የዘመናትን መልክ ለማሳየት በጽሑፍ ያሉ ሰነዶች ድርሻቸው ከፍተኛ ነው:: አዲስ ዘመን ጋዜጣም ባለፉት ሰማንያ ሦስት ዓመታት የየዘመኑን መልኮች ፍንትው አድርጎ ለአዳዲስ ትውልድ በማሳየት ዛሬ ላይ ደርሷል:: ቆየት ካሉ ዓመታት የተለያዩ ዜናዎች እስከ አዝናኝ ጉዳዮች በጋዜጣው የተዳሰሱ አንዳንድ ፅሁፎችን ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰን በጥቂቱ እናስታውስ::
ክፍያው በዝቷል
ለግሼ ወረዳ የሚሰጠውን ርዳታ የሚያመላልሱት የጭነት መኪኖች በዚያ ጠመዝማዛ መንገድ ከጭነቱ ላይ ሰው ጭነው መሔዳቸው ለእርዳታ እስከሆነ ድረስ ይደገፋል ነገር ግን ለጫኑበት ዋጋ የሚቀበሉት ገንዘብ አለቅጥ የበዛ ነው::
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጥር 29/77 ወደ ራቤል በሚጓዝበት ወቅት ሹፌርና ረዳት የተመኑትን ስድስት ብር መክፈል ስላልቻለ መሀል መንገድ ላይ እንዲወርድ ሆነ ለዚያውም አራት ብር ከፍሏል:: የወረደበት ቦታ ከተሳፈረበት በግምት 45 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከዚያ በኋላ በእግሩ ከሄደ ከአምስት ሰዓት በላይ ይወስድበታል:: አንዳንዶቻችን ለመለመን ብንሞክር እኛም እንዳንወርድ አስጠነቀቀን:: ምነው ትንሽ ዋጋው አልበዛም ብዬ ረዳቱን ብጠይቀው ‹‹ ያልፈለገ በእግሩ መሔድ ይችላል::›› አለኝ:: እስከተቻለ ድረስ ማሳፈሩን ጥሩ ሆኖ ሳለ በመንግሥት ርዳታ መኪና ለተወሰኑ ሰዎች ጥቅም 98 ኪ ሜትር ስድስት ብር ማስከፈል እጅግ ይቆጠቁጣልና ጉዳዩ የሚመለከተው ከፍል አስቸኳይ መፍትሄ ይፈልግለት::
– እሸቴ አሰፋ
(አዲስ ዘመን መጋቢት 05 ቀን 1977 ዓ.ም)
ደን ጨፍጭፈው ያቃጠሉ ተቀጡ
በኢሊባቦር ክፍለ ሀገር በደዴሳ ወረዳ ውስጥ ደን ጨፍጭፈው በእሳት ባቃጠሉ ሦስት ግለሰቦች ላይ የወረዳው ፍ/ቤት በድምሩ አንድ ሺ ብር እንዲቀጡ በይኖባቸዋል::
ሙሉነህ ለማ፤ አስረስ ለማና ሸምሱ አባ ቡልጎ በተባሉት ግለሰቦች ላይ ቅጣቱ ሊወሰንባቸው የቻለው አንደኛው ከሳሽ የጥንስስ አምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሁለተኛውና ሶስተኛው ደግሞ የቀበሌ ገበሬ ማሕበር የቁጥጥርና የአኢወማ ኮሚቴ ሊቃነ መናብርት ሆነው ሳለ መንግሥት ስለደን ያወጣውን ሕግ በመተላለፍ ጭፍጨፋ በማካሄዳቸውና በማቃጠላቸው መሆኑ ታውቋል::
በዚሁ መሠረት ፍርድ ቤቱ የእያንዳንዳቸውን ጥፋት ከመረመረ በኋላ በአንደኛው ተከሳሽ ላይ 500 ብር መቀጫ ወይም ስድስት ወር እስራት በሁለተኛው ተከሳሽ ላይ 300 ብር መቀጫ ወይም አራት ወር እስራት በሶስተኛው ተከሳሽ ላይ ደግሞ 200 ብር መቀጫ ወይም ሶስት ወር እስራት ወስኖባቸዋል::
(አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 1977)
የቴሌቪዥኖች ጉዳይ ከአዘጋጅዋ ፤
የቴሌቪዥን አገልግሎት በሀገራችን መሰጠት ከጀመረ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖታል:: ሆኖም እስከ ጥቂት ጊዜ ድረስ የስርጭቱ አገልግሎት በጥቂት ከተሞች ብቻ የተወሰነ ነበር:: በአሁኑ ወቅት ግን በአብዛኛው የሀገሪቱ ከተሞች እየተዳረሰ ነው:: ስለዚህም ዛሬ አብዛኛው ሕዝባዊ ድርጅቶች ቴሌቪዥን እየገዙ ሕዝብ ወቅታዊ ነገሮችን እንዲከታተል፤ ትምህርት እንዲያገኝ፤ እንዲሁም እንዲዝናና ለማድረግ በአመቺ ቦታዎች ላይ በማዘጋጀት ግልጋሎት እየሰጡ ናቸው:: ለዚህም የሰበታ ከተማ አጠቃላይ ም/ቤት ተግባር እንደምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል::
በአንጻሩ ግን በሕዝብ ገንዘብ ተገዝተው ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ያለባቸው ቴሌቪዥኖች አንድ ሰሞን በወረት እንዳሉ ለሕዝብ በተከታታይ ቀናት ማገልገል ጀምረው አናሳይም እስከማለት የደረሱ መኖራቸውን ከአንዳንድ ጠቋሚዎች ለመረዳት ችለናል::
ምናልባት ሕዝባዊ ድርጅቶች ለቴሌቪዥኖች በጥንቃቄ መያዝ በማሰብ ያደረጉት ከሆነ መልካም ነው:: ግን ለቴሌቪዥኑ ደኅንነት አንድ ሰው በሰዓቱ ከፍቶና ዘግቶ ፕሮግራሙን ለሚከታተለው ኗሪ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ረገድ መተባበር ይገባቸዋል እንላለን::
(አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 19 77 ዓ.ም)
የጆሮ ኩክ ምስጢር
ሁላችንም ብንሆን አብዛኞቻችን እንደሰማነው ወይንም ከመጽሐፍ አንብበን እንደተረዳነው ጆሮ ውስጥ የሚገኝ ኩክ ወደ ውስጥ የሚገባ አቧራ ወይንም ሌሎች ባዕድ ነገሮችን እየጠበቀ በማስቀረት ጆሮአችንን ከአደጋ ይከላከላል:: ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጆሮ ኩክ ሌላ ምስጢር ይዞ ተገኝቶአል:: የሶቪየት ሳይንቲስቶች ባደረጉት ጥናት መሠረት በጆሮ ውስጥ የሚገኘው ኩክ ዓይነት የሰዎች ዘርን አመጣጥ ለማወቅና የዘራቸውንም ዓይነት ከየትኛው እንደሆኑ ለመመደብ እንደሚረዳ ደርሰውበታል::
በሳይንቲስቶቹ ጥናት መሠረት ኩክን ደረቅና እርጥብ በማለት የመደቡት ሲሆን ለምሳሌ የሞንጎሎይድ ዝርያ የሆኑ ሕዝቦች (ጃፓን ኮርያ ቻይና ወ–ዘ-ተ) በጆሮአቸው ውስጥ ያለው የኩክ ዓይነት በአውስትራሊያና በአፍሪካ ሕዝቦች ውስጥ ሊገኝ ችሏል:: የዚህም ጥናት ዋና ዓላማ የሰዎችን የተለያዩ በሽታዎችን የመቋቋምና ያለመቋቋም ባህሪ ለማጥናት እንደሆነም ሳይንቲስቶቹ ገልፀዋል::
-ዳምጠው ዘገርጂ
(አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 1980 ዓ.ም)
አወይ ሞኝ መሆን!
ከንጉሤ አክሊሉ (ሎተሪ)
ለሥራ ጉብኝት – ፈረንጅ አገር ሄጄ
ከሱቅ ውስጥ አይቼ – ሙሉ ልብስ ወድጄ
ትንሽ ቀረብ ብዬ – ዋጋውን ባስተውለው
ሰባት ከሃምሳ ነው – እንቅጩን የሚለው
በጉልህ ተጽፎ – ለዓይን የሚነበበው::
በሰባት ከሃምሳ – ሙሉ ልብስ አግኝቼ
አጋጣሚው ገርሞኝ – በጣም ተደስቼ
ገብቼ ለካሁት ከቦታው አንስቼ::
ግና ይህን ስታይ – ፈረንጅቱ ጮኸች
ገጿን ሦስት ጊዜ – ደጋግማ አማተበች::
እኔም በሷ አድራጎት – በጣሙን ደንግጬ
‹‹ኃትስ ሮንግ›› ብዬብል – ዓይኖቼን አፍጥጬ
እንደው ዝም ብትለኝ ፣መላው ቢጠፋብኝ
ምክንያቱን ለማወቅ – ልቤ ገፋፋኝ::
ሌላ አንድ ሰው መጥቶ – ተጠግቶ አወራት
በገዛ ቋንቋዋ – ደጋግሞ አናገራት::
ስለኔም አድራጎት – ለካስ ነግሯት ኖሮ
ገልመጥ አደረገኝ – ግንባሩን ቆጣጥሮ
በእንግሊዝኛ ቋንቋ – ጠየቀኝ በአንክሮ::
የደረሰብኝን በግልጽ – ሳጫውተው
ምክንያቱን እንጃ! – ሳቅ አንከተከተው
ለካስ የገባሁት – ከልብስ ሱቅ ሳይሆን
ላውንደሪ ቤት ነው – አወይ ሞኝ መሆን!
(አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 1980 ዓ.ም)
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2016 ዓ.ም