አዲስ አበባ፡- «ኢህአዴግ እንደ ፓርቲም ሆነ አገር እንደሚመራ መንግ ሥት 2012 ምርጫው በተቀመጠው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይካሄዳል ብለን በማሰብ እየተንቀሳቀስን ነው። ለዚህም አፅንኦት ሰጥተን ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን ኢህአዴግ አቅጣጫ አስቀምጧል፤» ሲሉ የኢህአዴግ ጽሕ ፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም አስታወቁ።
ኃላፊው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፣ ቀጣዩ ምርጫ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮች ታርመው ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ ሆኖ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ አለበት ሲል ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መግለጹን አቶ ብናልፍ አስታውቀው፤ መንግሥትም ይህን አቅጣጫ ተቀብሎ እቅድ ያዘጋጃል ብለዋል። ይሁን እንጂ ምርጫው ይካሄዳል አይካሄድም የሚለው ጉዳይ ኢህአዴግ እንደ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ምርጫ ቦርድ ለሁሉም ፓርቲዎች በሚያዘጋጃቸው ውይይቶች በሚደረግ ውይይትና ውሳኔ ተገዥ ይሆናል ብለዋል።
ምርጫውን በሚመለከት የኢህአ ዴግ ሥራ አስፈፃሚ ተወያይቶ
ያሳለፈው አቅጣጫ ምርጫ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይካሄዳል በሚል ታሳቢ ነው። እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይካሄዳል የሚል እምነት አለን ያሉት አቶ ብናልፍ፤ ነገር ግን ይካሄዳል አይካሄድም የሚለው ኢህአዴግ ብቻ ውን የሚወስነው አይደለም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርጫውን በሚመለከት በተለያዩ ፓርቲዎች የተለያየ ሃሳብ እየተነሳ ነው ያሉት አቶ ብናልፍ፤ አንዳንዶቹ በተያዘለት ጊዜ ሰሌዳ ይከናወን የሚል አቋም ሲይዙ፤ አንዳንዶች ደግሞ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ምርጫ ማከናወን የሚቻልበት ጊዜ ላይ አይደለንም የሚል አቋም እንዳላቸው አስታውሰዋል። በመሆኑም የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋል ሲሉ መናገራቸውን አቶ ብናልፍ ገልጸዋል።
የኢህአዴግ መንግሥት ሁኔታዎችን በዝርዝር ገምግሞ ዝግጅት እንዲያደርግና ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ምናልባትም በአገሪቱ ታሪክና በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው በጣም የተሻለ ምርጫ ለማካሄድ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተወስኗል ብለዋል። መንግሥትም ቀጣዩን ዝርዝር ሥራ እቅድ አውጥቶ የሚፈፀም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ሀብታሙ ስጦታው