አዲስ አበባ፡- የቲቪ በሽታን እንዲመረ ምሩ ስልጠና የወሰዱ ዓይጦች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እያከናወኑ በመሆኑ ምስጋና ቀረበላቸው። ምስጋናውን ያቀረበው በጤና ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደረው አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ነው።
የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ገነቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ዓይጦቹ የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡ እያከናወኑት ሲሆን ይህም በህክምናው ላይ ትልቅ እምርታ እንደሚያመጣ ተስፋ አድርገዋል። በተለይም ደግሞ በአክታ የቲቢ በሽታን በመመርመር ረገድ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ነው።
አይጦቹ በላብራቶሪ ውስጥ በማይክሮስኮፕ በመታገዝ ከሚደረገው ምርመራ ጋር የተቀራረበ ውጤት እየተናገሩ ሲሆን፤ 90 ከመቶ የሚሆነውን ውጤት በትክክል መለየት ችለዋል፤ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ አገላለፅ፤ ዓይጦቹም ለዚህ ምርምር ብቻ የሰለጠኑና የቲቢ በሽታን በማሽተት የሚለዩ ናቸው። ዝርያቸውም አፍሪካዊ ሲሆኑ፤ ላብራቶሪ ውስጥ የተዳቀሉ ናቸው። ይህንንም የሚሰራው በታንዛኒያ የሚገኝ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ተባባሪ ድርጅት ነው። ስልጠናው ከፍተኛ ምርምርና ሳይንስ የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሙሉ ስልጠናው የወሰዱትም በታንዛኒያ አገር መሆኑ ተገልጿል።
እንደ ዶክተር አበበ ገለፃ፤ ዓይጦቹ በተለመደው መልኩ ምርምር የሚደረግባቸው ሳይሆኑ የቲቢ በሽታን በማሽተት የሚለዩና የሚመረምሩ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በምርምር ተቋሙ ውስጥ 15 ዓይጦች ያሉ ሲሆን፤ ልዩ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። አንዷን አይጥ ለማሰልጠንም በሺዎች የሚቆጠር ብር ወጪ ይደረጋል።
አሁን በሥራ ላይ ያሉ ዓይጦችም በሚቀጥሉት ዓመታ በርካታ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ተስፋ ተደርጎባቸዋል። ለአይጦቹ ሲባል በተጠና መንገድ የተቀመመ በእጅጉ የተመጣጣነ ምግብ ከውጭ አገር የሚመጣ ሲሆን፤ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮትና የመሳሳሉ ምግቦች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥንቃቄ ይዘጋጅላቸዋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ አሁን ምርምር ላይ የሚገኙት አይጦች እስከ 10 ዓመት ድረስ የሚቆዩ ሲሆን፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው።
አልፎ አልፎም ሥራቸውን በላቀ ሁኔታ የሚወጡ ዓይጦች ማበረታቻ እየተደረገላቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
ዓይጦች በሌሎች ዓለማት የተቀበረ ፈንጅ በመለየትና በማምከን ረገድ የተዋጣላቸው ሲሆኑ፤ ካምቦዳውያን እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ዓይጦችን ለዚሁ ተግባር በሰፊው ይጠቀሙባቸው ነበር።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር