አዲስ አበባ፡- ለውጡን እየመራ ያለው አመራር በኢትዮጵያ ታሪክ ተገኝተው ካመለጡ ወርቃማ የፖለቲካ ዕድሎች ትምህርት በመውሰድ የተንዣበበውን ችግር መፍታት እንደሚገባው ተጠቆመ፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጋሻው አይፈራም፤ በመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ አማካኝነት ሲካሄድ በቆየው የውይይት መድረክ ላይ ባቀረቡት ጥናት፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት መንግስታት የታሪክና የፖለቲካ አስተዳደሩ ውስጥ የተገኙና ያመለጡ እድሎች አሁን የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ ትምህርት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር ጋሻው በጥናታቸው እንዳሰፈሩት፤ በፖለቲካና ኢኮኖሚ በተለይም ከእኩልነትና ፍትሐዊነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የ1952 ዓ.ም የኢትዮ ኤርትራ ፌዴሬሽን፣ የ1960ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት፣ የ1974ዓ.ም አብዮትና የ2005 ዓ.ም ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
በየአጋጣሚዎቹ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ ሲገባ እድሎቹ መክነዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ሌላኛው አዲስ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ ተስፋው እንዳይጨልም መንግስትም ሆነ ሌሎች አካላት ካለፉት ስህተቶች መማር ይኖርባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግሮች የሚታዩበት መንገድ የቅኝ ግዛት፣ የብሄር ጭቆና እና የአገር ግንባታ እሳቤዎች መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህም በመሠረታዊነት ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ የማይታረቅ ህልም ይዘው የሚንቀሳቀሱና የልሂቃን እሳቤ በመሆን ማኅበረሰቡን በማያሳትፍ መልኩ ሲዘወተሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም በኢ ትዮጵያ ያለው የልሂቃን የበላይነት ፈር እንዲኖረው ካለፉት ስህተቶች ትምህርት መውሰድ የመንግስትና ባለ ድርሻ አካላት የቤት ሥራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ በመልካም አጋጣሚዎች የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ቢኖሩም ያጋጠሙት ውድቀቶች በምን መንገድ ታጡ የሚለውን መገምገም እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር ጋሻው፤ የፖለቲካ ሽግግሩና የዴሞክራሲ ሂደቱ የአገሪቷን ተቋማት በለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት የፖለቲካውን ምህዳር ማስፋት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የውይይት መድረኩ ‹‹ልማታዊ ዴሞ ክራሲያዊ መንግስትና የለውጥ አመራር›› በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሁለት ቀናት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ማዕከል ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
አዲሱ ገረመው