“ፍርደኞቹ ራሳቸው በፖሊሶች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያካሄዱ ነው” – ጠቅላይ አቃቤ ህግ
አዲስ አበባ፦ በማረሚያ ቤት፣ በቀጠሮና ማረፊያ ቤት የሚገኙ ፍርደኞች ሰብአዊ መብት ጥሰት ድሮ ከነበረው እየጨመረ እንደሆነ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ደግሞ ፍርደኞቹ ራሳቸው በፖሊሶች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያካሄዱ ነው ሲል አመለከተ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የ2011 በጀት አመት የ11 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡
ሪፖርቱን መሰረት አድርገው የምክር ቤቱ አባላት እንዳሉት፤ ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በሪፖርቱ የታራሚዎች አያያዝ እየተሻሻለ ነው ብሎ ቢያቀርብም አባላቱ ግን በማረሚያ ቤት ፣በቀጠሮና ማረፊያ ቤት የሚገኙ ፍርደኞች አያያዝ ምንም የተሻሻለ ነገር አለመኖሩንና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እየጨመረ እንደመጣ የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ የመጣብኝን ክስ አልቀበልም እንደውም ታራሚዎቹ ራሳቸው በፖሊሶች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እያካሄዱ መሆኑን ገልጿል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለመስክ ጉብኝት በማረሚያ ቤቱ በሄዱበት ጊዜ ያዩዋቸው ብለው ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል ታራሚዎች ሙቀት በበዛበት ክፍል ውስጥ መኖራቸው፣ በታመሙ ሰአት በጊዜ ወደ ህክምና አለመወሰዳቸው፣ የመፀዳጃ ቤት ችግር ለአብነት ካቀረቧቸው መካከል ዋንኞቹ ናቸው፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ታራሚዎች የተለየ መብት ያላቸው ይመስል ሁሉም ማረፊያ ቤት ያለ ሰው መለቀቅ አለበት የሚል እሳቤ ያላቸው በመኖራቸው ምክንያት ፍርደኞቹ በፖሊሶች ላይ ድብደባና ጉዳት እስከማድረስ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህጉ በአሁኑ ሰአት እንዳለፉት አመታት ሰው ለፍርድ ሳይቀርብ በግፍ የሚገደልበት፣ ጥፍሩ የሚነቀልበት፣ የሚደበደብበት፣ ግለሰቦች የተኙበት አልጋ ሁሉ ሳይቀር የሚወረስበት አይነት የመብት ጥሰት አለ ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ ብለዋል፡፡
ታራሚዎችን በተመለከተ የተሰሩ ሰፋፊ ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፤ በከባድ ወንጀል ተይዘው የሚገኙ እስረኞች እንኳን ሳይቀሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እየተገናኙ ጠበቆ ቻቸውን እያማከሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011