እውን ሀገራቸውን ይወዳሉ?

‹‹ጃፓን እንደምን ሰለጠነች? ዱባይ እንደምን ሰለጠነች? አሜሪካ እንደምን ሰለጠነች?›› የሚሉ በመጽሐፍ መልክም ሆነ በመጣጥፍ መልክ ወይም በመድረክ ላይ የሚነገሩ ብዙ ሰርቶ ማሳያዎች (ሞዴሎች) አሉ። የሥልጣኔ ማማ ላይ ናቸው የተባሉት ሀገራት እንዴት እንደሰለጠኑ ይነገር ቢባል ከአንድ መጽሐፍ በላይ ዝርዝር ይወጣዋል። በአጭሩ በአንድ ዓረፍተ ነገር ሲገለጽ ግን፤ ከቁስ አካል በፊት በአዕምሮ ስለሰለጠኑ ነው። ምክንያቱም ቁስ አካልን የሚሰራው አዕምሮ ነው። የተሰራውን እንዳይበላሽ የሚያደርገው የሰለጠነ አዕምሮ ሲኖር ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያውያን ከቁስ አካል ሥልጣኔ በፊት የአስተሳሰብ ሥልጣኔ ላይ ልንረባረብ ይገባል።

ሰሞኑን ‹‹ኢትዮጵያ እየመከረች ነው›› በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው። በምክክሩም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳቸውን እየሰጡ አጀንዳ እየተለየ ነው። ምክክር በሃሳብ ለመከራከር አንዱ የመሰልጠን ምልክት ነውና አንድ እርምጃ ጀምረናል ማለት ነው።

እዚህ ላይ ግን አንድ በትልቁ የምታዘበው ነገር አለ። ኢትዮጵያን ሰላምና ዴሞክራሲ ያላት ሀገር ለማድረግ፣ የሰለጠነች ሀገር ለማድረግ፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች ለማድረግ ከድሮ ጀምሮ ዛሬ ድረስ እየመሩ ያሉ መንግሥታትን የሚቃወሙ ኃይሎች አሉ። ይህንን ስል የግድ በፓርቲ ደረጃ ያሉትን ብቻ አይደለም። በግለሰብ ደረጃ በተለይም በዘመኑ የዲጂታል ትግል ‹‹አክቲቪስት›› የሚባሉትን የበለጠ ይመለክታል፤ ያም ሆኖ ግን ትዝብቴ በሕጋዊ ፓርቲ ውስጥ ያሉትንም ይመለከታል።

የምር እነዚህ እየታገሉ ያሉ ወገኖች ሀገራቸውን ይወዳሉ? የሀገር ፍቅር አላቸው? የሀገር ፍቅር ማለትስ ምን ማለት ነው?

ፍቅር ማለት ከራስ በላይ ለሚወዱት ማሰብ ነው። የሀገር ፍቅር ሲሆን ደግሞ ከፆታዊ ፍቅርም ሆነ ከቤተሰብ ፍቅር በላይ ነው፤ እሱ እንኳን ቢቀር ቢያንስ ለግለሰቦች ካለን ፍቅር ማነስ የለበትም። ትክክለኛ ፍቅር ሲኖር ከራስ በላይ የሚታሰበው ለተፈቀረው አካል ነው።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን እየታገልን ነው የሚሉ አካላት የሀገር ፍቅር ያላቸው አይመስልም። ምክንያቱም ብዙዎቹ የራሳቸው የግል ክብር የሚበልጥባቸው ናቸው። መጥፎ ነገርም ቢሆን እነርሱ የተናገሩት ይሳካ ዘንድ የሚጥሩ ናቸው። ‹‹እገሌ ተናግሮ ነበር›› ለመባል የሚሰሩ ናቸው። ለዚህም ነው በጥላቻ የተተበተቡ የሆኑት። አንድ ምናባዊ ምሳሌ እንጠቀም።

ከበደ የተባለ ሰው ‹‹አንድን የፖለቲካ ቡድን ከምድረ ገጽ መጥፋት አለበት›› አለ እንበል። በኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ዓውድ የዚህ ሰው ጥረት እሱ የተናገረው ይሳካ ዘንድ ጥረት ማድረግ ብቻ ነው። ከዚያ ‹‹መጥፋት አለበት!›› ካለው ቡድን ጋር ድርድር ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደርሶ ሰላም ተፈጠረ እንበል። ይህ ሰው እንኳንም ሰላም ሆነ ከማለት ይልቅ እሱ ፎክሮ የነበረው ፉከራ ስላልተሳካ ብቻ የሰላም ስምምነቱ ትክክል እንዳልሆነ አድርጎ ይከራከራል ማለት ነው።

ይህ ሰው ፈሪ ነው ማለት ነው። ‹‹እንዲህ ብለህ ነበር፣ ያኔ ፎክረህ ነበር…›› ላለመባል ሲል የሚደረገው የሰላም ስምምነት ትክክል አይደለም ብሎ ይከራከራል። ይህ ሰው ከሚሊዮኖች ሕይወት ይልቅ የእርሱ የግል ክብር ይበልጥበታል። የእርሱ የግል ክብር ማለት በእርሱ የግል ፍላጎት መጥፋት አለበት ያለው ቡድን ሲጠፋ ነው። እርሱ የተናገረው ነገር ይሳካ እንጂ ሀገሪቱ ብትፈራርስ አያሳስበውም። ይህ እልም ያለ የፈሪ ሰዎች አቋም ነው።

ጀግና ግን ከራሱ በላይ ለሌሎች ነው የሚኖረው፤ አፍቃሪም ከራሱ በላይ ላፈቀረው አካል ነው የሚኖረው። ሀገሬን እውዳለሁ የሚል ሰው ከራሱ የግል ፍላጎት ይልቅ የሕዝቦች ሰላም ሊያሳስበው ይገባል። ስለዚህ አንድ ጀግና ሀገር ወዳድ የሚከተለውን ያደርጋል ማለት ነው።

በወቅቱ በነበረው አቋም ወይም በሆነ ስሜት ወይም በሆነ አረዳድ ‹‹እገሌ›› የሚባል ቡድን መጥፋት አለበት አለ እንበል። በዚህም ምክንያት ጦርነት ተፈጠረ እንበል። የተፈጠረው ጦርነት ብዙዎችን እያረገፈ ነው፣ ንብረት እየወደመ ነው። ስለዚህ ይህ ጀግና ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ልዋረድ፣ እኔ ልሰደብ፣ እኔ መሳቂያ ልሁን ብሎ በማሰብ ሕዝቡን ያድናል። ይህን የምለው በግለሰቦች ደረጃ ያለውን ነው። በቡድን (በፓርቲ) ደረጃ ሲሆን ደግሞ ሕዝብን ለማዳን ፖለቲካዊ ውሳኔ ይወሰናል ማለት ነው። ይህ እንደ ፍርሀት ሳይሆን እንደ ጀግንነት መታየት አለበት። ምክንያቱም ጀግንነት ማለት ከራስ የግል ክብር በላይ ለሌሎች ማሰብ ነው።

ይህን ምናባዊ ምሳሌ የጠቀስኩት በገሃዱ ዓለም የሚታየው የዚህ ቀጥተኛ ነፀብራቅ ስለሆነ ነው። ትልልቅ ፓርቲዎችን ይመሩ የነበሩ፣ ዕድሉን ቢያገኙ ሀገር ሊመሩ የነበሩ፣ ተደራራቢ የትምህርት ደረጃ ያላቸው… ትልልቅ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ባላቸው ልዩነት ምክንያት ጥፋት ሲመኙ ይሰማል። እነርሱ በግለሰብ ደረጃ የጠሉት ሰው ይጎዳ ዘንድ ሀገራዊ ጥፋትን ሲደግፉ ይታያል። ለዚያ በግል ጥላቻ ብቻ ለጠሉት ሰው ሲሉ ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን ጭምር ሊቃወሙ ይችላሉ።

አንድ 20 ዓመት በላይ በተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ታዋቂ የሀገራችን ፖለቲከኛ በአንድ የቴሌቪዥን መዝናኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው አንድ የሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በአሁኑ ጊዜ የሚመራውን ተቋም ሲወቅሱ ሰማሁ። ይህ የሚወቅሱት ሰው ደግሞ በጻፈው መጽሐፍ እርሳቸውን ይወቅሳል። ይህን የግለሰብ ጉዳይ ወደ ተቋም ወሰዱት ማለት ነው። የተቋሙን ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ በተቋሙ እየተሰሩ ያሉ ነገሮችን መተቸት ሲገባቸው የግል ቂም መሆኑን በሚያስነቃ ሁኔታ ይወቅሳሉ።

እነዚህ ችግሮች የሚፈጠሩት ከሀገር በላይ የግል ወይም የቡድን ጥቅምን በማስቀደም ነው። እኔ የተናገርኩት ውድቅ ከሚሆን እኔ የተናገርኩት ተተግብሮ የጠፋው ይጥፋ ከሚል ስሜት ነው። ጀግና እና ሀገር ወዳድ የሆነ ሰው ግን ከራሱ የግል ክብር ይልቅ እሱ ተዋርዶ (መዋረድ ከተባለ) የሕዝቡን ሰላም ያስቀድማል።

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ እንዲህ አይነት ልማዶቻችንን የሚቀርፍ ባህል መፍጠር አለበት። የሀገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሰዎች፣ የሀገር ፍቅር አለን የሚሉ ሰዎች ከግልና ከቡድን ፍላጎት ሊላቀቁ ይገባል። እንዲህ ብለን ስለነበር ‹‹ምነው ተንሸራተታችሁ?›› እንባላለን የሚል ግትር አቋም መያዝ ጀግንነት ሳይሆን ፈሪነት ነው። ነገሮች በተለያዩ አስቻይ ሁኔታዎችና በነባራዊ ዓውድ ይቀያየራሉ። ይህን መረዳትና ለሀገርና ለሕዝብ በሚጠቅም መንገድ አቋምን መቀየር ዘመናዊነትና አርቆ አስተዋይነት እንጂ ፍርሀት አይደለም። አለበለዚያ የግል ክብር ፍለጋ ነው የሚሆነው። የግል ክብርን ለማስጠበቅ ሲባል ሀገርና ሕዝብን የሚጎዳ ነገር ላይ ግትር የሚሉ ግን እውን ሀገራቸውን ይወዳሉ?

ዋለልኝ አየለ

 አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2016 ዓ.ም

Recommended For You