አዲስ አበባ፡- የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ሥሪትና መንግስት ምስረታ ባለመጠናቀቁ ቀጣናው እስካሁን ድረስ በችግር ውስጥ እንዲማቅቅና ለዜጎች ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ተገለጸ።
ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ 18ኛውን የጥናትና ምርምር ጉባዔ ትናንት በጀመረበት ወቅት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ሰለሞን እምሩ፣ የአፍሪካ ቀንድ፤ ፌዴሬሽንና ያልተቀናጀ ግዛት በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ፤ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ስሪትና መንግስት ምስረታ አለመጠናቀቁን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 1991 ቀደም ብሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ክስተቶች የነበሩ ሲሆን፤ በዚህም የዓለም ፖለቲካና መንግስታዊ ምስረታ በእጅጉ ተቀያይሯል። በዚህም የካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝም እና ሌሎች የፖለቲካ ጎራዎች አሰላለፍ ጎልቶ የወጣ ሲሆን፤ አገራት ላይም በርካታ ለውጦች መጥተዋል። ይሁንና ይህ ክስተት ምስራቅ አፍሪካን ባለመዳሰሱ የቀጣናው ፖለቲካ እንደነበር ሊቆይ ተገዷል።
አገራቱ ህገ መንግስት ከማውጣት በዘለለ የሕግ የበላይነትን እንዳልተገበሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ መሪዎች አገሪቱን እንደፈለጋቸው የሚዘውሩ እንጂ የዴሞክራሲ ስርዓትን አልገነቡም፤ ዜጎችም በጽኑ የሚያምኑባት አገር ባለመመስረታቸው የመገንጠል ጥያቄዎች፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች፣ የሃይማኖት ጦርነቶችና ሌሎች ክስተቶችን ለማስተናገድ ተገደዋል። ከዚህም በዘለለ በቅኝ ግዛት ወቅት የተተከለው ጠባሳ ቀጣናውን ወደ ኋላ ማስቀረቱን ጠቁመዋል። ይሁንና እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም ምስራቅ አፍሪካ በዓለም ላይ ከሚገኙ ስትራቴጂ ስፍራዎች ቀዳሚው በመሆኑ ሁሌም በእይታና ኃያላን አገራት ሽኩቻ ቀጣና ሆኗል።
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ውስጥ ያመለጧት ዕድሎችና በአሁኑ ወቅት ባለው ክስተት ምን መማር ይገባል በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ጋሻው አይፈራም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ በርካታ ዴሞክራሲ ስርዓትን መገንባት የሚያስችሉ ዕድሎች አጋጥሟት የነበረ ቢሆንም አልተጠቀመችም። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ለውጥ በአግባቡ መምራት ከተቻለ የተሻሉ ዕድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር