አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ምርት እንዲያቆሙ እገዳ ከተጣለባቸው 22 ፋብሪካዎች ውስጥ 19ኙ ወደ ምርት እየተመለሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል አካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ በተለይም ለበሪሳ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 400 ፋብሪካዎች ውስጥ 22 የሚሆኑት የአየር ንብረት ብክለት በማስከተላቸው ምርት እንዲያቆሙ ክልከላ ተደርጓል።
እገዳው የተላለፈባቸው ፋብሪካዎች የአካባቢውን አየር ፀባይ በመበከል በሰዎችና እንስሳት ላይ የጤና እክል የፈጠሩ እንዲሁም በአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ችግር ያሳደሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች እስኪያሟሉ ድረስ እንዳያ መርቱ መታገዳቸውን አመልክተዋል።
ይሁንና ክልከላ ተደርጎባቸው ከነበሩ 22 ፋብሪካዎች ውስጥ ከሦስቱ በስተቀር 19ኙ ብክለትን የሚያስቀር መስፈርት በማሟላታቸው ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ብለዋል። መስፈ ርቱን ያላሟሉ ፋብሪካዎች ላይ ደግሞ ሂደቱን ጠብቆ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉም ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ከሚገኙ ፋብሪካዎች ውስጥ 80 ከመቶ የሚሆኑት መገኛቸው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ብክለትን የማይከላከሉና መስፈርቶችን ያላሟሉ ከሆነ መቼም ቢሆን ማምረት እንደማይችሉ አስገንዝበዋል።
የፋብሪካ ዎች መስፋፋት የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ወደፊት እንዲያስፈነጥር በእቅድ ወደ ስራ መግባት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአርሶ አደሩ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮችን ማስቀረትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ሲፈጸሙ የነበሩ ስህተቶች መድገምና ነዋሪዎች ላይ ብክነትን የሚያስከትሉ ተረፈ ምርቶችን መልቀቅ እንደማይቻል አስረድተዋል። የተጀመረው ጥረት ቀጣይነት እንዲኖርም የማያቋርጥ ክትትል የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል። አስፈላጊ በሆነ ሰዓትም ፋብሪካዎች ለመንግስት አካላትና ለመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ክፍት እንዲሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
ቀደም ሲል ችግሮች ሲያደርሱ የነበሩ ፋብሪካዎች ለሚዲያዎችና ለመንግስት አካላት ዝግ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ክፍት እንደሚደረጉ አመልክተዋል። ህዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በተከታታይ አስፈላጊውን ክትትልና ምልከታ በማድረግ መፍትሄ የሚሰጠው መሆኑንም አስገንዝበዋል። በፋብሪካዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ምልከታም ምርቶቻቸው የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገባ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የፋብሪካ ባለቤቶችም ቀደም ሲል የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ በማጤን ዘመናዊ አሠራር እየተገበሩ መሆኑን አስረድተዋል። ባለሃብቶችም ይህን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመትከል ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ እስካሁን ድረስም ህጋዊ አሰራርን ተከትለው ችግሮችን ያላስተካከሉ ፋብሪካዎች በመኖራቸው ወደ ትክክለኛው አሰራር እንዲገቡ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር