አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የፀረ ሙስና ትግል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና አሁን ካለው በላቀ ደረጃ ማደግ እንዳለበት የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።
የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ኮሚሽኑ ከሕዝብ ተወካዮች የመንግስት ተጠሪ ፅሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ለምክር ቤቱ አመራሮችና አባላት ትናንት ስልጠና በሰጠበት ወቅት እንደገለፁት፤ የፀረ ሙስና ተቋሙ አቅምና ጉልበት የፓርላማ አባላቱና ህዝቡ በመሆናቸው ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርባቸዋል።
ምክር ቤቱም የሕዝቡን ድጋፍ የሚጠይቁ ችግሮች በማንሳት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን የተባበሩት መንግስታት የፀረ ሙስና ስምምነቶች መሰረት አድርጎ ተገቢውን መረጃ በመስጠት፣ በሙሉ አቅም በመሳተፍና ተቋማት ግዴታቸውን እንደ አገር ለመወጣት የሚያስችል አሰራር መፍጠር እንደሚኖርበት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ጨምሮ የፍትህ አካላትን በማደራጀት የፀረ ሙስና ትግሉን የሚያጠናክሩበት ሁኔታ እንዳለ የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ረገድ የተጀመረ ሂደት ቢኖርም የፀረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂ ሁሉንም ተቋማት የሚመለከት ስለሆነ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተቋማት በኃላፊነት መንፈስ እንዲሳተፉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
‹‹የክስ ምርመራ ስራችን በፀረ ሙስና ካልተደገፈ ውጤታማ ይሆናል ብለን አንገምትም›› ያሉት አቶ አየልኝ፤ ሁሉም ተቋማት የሚሰጣቸውን ድጋፍና እገዛ ተቀብለው የሚሰሩበት፣ ካልሰሩ ደግሞ የሚያስጠይቃቸው እንዲሆን በምክር ቤቱ ግልፅ አቅጣጫ መቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሆን መደረጉን አስታውሰዋል። ይህም የሆነው ኮሚሽኑ ገለልተኛ ሆኖ አጠቃላይ በተቋማት የሚታየው የስነ ምግባርና የሙስና ሁኔታ ላይ እያስተማረና ርምጃ መውሰድ በሚገባው ላይ ርምጃ እያስወሰደ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር ቢሰራ ሰፊ ሕዝብ ማንቀሳቀስ ይችላል በሚል እምነት መሆኑን አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ የኮሚሽኑ አዋጆች ተስተካክለው በሚመጡበት ወቅት በዝርዝር ተመልክቶ በተሟላ ሁኔታ ስራውን ማከናወን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት የተናገሩት አፈጉባዔው፤ ኮሚሽኑን ብቻ ሳይሆን በጋራ የሚሰሩ ተቋማትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። ይህንን ታሳቢ ያደረገ ስራም ከምክር ቤቱ እንደሚጠበቅ አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
ቦጋለ አበበ