ከቤቴ ስወጣ አራት መንታ መንገዶች ያገጡብኛል። መሀል ላይ ክብ ቅርጽ ሰርተው ሃሳቤን ይቀሙኛል። አንዱ ወደመስኪድ፣ አንዱ ወደስላሴ ቤተክርስቲያን፣ የተቀሩት ሁለቱ ወደማፈቅራት ሴት ሰፈር እና መቼም ልሄድበት ወደማልፈልገው የሆነ ሰፈር። ወደማፈቅራት ሴት ሰፈር ከሚወስደኝ መንገድ ሌላ ወዴትም አልሄድም። ገና ከቤት ስወጣ እግሮቼን ሳላዛቸው እዛ መንገድ ላይ አገኛቸዋለሁ። ከንቱነቴን ከሚነግሩኝ አጋጣሚዎች አንዱ የቤቴ አራት መንታ መንገዶች ናቸው። እግዜርን አስትቶ፣ አላህን አስረስቶ ወደሴት የሚወስድ ሃሳብና ምኞት ምን ይባላል? ለእግዜርና ለአላህ ያልሆንኩ የራሴ ምርኮኛ። ራስ ከሰማይ ነው የሚጀምረው…ከአላህና ከእግዜር ዙፋን። በብዙ አማራጭ ብንከበብም ከሰማይ እስካልጀመርን ድረስ መንገድ ይጠፋናል። ወደምወዳት ሴት ሳገድም ቤተክርስቲያን ስሜ፣ መስኪድ ተንበርክኬ ብለማምን በምሄድበት መንገድ እሷ ትመጣ ነበር የሚለው ያልገባኝ የማይገባኝ ነው።
እኛ ሰዎች የሚሻለንን አናውቅም። በተፈጥሮ ሳይሆን በራሳችን ቅደም ተከተል የምንጓዝ ነን። አላህና እየሱስን በራፌ ላይ ሆነው አልተጠቀምኩባቸውም። በቅዳሴና በአዛን ማልደው ሲቀሰቅሱኝ እንኳን ያቺን ቆሽማዳ ሴት ቀርቶ ከዓለም ቆንጆዋን መርጠው ጀባ እንደሚሉኝ የጠፋኝ ነኝ። ለአንዲት ጉብል እየሱስና አላህን መካድ.. ይሄ አይደል ከአፈር ወደአፈር? ይሄ አይደል እጸበለስን ካስበላው የከፋ ግፍና በደል? ህይወት አንድ ልክ እንጂ ሁለትና ሶስት ልክ የሆነ የላትም። አንዱ እውነት ነው ወደሌሎች እውነት የሚመራን። አንዱ ልክነት ነው ወደሌሎች የሚያራምደን።
እየሱስን አስትተው ወደሰፈሬ ጉብል በወሰደኝ አራት መንታ መንገድ ትካዜ ወደቀብኝ። ውል ነው የጠፋብን.. ውሉን ያገኘ እንደቱባ ክር ካለጉርብጥባጤ ህይወትን ይተረትራታል። ውሉን ያጣ እንደእኔ እየሱስንና አላህን ደጃፉ ጋ አስቀምጦ ወደማይጠቅመው ይራመዳል። ያልቻልነው ውሉን ማግኘት ነው። በዘፈቀደ መሀል፣ ዳር፣ ግራና ቀኝ ዳክረናል። በያዝ ለቀቅ ውሉን ሰውረነዋል። እናም ተበጣጥሰናል..
ህይወት እንደቱባ ክር ናት…መሰረተ ውሏ ከተገኘ አታስለቅስም..አታስተክዝም። ውሏን ለማግኘት መሀሏን መበጠስ ውሏ ቢገኝ እንኳን መሀል ላይ እንድንቆም የሚያደርግ ነው። ከመበጠስ እና ከመወታተፍ በዝግታ ውሏን መሻት..በህይወት መዝገብ ውስጥ የተጻፈ የሰው ልጆች ሁሉ ቀዳማይ ጥበብ ነው።
እጄን አገጬ ላይ አሳርፌ የመጣሁበትን እቃኛለው… የምሄድበትንም። የረገጥኳቸው አምናና ካቻምናዎች… የምረግጣቸው የራቁ ከርሞዎች በነፍሴ ፊትና ኋላ ላይ ታትመው ከአፈር ወደአፈር ማንነቴን ይነግሩኛል። አጭር ታሪክ ከዘለገ አርምሞ ጋር ሰውነቴን አሳድፈው እንድጠይቅ፣ እንድሞግት፣ እንድመራመር፣ እግዜር ዓለም የለም እንድል ይተናነቁኛል። በትናንትና በነገ ተቋጥሮ ከአፈር ወደአፈር የሚደረግ ግስጋሴ፣ ሰው በመሆን ሶስት መቶ ስልሳ ዲግሪ ውስጥ የሚደረግ እሽክርክሪት..የመኖር ጣሙን ያመሩብኛል..የሰው መሆንን ቅል ያጠፉብኛል።
አሁንን እንጂ እኮ ነገን አናውቀውም። ማን አሁን የነገ መተከዣ እንደሆነ አስቦ ያውቃል? ማንስ የዛሬ ብርሀኖች የነገ አስፈሪ ጉሞች እንደሆኑ አምኖ ያውቃል? በለምለም ዜማቸው ስር ያስጠለሉን የዛሬ ጥላዎች የነገ ተሲያቶች.. የከርሞ ጠራራዎች ናቸው። እንደጀምበር ከታሪካችን ማህጸን ላይ ፍጭጭ ብለን ወደማብቂያችን አድማስ እንሄዳለን..ከአፈር ወደአፈር።
ምንም አናመጣም..ምንም አምጥተንም አናውቅም። ይሄን ሥርዓት ለመገርሰስ ሰው በመሆን ውስጥ ብዙ መላምቶች ተሞክረዋል…ግን ምንም አልመጣም ሊመጣም አይችልም። ምንም መሆናችን ምንም ያለማምጣታችን ምሳሌ ነው። ምንም እንደማናመጣ እንድናውቅ ምንም መሆናችንን ልናውቅ ይገባል።
ከምላሳችን ላይ ጸጉር ነጭተን..በሁለት መልክ ጸጉራችን ምለን…ዋሽተንና እንደይሁዳ ከድተን አሁንም ሰው ነን። ሥርዓትን ሽረን፣ በነውር ዘምነን፣ ቧልተን፣ ተዘባብተን አሁንም ሰው ነን። ቃል አጥፈን፣ እምነት አጉድለን፣ ተመጻድቀን፣ ተታብየን፣ አስመስለን፣ ሰርቀንና አስጨንቀን አሁንም ሰው ነን። በዝሙት ዘምነን፣ በአምላክ ላይ ቀልደን፣ ንቀንና አቃለን፣ ሰይፈን፣ ተሰይፈን አሁንም ሰው ነን። እንዴት? ለምን?
ዝንተአለም ስንት ቀን ነው? መልኩ፣ ቀለሙ ምን መሳይ ነው? በህይወት ውስጥ ተሰንቅሮ ስለምን እንደርስበት ዘንድ ያዳክረናል? የማንደርስበት ነገ ለምን ተሰጠን? ነው ወይስ በዛሬና በነገ መሀል እያለፍነው እየሄድን ይሆን? ከፊት ለፊታችን ብዙ ዘላለማትን ከኋላችን ትተን ሄደንስ ቢሆን ማን ያውቃል? በማያልቅ ምኞት ስር የወደቅን አይደለን..! የፊቱን እንጂ ማን ኋላውን ተመልክቶ ያውቃል? አልደርስ ያልንበት ዘላለማት እግራችን ስር ደፍጥጠነው ወደነገ ልንሄድ እየተረማመድንበት ቢሆንስ? ከዛ አንባ የሰቀልነው በምኞት የምንዳክርለት ነገ የቆምንበት ዛሬ ቢሆንስ? ደግሞም ነው…ዛሬ ነገ ነበር…ትናንት ዛሬ ነበር። እናስ ዘላለማት ምንድነው? ያለንበትን ንቀን የሌለንበትን እየናፈቅን፣ የመጣውን ሰደን ላልመጣው እየተንጠራራን ምኞት ምንድነው? በማይቆም እግር ወደሚመጣው እየሄድን..ከወዴት ነው መቆሚያችን? መሄድ ብቻ ምንድነው? መቆም የሌለው…ማሰብ የሌለው…ብስለት የሌለው መሄድ…ዘላለማትን እያሳለፈ ዘላለማትን ከመጠበቅ በቀር መስከን አያውቅም።
ፊትለፊታችን እያየን የዘነጋናቸው ብዙ ኋላዎች አሉን። ወደፊት ማለት መልካም ነው ኋላን በመረሳት ውስጥ ፊተኝነት ግን ደርሶ መውደቅ ነው። ያመጡን አሮጌ ምንጣፎች ለክብራችን መሬት ሆነው ባያጸኑን ኖሮ፣ ያሻገሩን ንትብ ድልድዮች ተሰትረው ባያቆሙን ኖሮ፣ የተዘረጉልን ጎስቋላ እጆች፣ ያስደገፉን ዝንፍ ትከሻዎች ባያራምዱን ኖሮ ዛሬ ተረት ነበር።
ሰው ያለፈበትን እንደመርሳት ክህደት የለውም። ያለፉ ታሪኮቻችን አሁን ላለንበት ደማቅ ታሪክ መሀል አንጓዎች ናቸው። የመጡበትን ትናንት መካድ ራስን መካድ ነው። ወዴትም የምናንጸባርቀው ብርሀን የለንም የዛሬ ጨረሮች ከትናንት ያመጣናቸው ጭላንጭሎች ናቸው። ትናንትን መርሳት በብዙ ጨለማ ውስጥ ብርሀን የሆኑንን ከዋክብት ውለታ መብላት ነው…እናም ራስን መካድ።
በህይወት ማድጋ ውስጥ ያልገቡን፣ የማይገቡን ታሪኮች አሉ…ቢገቡን እንኳን ጠይቀን ልክ የማንሆንባቸው ልክ ብንሆንባቸው የማንደነቅባቸው ግዙፍ ምናምንቴዎች። ለምን ብለን ስንጠይቅ በተፋለሰ ኮቴ ውስጥ መቆማችን እንደምክንያት ይነሳል።
ዝንታለምን አናውቀውም…ብቻ በአንድ የተረገመ የመከራ ቀን ላይ አልነጋ ባለ ቀን እንመስለዋለን። ክፉ ቀን ረጅም ነው…ጠንበለል። የደስታ ቀን አጭር ነው… ድንክዬ። ጊዜ እዛም እዚህም አንድ አይነት ቢሆንም በስሜታችን በኩል ግን ብዙ አይነት ነው። እስክናድግ ድረስ ያለው ዘመን ዝንተአለም ነው፤ ካደግን በኋላ ደግሞ ወደኋላ መመለስን..ልጅ መሆንን ምንናፍቅ..ይሄ እኮ ነው ውል አልባነት።
በዚህ ከአፈር ወደአፈር ህይወት ውስጥ በአራት መንታ መንገድ ላይ ወደሞት የወሰደችን ሴታም ነፍስ መከተል..ጎለጎታን ረስቶ ባልተገራ በራስ ስሜት በራስ ላይ መጨከን ካልሆነ ምንም ሊባል አይችልም።
ቃሉስ ‹ወደመጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ። አፈር ነህና ወደአፈርም ትመለሳለህና› አይደል የሚለው..ዘፍጥረት 3-19
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም