ማእከል ውጪ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡና ማእከሉን የሚደግፉ ሌሎች ጤና ተቋማት አልበቀሉም:: በዚህም ምክንያት ይህ ማእከል የብዙ ኢትዮያውያንን ጫና ተሸክሞ ላለፉት ሰላሳ አምስት ዓመታት የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል:: በዚህም በርካታ ሕፃናትን የመኖር ተስፋና ጤና አለምልሟል::

አሁንም ማእከሉ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠባበቁ በርካታ ሕፃናትን ተቀብሎ ለማስተናገድ እየተፍጨረጨረ ነው:: ማእከሉ በተቻለው አቅም ሁሉ ለሕፃናቱ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ታዲያ አገልግሎቱን ከሚፈልጉ ሕፃናት ቁጥር ጋር በሚመጣጠን መልኩ ባለመስፋቱ፣ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን በየግዜው በቶሎ ባለማግኘቱና በበቂ ሁኔታ ድጋፍ እያገኘ ባለመሆኑ የልብ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱን በሚፈለገው ልክ ለፈላጊዎች ተደራሽ ማድረግ ተስኖታል:: እንዲያም ሆኖ ግን በብዙ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በየግዜው በሚደረግለት ድጋፍ እስካሁን ድረስ አገልግሎቱን ማስቀጠል ችሏል::

አቶ ንጉሴ ቦጋለ የእዮብ ተስፋ ለልጆችና ለወጣቶች ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅቱ ከ25 ሺ ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የልብ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የሕክምና ግብዓቶችን ለልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ በቅርቡ ድጋፍ አድርጓል:: በዚህ ድጋፍ የተካተቱ የሕክምና ግብዓቶች ለልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እጅግ አስፈላጊ ሲሆኑ በዋናነት የልብ ክፍተት ችግር ያለባቸው 40 ወረፋ በመጠበቅ ላይ ያሉ ሕፃናት በድጋፍ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል:: ከዚህ በፊትም ድርጅቱ 20 ሺ ዶላር ዋጋ ያላቸው ተመሳሳይ የሕክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጎ 32 ሕፃናት የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ አደርጓል:: ከልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተመሳሳይ የሕክምና ግብዓቶች ድጋፎችን አድርጓል::

አቶ ንጉሴ እንደሚያብራሩት፣ ድርጅቱ ይህን ድጋፍ ለማበርከት የተነሳሳበት ዋነኛ ዓላማ የጓደኛቸው ልጅ እዮብ ቅርጫት ኳስ በመጫወት ላይ እያለ ባጋጠመው የልብ ሕመም ምክንያት በአሜሪካን ሀገር ሕይወቱ በማለፉና የእርሱን ሕይወት ማለፍ ተከትሎ በርካታ ሕፃናትና ታዳጊዎች በልብ ሕመም ምክንያት ሕይወታቸው እንዳይቀጠፍና ተገቢውን የልብ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚያደርጉና የኢትጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ የመሰሉ ማእከላትን በእርሱ ስም ለመደገፍና ለማበረታታት ነው::

ድርጅቱ እንዲህ አይነቱን ድጋፍ የሚያደርገው በውጪና በሀገር ውስጥ ካሉ የእዮብ ቤተሰቦችና ዘመዶችን ገንዘብ በማሰባሰብ ሲሆን በዚህ የእርዳታ ማሰባሰብ ሌሎችንም ኢትዮያውያንን አካቶ እርዳታውን ከዚህም በላይ ማሳደግ ይፈልጋል:: ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል:: ነገር ግን እዮብ ተስፋ ለልጆችና ለወጣቶች ተራድኦ ድርጅትና ሌሎችም ለማእከሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ እውቅና ከመስጠት አኳያ በመንግስት በኩል ክፍተት ይታያል:: እንዲህ ያለው ድጋፍ እውቅና ቢሰጠው ግን ሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ያነቃቃቸዋል::

ድርጅቱ ምንም እንኳን የእዮብ ቤተሰቦችንና አንዳንድ ደጋግ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ድጋፍ እያሰባሰበ የሚገኝ ቢሆንም በአዲስ አበባም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንም በማሳተፍ ለኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ድጋፍ ማሰባሰብ ይፈልጋል:: ይህንን ለማድረግ ደግሞ ድርጅቱ ከመንግስት በኩል እውቅና እንዲሰጠው ይፈልጋል:: በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ሊረዱ የሚገቡ ሕፃናት ተገቢውን እርዳታ እያገኙ አይደሉም:: የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት አሁንም በርካታ ሕፃናት ወረፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ:: ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ከመንግስት በኩል እውቅና አግኝቶና ተመዝግቦ በኢትዮጵያ ስራውን ቢጀመር ወረፋ እየተጠባበቁ የሚገኙ በርካታ ሕፃናት በአንድ ግዜ የሚታከሙበትን ሁኔታ ያመቻቻል:: ለዚህም ድርጅቱ በራሱ በኩል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል:: አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ለድርጅቱ ቀና ትብብር እያደረጉ ይገኛሉ::

በቀጣይም በአሜሪካን ሀገር አትላንታ ላይ በሚደረገው የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የእግር ኳስ ጨዋታ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስለሚገኙ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እርዳታ ለማሰባሰብ ድርጅቱ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: ይህም ከዚህ ቀደም ድርጅቱ ከእዮብ ቤተሰቦች ብቻ ሲያሰባስብ የነበረውን እርዳታ ከመላው ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ ለልብ ሕሙማን መርጃ ማእከሉ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማሳደግ ያግዘዋል::

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕህፃናት መርጃ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ህሩይ አሊ እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና የሚሰራ የሕክምና ተቋም ይኸው የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ብቻ ነው:: ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ላላት ሀገር ግን ይህ መርጃ ማእከል በቂ አይደለም:: በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ድርጅት እርዳታ ብቻ መርጃ ማእከሉ ሊቀጥል አይችልም:: ነገር ግን እርዳታው ማሳያ ሊሆን ይችላል:: እርዳታዎቹ ከተለያዩ ቦታዎች ከመጡና ትብብርና ድጋፍ ካለ አሁን ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ በእጥፍ ያሳድገዋል:: በሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በግለሰቦችና በራሱ በመርጃ ማእከሉ የሚሰጠውን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው::

መርጃ ማእከሉን እየገጠሙት ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ሲሆን አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ለመሸፈን የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልገዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ወስጥ መርጃ ማእከሉ ብዙ ገንዘብ ቢኖረውም ከ80 በመቶ በላይ ያለው አላቂ የሕክምና መሳሪያዎች በሀገር ውስጥ አይገኙም:: ከዚህ አኳያ እነዚህን መሳሪዎች ከመግዛት ይልቅ ከውጪ ሀገር መሳሪያዎቹን በአይነት ድጋፍ እንዲደረግለት ይፈልጋል::

አሁን ባለው ሁኔታ ከ7 ሺ በላይ የሚሆኑ ሕፃናት የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ እየተጠባበቁ ይገኛሉ:: በተመላላሽ ሕክምና ክፍል ዓመት ከ13 እስከ 14 ሺ የሚሆኑ ሕፃናት ክትትል ያደርጋሉ:: በአንድ ዓመት ከ400 አስከ 450 የሚሆኑ ሕፃናት ደግሞ ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ:: አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከ780 እስከ 1000 የሚሆኑ አዳዲስ ታካሚዎችን መርጃ ማእከሉ እየተቀበለ ነው:: ይህ በንፅፅር የአዳዲስ ታካሚዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል::

ስለዚህ እነዚህን አዳዲስ ታካሚ ሕፃናትን በቀዶ ሕክምና ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህ ግን ድርጅቱ እስካሁን አልታገዘም ማለት አይደለም:: ከችግሩ ስፋት አንፃር ግን ገና ብዙ ድጋፍ ያስፈልገዋል:: በዚህ ረገድ በሁሉም አቅጣጫ ብዙ መስራት ይጠይቃል:: ከዚህ አኳያ የሚደረገውን ድጋፍ ለማጠናከርና የመርጃ ማእከሉን ገቢ ለማሳደግ በቋሚነት የሚደግፉትን ለምሳሌ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም በመሰሉ ድርጅቶች በማካኝነት በአጭር የፅሁፍ መልክት ሕብረተሰቡ እርዳታ እንዲያደርግ የሚደረጉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ::

በአይነት የሚደግፉ በውጭ ሀገር የሚገኙ ድርጅቶች አሉ:: በነዚሁና ሌሎችም ደርጅቶች አማካኝነት ገቢ ለማሰባሰብም መርጃ ማእከሉ ጥረት ያደርጋል:: በቅርቡም በአሜሪካን ሀገር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይኖረዋል:: ሌሎችም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ጥረቶች አሉ:: ነገር ግን ይህ ሁሉ ተደርጎ አሁን ያለውን ችግር በአንድ ሆስፒታል ብቻ መቅረፍ አይቻልም::

ከዚህ አኳያ አንዱ መርጃ ማእከሉ ጠንክሮ መስራት ያለበት የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ነው:: ለዚህም ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥሮ እየሰራ ይገኛል:: ቢያንስ ይህ የመርጃ ማእከል በመከፈቱ ቀደም ሲል ወደውጪ ሀገራት ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ለመታከም የሚሄዱትን ወጪ ማስቀረት ተችሏል:: ቀጣይ ደግሞ ከየክልሉ የሚመጡትን ታካሚዎች በተቻለ መጠን ቅድመና ድህረ ክትትላቸውን እዛው ባሉበት ሆነው የሚከታተሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ጋር እየሰራ ይገኛል:: ከዚህ አንፃር መርጃ ማእከሉ በሰው ሃብት ልማት ላይም ሆነ የሕክምና አገልግሎት ቁጥሩን በመጨመር ላይ ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራ ነው::

ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፣ ለልብ ቀዶ ሕክምና ስራ ላይ የሚውሉት ሕክምና መሳሪያዎች በጣም ውድ ናቸው:: ነገር ግን መሳሪያዎቹ በየዓመቱ የሚገዙ ባለመሆናቸው የተወሰነ ግዜ እፎይታ ይሰጣሉ:: አላቂ እቃዎቹ በራሳቸው በሀገር ውስጥ ካለመገኘታቸው ባሻገር በጣም ውድ ናቸው:: በዚህ ምክንያት የአንድ ሕፃን ወላጅ ከ700 እስከ 800 ሺ ብር ለልብ ቀዶ ሕክምና ሊያወጣ ይችላል:: ይህን ወጪ ደግሞ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ወላጆች መሸፈን አይችሉም:: ለዛም ነው የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከል የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱን በነፃ የሚሰጠው::

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማእከልን መርዳት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም:: በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በርካታ በዝቀተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወላጆች ሕፃናትን አወንታዊ በሆነ መልኩ ሕይወታቸውን መቀየር ማለት ነውና ነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን እነዚህን ሕፃናትንና ታዳጊዎችን መርዳት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን አለበት::

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You