የመጀመሪያው የአማርኛ ታይፕራይተር ፈጣሪ-ኢንጅነር አያና ብሩ

ኢትዮጵያ የብዙ ታላላቅ ምሁራን አገር መሆንዋ የታወቀ ነው። ነገር ግን ታሪካቸው በአግባቡ ተፅፎ የተመዘገበው የጥቂቶቹ ብቻ ነው:: በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጰያውያን፤ ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ እሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ፣ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ምሁራን እንደ ነበሩ አይካድም።

የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ። በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ፤ ስለዚህ፣ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው። ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር አንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ስለዚህ ምሁር ማለት በልምድ፣ በትምህርትና በልዩ ልዩ መንገድ ያገኛቸውን ማስተዋሎችና ዕውቀት በሀሳብ መልክ ለኅብረተሰቡ የሚያቀርብ ሰው ነው። ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በዓለም መድረክ ላይ አዳዲስና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግኝቶችንና ፈጠራዎችን ይዞ ብቅ በማለት የበርካቶችን አንገብጋቢ ችግር የፈቱና ብዙዎችን በስራዎቻቸው ያስገረሙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ።

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልበሩም። በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው። ከእነዚህም ልሂቀን መካከል የመጀመሪያው የአማርኛ ታይፕራይተር ፈጣሪው ኢንጅነር አያና ብሩ አንዱ ናቸው።

ኢንጅነር አያና ብሩ ትውልድ እና እድገታቸው በወለጋ ነው። በወቅቱ በእንግሊዝ ኤምባሲ ሲሠሩ የነበሩት ታላቅ ወንድማቸው አቶ ዳባ ብሩ አያናን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት አስገቧቸው። የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በብቃት ያጠናቀቁት አያና ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ግብፅ ተላኩ። ከዚያም ወደ እንግሊዝ ሀገር በማቅናት ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ተመርቀዋል። እንግሊዝ ሀገር እያሉም ለሀገራቸው የሚጠቅም ሥራ ሲያልሙ የነበሩት ኢንጂነር አያና “ኦሊቬቲ” ከተባለ የጣሊያን ካምፓኒ ጋር ባደረጉት ምርምር የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር ማሽን ዲዛይን አዘጋጁ።

ይህን ዲዛይን ወደ ተግባር ለመቀየር እንግሊዝ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ቢሞክሩም “የአማርኛ ፊደል (ቋንቋ) የሚያገለግለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በመሆኑና ገበያ ስለማያስገኝ አያዋጣንም” የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። በምላሹ ተስፋ ያልቆረጡት ወጣቱ መሐንዲስ ዲዛይኑን ይዘው ወደ አሜሪካኖች ሲሄዱ አሜሪካኖቹ እንደሚሠሩላቸው ግን የአሜሪካ ዓርማ እንደሚታተምበት ነገሯቸው፤ ኢንጂነር አያናም በሥራቸው ላይ የኢትዮጵያ ዓርማ እንዲታተም ፍላጎት ቢኖራቸውም አማራጭ ስላልነበራቸው ፈቅደው ሁለት ታይፕራይተሮችን አሠርተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ማሽኑን ለንጉሡ በመስጠትም አገልግሎት ላይ እንዲውል አድርገዋል።

ግንቦት 1939 ዓ.ም የጽሑፍ መኪናዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ተፈቅዳ ጽሑፍ ታትሞባታል። ኢንጅነሩ የሠሯት የመጀመሪያዋ የአማርኛ ታይፕራይተር አሁንም በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ትገኛለች። ኢንጂነር አያና በዘመናቸው በዓለም ላይ የነበረው የፈጠራ ሥራ ለሀገራቸው ጥቅም እንዲውል ያደረጉ ትውልድ እና ዘመን ተሻጋሪ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ይህም ለሳቸው ዘመን እና ከዚያ በኋላ ለመጣው ትውልድም በሙያ ሀገርን ማገልገል ምን እንደሆነ ያሳዩበት ከመሆኑም ባሻገር ለዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር መሰረት የጣለ ነው።

በመቀጠልም በአውራ ጎዳና ኃላፊነት ተመድበው መሥራት ጀመሩ። በዚያ ሲያገለግሉም ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚወስደውን መንገድ እያጠናቀቁ እያሉ ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሀገራችንን ለመውረር እየገፋች መጣች። ከዚያም ሥራውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ወደ ማይጨው በመዝመት ከጠላት ጋር ተዋግተዋል። በማይጨው የነበረው የወገን ጦር ሲፈታም ወደ መሀል ሀገር በመመለስ የሽምቅ ውጊያን ማስተባበር ጀመሩ።

ንጉሡ ወደ ውጭ እንዲሄዱ ሲወሰንም ኢንጂነር አያናን አስጠርተው እሳቸው እንግሊዝኛ ቋንቋን ስለሚችሉ አብሯቸው እንዲሄዱ ጠይቀዋቸው ነበር፤ ኢንጂነር አያና ግን የንጉሡ መሄድ አስፈላጊ ከሆነ አርበኞቹን የሚያስተባብር አንድ ሁነኛ ሰው ትተው እንዲሄዱ፣ በእርሳቸው በኩል ግን ወደ ውጭ ከመሄድ እዚሁ ሀገር ውስጥ ሆነው አርበኞቹን ቢያስተባብሩ እንደሚመርጡ ተናግረው እዚሁ ቀሩ።

ጣሊያን አዲስ አበባን ሲቆጣጠርም ኢትዮጵያ የጣሊያንን አገዛዝ እንዳልተቀበለች የሚያጋልጡ መልዕክቶችን በማዘጋጀት ማሰራጨት እና ለአርበኞች መረጃን የማቀበል ሥራቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ግራዚያንን ለመግደል የተደረገውን ሙከራ በማቀናበር የተጠረጠሩት ኢንጅነር አያና፣ ጣሊያኖች በግራዚያኒ አማካኝነት፣ “አያናን አንገቱን ቆርጦ ለሚያመጣልን አሥር ሺህ ጠገራ እንከፍላለን” የሚል አዋጅ አስነገረች። ኢንጂነር አያና ግን ምንም ሳይፈሩ ወራሪውን መታገላቸውን ቀጠሉ።

በኋላም ወደ ጊምቢ ወለጋ ሄደው ሕዝቡን እየቀሰቀሱ አርበኞችን እያበረታቱ በዚያው ወደ ሱዳን ተሻገሩ። በሱዳንም ከንጉሡ እየተጻጻፉ የማበረታቻ መልዕክቶችን ለአርበኞች ማድረሳቸውን ቀጠሉ። የጣሊያንን ግፍ ሲቃወሙ ከነበሩት ሲልቪያ ፓንክረስት ጋርም ተገናኝተው የጣሊያንን ግፍ በጋዜጦች በማሳተም ለዓለም ማኅበረሰብ ማጋለጣቸውን ቀጠሉ። ወደ ጊምቢ በመመለስ አርበኞችን በመቀስቀስ ላይ እያሉ አንዱ አብሮ አደግ ወዳጃቸው ወደ ቤቱ ወስዶ ከደበቃቸው በኋላ በጎን ለጠላት ጠቁሞ አስያዛቸው፤ ጠላትም በጊምቢ ከተማ ገበያ ላይ በጥይት ደብድቦ ገደላቸው።

ሀገርን ማገልገል ልማዳቸው የሆነው ኢንጂነር አያና ቤተሰብ፤ ልጃቸው ኮሎኔል አበራ አያና በደርግ ዘመነ መንግሠት የአዲስ አበባ ፖሊሰ ዋና አዛዥ ሆነው ሠርተዋል። ኮሎኔል አበራ በኃላፊነት ባገለገሉበት ወቅት የማረሚያ ቤት ሥርዓቶችን እና የሕግ ታራሚዎችን አያያዝ የቀየሩ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ታሪካቸው ያሳያል። አንድ በሕግ ጥላ ስር ያለ ሰው የማረሚያ ጊዜውን አጠናቆ ወደ ሕብረተሰቡ ሲመለስ በአዕምሮም፣ በአካልም፣ በክህሎትም ጎልብቶ ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆን የተለያዩ ሙያዎች ሥልጠና እና የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴዎች በወህኒ ቤቶች ውስጥ ተጠናክሮ እንዲሰጥ ያደረጉ ናቸው።

ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያውያን የእንግሊዘኛውን የታይፕራይተር ወይም የጽሕፈት መሣሪያ አጠቃቀም ከተረዱ ወዲህ መሣሪያውን ለአማርኛ ቀለሞች እንዲያገለግል ለ85 ዓመታት ቢታገሉም ሳይሳካ ቀርቷል። በመካከሉ ከተደረጉት የተለያዩ ሙከራዎች መካከል የኢንጂነር አያና ሥራ አንዱ ነበር።

ዋናውም ችግር የመሣሪያው መርገጫዎች በአማርኛ ፊደላት መብዛት የተነሳ በቂ ስላልነበሩ ፊደላቱን ከተለያዩ መርገጫዎች በመሰብሰብ በመቀጣጠል የሚያስከትብ ዘዴ ከዓመታት በኋላ አቀረቡ። በእዚህ ዘዴ “ሀ” ከአንድ መርገጫ ከተከተበ በኋላ “ሁ” ፊደል የሚከተበው “ሀ” ጎን የመቀነስ ምልክትን ወይም “-” በማስቀመጥ ነበር።

ይኼንኑ የመቀነስ ምልክት “ለ”፣ “ሐ”፣ “መ” እና የመሳሰሉት ጎን በማስቀመጥ “ሁ”፣ “ሉ”፣ “ሑ”፣ “ሙ” ስለሚመስሉ አንዱኑ መቀጠያ ለተለያዩ የፈጠራ ቁርጥራጮች እንዲሆን ተደረገ። እንደነ “ሹ” የመሳስሉትን በቅጥልጥል ለመክተብ ከ“ሰ” እና የመቀነስ ምልክት የተሠራውን “ሱ” ፊደል በሌላ መርገጫ ቀደም ብሎ ወይም ወደኋላ መልሶ ሌላ ረዥም መስመር ከሌላ መርገጫ ከ“ሰ” አናት ላይ በማስቀመጥ ይሠራ ነበር።

ይህ የቅጥልጥል ፊደል አሠራር መኖር የአማርኛ ባልሆኑ (በእንግሊዘኛ) ፊደሎች ቀለሞቹን በመሳል የቢሮ ሥራ መሥራት ስለተቻለ ኢንጂነር አያና ብሩ፤ ለኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ ናቸው። የኢንጂነር አያና መሣሪያ ባይኖር ኖሮ የቢሮ ጽሑፎችን በእጅ ጽሑፍ ተጠቅሞ መቀጠል የማይታሰብ በመሆኑ ኢንጂነር አያና ብሩ ለአማርኛ እድገት ክፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል።

ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሊቆች፣ ሚኒስትሮችና ደራስያን የእንግሊዝኛውን የታይፕ መጻፊያ ለአማርኛ መክተቢያ እንዲያገለግል ወደ ሰማንያ ዓመታት ሲመራመሩ ቆይተው፤ ባይሳካላቸውም ኢንጂነር አያና ብሩ ጥረቶቻቸውን የአማርኛ ታይፕራይተር በመሥራት አሳክተዋል።

የግዕዝ ኮምፒዩተራይዜሽን ፈር ቀዳጅ የሆኑት ኢንጂነር አያና ብሩ የኮምፒዩተርን ኃይል እና እምቅ አቅም የተገነዘቡ እና ከዘመኑ በፊት የነበሩ ባለራዕይ ናቸው። ኢንጂነር አያና ብሩ በፈር ቀዳጅነት የጀመሩት ጥረትና ፈጠራ ባይኖር ኖሮ የአማርኛና ግዕዝ ፊደላትን የኮምፒዩተር ፅሁፍ ማዘመን፣ በዩኒኮድ ደረጃ እንዲመደብ ማድረግና አሁን ያለውን በኮምፒዩተሮችና ኢንተርኔት ላይ አማርኛንም ሆነ በግዕዝ ፊደላት የሚፃፉ ቁንቋዎችን በቀላሉ ለመተየብም ሆነ ለማንበብ የሚያስችል መንገድ ላይ መድረስ ባልተቻለ ነበር።

በቅርቡ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው ስትራይድ ኢትዮጵያ ኤክስፖ የተጠናቀቀው (STRIDE Ethiopia 2024 Expo) በተለያዩ ዘርፎች የሕይወት ዘመን ሽልማቶች በመስጠት ነበር፤ በሕይወት ዘመን አበርክቶ ሽልማት ምድብ በየዘርፉ ለሀገራቸው ዘመን ተሻጋሪ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ኢትዮጵያውያን የሕይወት ዘመን ሽልማቶች ተሰጥተዋል። ተሸላሚ ከነበሩት ግለሰቦች መካከልም ዛሬ ታሪካቸውን በአጭሩ ያስነበብናችሁ ኢንጂነር አያና ብሩ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነበሩ።

ኢንጂነር አያና ብሩ የመጀመሪያውን የአማርኛ ታይፕራይተር የሠሩ በመሆናቸው “የኢትዮጵያ ታይፖግራፊ አባት” በሚል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሕይወት ዘመን ሽልማት ሰጥቷቸዋል። አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ደማቅ ልጆች አሏት። በኪነ ጥበቡ፣ በማኅበራዊውና በኢኮኖሚው፣ በቴክኖሎጂ በፖለቲካውና በሌሎች የሕይወት መስኮች የጥበብን የተካኑ ቁጥራቸው ብዙ ነው። ለእነዚህ የሀገር ካስማ ግለሰቦች እውቅና መስጠት መቀጠል ያለበትና ይበል የሚያሰኝ ነው።

እኛም በዚህ ለህዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ እውቅና የመጀመሪያውን የአማርኛ መጻፊያ ወይም ታይፕራይታር ፈጣሪ ኢንጂነር አያና ብሩን አመሰገንን። ሰላም!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You