-የ50 ዓመታት የውሃ ጥያቄ ተመልሷል
አዲስ አበባ፡- በሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት ተቋማት በአካባቢው የልማት ሥራ ላይ ከሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ተራቁቶ የነበረ 80 ሄክታር መሬት ደን እየለማ መሆኑ ተገለፀ። በአንኮበር ወረዳ አይገብር በሚባል አካባቢ ለ50 ዓመታት የዘለቀው የውሃ አቅርቡልን ጥያቄም ምላሽ ማግኘቱም ተጠቁሟል።
የልማት ሥራው ከሚሠራባቸው ወረዳዎች መካከል የአንኮበር ወረዳ የመስኖ ምህንድስና ባለሙያው ኢንጅነር ኃይለሚካኤል ጉርምስ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በአካባቢው ከ80 ሄክታር በላይ መሬት በአራት ወረዳዎች ደን እየለማ ሲሆን ይህም ቀድሞ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማትና የደን ሃብትን በማብዛት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር አዳዲስና ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ባለሙያው ገልፀው፤ በተለይም አገር በቀል ዛፎች ዘራቸው እንዲበራከትና እንዲጠበቁ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል። ቀደም ሲል በአካባቢው የዓሳ እርባታ እንዳልነበረ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ወጣቶችን በማደራጀትም በደን ሃብት እንክብቤ ላይ በመሠማራታቸው የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው አስገንዝበዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ምንሽር በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ወደ ዞኑ ከመጣ በኋላ ለዘመናት ህብረተሰቡ ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውንና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እየተቃለሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ ከፍተኛ የውሃ ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን ወደ ስፍራው መግባትን ተከትሎ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም በመስኖ እና ሌሎች ግብርና ሥራዎች ማዘመን ላይም ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም አስረድተዋል። ግማሽ ክፍለ ዘመን ሲጓተቱ የነበሩ ጥያቄዎች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሲከሰትባቸው የነበሩ አካባቢዎችም ምላሽ ማግኘታቸውንና ለነዋሪዎች እፎይታ መፍጠሩን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተባባሪ አቶ ደጀኔ መብራቴ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በዞኑ ሁለት አስርት ዓመታት በፊት የተጀመሩ በርካታ ተግባራት መኖራቸውንና የማህበረሰቡ ጥያቄዎች እየተመለሱ ነው። በአሁኑ ወቅት በዞኑ አራት ወረዳዎች እየለማ ካለው 80 ሄክታር ደን በተጨማሪ ጎን ለጎን በአፈር እቀባ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ እየተከናወነ ነው።
ከደን ልማት በተጨማሪ በወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትና ማህበረሰባዊ ፋይዳ ያላቸው ሥራዎች በሰፊው እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህ ዓመትም 9ሺ600 የማንጎ፣ አቮካዶ እና ፓፓያ ችግኞች መሰራጨታቸውን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል በአካባቢው ብዙም ባልተለመደ መልኩ 20ሺ የቡና ችግኞች ለህዝቡ መከፋፈሉን አስገንዝበዋል። በእነዚህ ተግባራትም ወጣቶችና ሴቶችም በሰፊው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ደጀኔ ገለፃ፤ ኮሚሽኑ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ብቻ በአንኮበር፣ በረኸት እና ምንጃር በሚሰኙ ወረዳዎች ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ ሥራ ላይ ውለዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል 25 ሚሊዮን 778ሺ ብር፣ ለንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 24 ሚሊዮን ብር በመበጀት 62ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ሆነዋል። በተጨማሪም 14ነጥብ2 ሚሊዮን ብር ለዋሽ ኢመርጀንሲ እና 8ነጥብ5 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለሥነ ተዋልዶ ትምህርት ግንዛቤ ማስጨበጫ በመበጀት 120ሺ ዜጎችን ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ኮሚሽኑ ኖርዌይና ጀርመን አገር ከሚገኙ ለጋሽ አካላት፣ ፓድ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ባገኘው ገንዘብ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ መንግስት ያወጣውን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ይሁንና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ማነስ፣ ፋይናንስ እጥረት፣ ከመንግስት በኩል ሥራውን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ፍልሰትና መሰል ችግሮች ለሥራው እንቅፋት መሆናቸውንም ጠቁመው፤ በቀጣይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አቶ ደጀኔ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር