አብዮተኛው ግንቦት 20

ከስድስት ዓመታት በፊት ግንቦት 20 ዜና ነበር፤ እነሆ አሁን ታሪክ ሆኗል። ከስድስት ዓመታት በፊት ድል ባለ የካድሬ ድግስ በድምቀት ይከበር ነበር። እነሆ ዘንድሮ ግን በዋዜማው ‹‹ነገ ሥራ ይዘጋል አይዘጋም?›› አወዛጋቢ ሆኖ ነበር። ምንም እንኳን በአዋጅ ያልጸደቀ ቢሆንም በቀን መቁጠሪያ (ካላንደር) ላይ ስለተመዘገበ ዝግ ሆኖ ውሏል። ወደፊት የሚኖረውን ዕጣ ፋንታ ወደፊት እናያለን።

በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን አብዮተኛውን ግንቦት 20 በዝርዝር እናያለን። ከዚያ በፊት ግን ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን አጠር አጠር አድርገን እናስታውስ።

ከ119 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 19 ቀን 1897 ዓ.ም ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ተወለዱ። ከዚህ በፊት ሙሉ ታሪካቸውን በዝርዝር ያስነበብን ቢሆንም አሁንም በጥቂቱ እናስታውሳቸው። ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ደቡሳ ከአዲስ አበባ 104 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ወሊሶ ማሩ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ተወለዱ። በትምህርት ረገድ ፊደልን በአካባቢያቸው የቆጠሩ ሲሆን፣ የሃይማኖት ትምህርትም ተምረው በዲቁና ቤተ ክርስቲያንን እስከማገልገል ደርሰዋል።

ከ1912 ዓ.ም እስከ 1918 ዓ.ም በቀድሞው የጦር ሚኒስቴር ፊታውራሪ ሀብተዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) አስተዳደር ውስጥ ወታደራዊ ተግባራትን ተወጥተዋል። ከ1919 ዓ.ም እስከ 1924 ዓ.ም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥት ውስጥ በጋሻ ጃግሬ ደንብ አገልግሎታቸውን አበርክተዋል። ከ1921 ዓ.ም እስከ 1928 ዓ.ም ወደ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋው ወሰን ተዛውረው በማገልገል የባላምባራስነት ማዕረግ አግኝተዋል። በ1928 ዓ.ም በነበረው የማይጨው ጦርነት ከጣሊያን ጋር ተዋግተው ተንቤን ላይ ከፍ ያላ ጀብዱ ሠርተዋል። ከ1929 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም የብዙ ሺህ አርበኞች መሪ ሆነው በየአውራጃው በመዞር ለ5 ዓመታት ከፋሺስት ጣሊያን ጋር ተዋግተዋል።

ገረሱ ዱኪ በየአወራጃው በመዞር የጣሊንን ከከፋፍለህ ግዛ የውጭ ፖሊሲ በፅኑ ተቃውመዋል፤ ገረሱ የጣሊያንን ሴራ ገርስሰዋል። ወታደራዊ ስትራቴጂስት እና ጀግና በመሆናቸውም ከቀዳማዊ ኃይለሥለሴ እጅ ቤልጅየም ሰራሽ ቤልጂግ ጠመንጃ ተሸልመዋል።

ከ83 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 19 ቀን 1933 ዓ.ም የደርግ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተወለዱ። ግንቦት የደርግ እና የኢህአዴግ ታሪክ እስከሚመስል ድረስ፤ መሪዎቹ የተወለዱት በግንቦት ወር፣ የሚመሩት ድርጅት የታቀደውና የተወለደው በግንቦት ወር፣ ተቃዋሚዎቻቸው የጠነከሩባቸው በግንቦት ወር ሆኗል። ከ83 ዓመታት በፊት የተወለዱት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ በጋዜጠኛና ደራሲ ገነት አየለ አማካኝነት ባለፈው ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም 83ኛ ዓመታቸውን ሲያከብሩ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ውብአንቺ ቢሻው ጋር የተነሱት ፎቶ በማህበራዊ ገጾች ሲዘዋወር ውሏል።

ከ25 ዓመታት በፊት ግንቦት 19 ቀን 1991 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጀመረ። በዓለም የሞባይል ስልክ ታሪክን ስንመለከት እንደ መጀመሪያ የሚቆጠረው በ1965 ዓ.ም (እ.አ.አ 1973) ‹‹ሞቶሮላ›› የሚባለው በቅርጹ ፖሊሶች የሚይዙትን መገናኛ የመሰለ፣ በመጠኑ ግን የአነስተኛ ሬዲዮ መጠን ያለው ነበር። የሞባይል ስልክ በኢትዮጵያ አገልግሎት ሲጀምር መጠኑና ቅርጹ በመጠኑም ቢሆን ዝግመተ ለውጥ ያሳየበት ነበር።

ከ1491 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 20 ቀን 525 ዓ.ም በገናናነታቸው ከሚጠቀሱት የኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል አንዱ የነበሩት ባሕር ተሻጋሪውና መናኙ ንጉሥ አፄ ካሌብ አረፉ። እኚህ የአክሱም ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ንጉሥ የዛሬዋን ሀገረ ኤርትራን ጨምረው ቀይ ባህርን የሚያስተዳድሩ ንጉሥ ነበሩ። የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ይህን ለማስታውስ ለመጀመሪያ ልጃቸው ‹‹ካሌብ›› የሚል ስም እንዳወጡለት በመጽሐፋቸው ገልጸዋል።

ከ10 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ዝነኛው ጀርመናዊ የፊልም ተዋናይና በጎ አድራጊ ካርልሄይንዝ በም አረፉ። ካርል ‹‹የሰዎች ለሰዎች ድርጅት (Menschen für Menschen)›› የተሰኘውን የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም በርካታ ኢትዮጵያውያንን ከችግር ታድገዋል፤ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ጣቢያዎችን ገንብተዋል። ለበጎ አድራጎት ስራቸውም የክብር ኢትዮጵያዊ ዜግነት ተሰጥቷቸዋል። በአንዳንድ ከተሞችም ሀውልት ቆሞላቸዋል።

ከ110 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ አባታቸውን ራስ ሚካኤልን ‹‹ንጉሰ ወሎ ወትግሬ›› ብለው አነገሱ።

አሁን ወደ አብዮተኛው ግንቦት 20 ታሪክ እንሂድ። ግንቦት 20 አብዮተኛ የታሪክ ክስተት ነው። ቀኑን በድምቀት ያከብረው የነበረውና የታሪኩ ባለቤት ነኝ የሚለው ኢህአዴግ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ርዕዮተ ዓለሜ ነው ይል ነበር። ወዲህ ደግሞ ግንቦት 20ን አብዮተኛ የሚያደርገው አዲስ የአገር አወቃቀር ቅርጽ ያስያዘ ስለሆነ አዲስ አብዮት ተፈጥሯል ማለት ነው። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የኢትዮጵያ ካርታ አዲስ ቅርጽ ያዘ። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከመሃሉ ላይ ኮከብ ስለተጨመረበት አዲስ ቅርጽ ያዘ። ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ስለፈጠሩ አዲስ አብዮት ተፈጠረ። በእነዚህና ሌሎች ነገሮች ግንቦት 20 ልክ እንደ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም አብዮተኛው የታሪክ ክስተት ሊባል ይችላል።

ከ33 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት ገርስሶ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩ የጻፏቸው መጻሕፍት፣ በተለያዩ መድረኮች የተናገሯቸው ንግግሮች፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች… እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ያስወገደው በሕዝብ ትብብር ነው።

ምንም እንኳን ጦርነቱ የዓመታት ቢሆንም ኢህአዴግ ግንቦት ሃያን በተለየ ያከብረው የነበረው አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትና ቤተ መንግሥት የገባበት ቀን ስለሆነ ነው።

የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት ኢህአዴግ ደርግን ለማስወገድ ሕዝባዊ ድጋፍ የሚያስገኙ ዘዴዎችን ተጠቅሟል። ከእነዚህም አንዱ የጦርነቱን ዘመቻዎች የአካባቢው ሰዎች በሚያከብሯቸውና በሚያደንቋቸው ሰዎች ይሰይም ነበር። የአካባቢው ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ ይሰይም ነበር።

ለምሳሌ፤ በወለጋ እና በሌሎች የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበረውን ዘመቻ ‹‹ቢሊሱማ ወልቂጡማ›› ብሎ ነበር የሰየመው። ቃሉ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ነፃነትና እኩልነት ማለት እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ስም የሰየመውም የአካባቢው ሰው የኦሮምኛ ተናጋሪ ስለሆነ ነው።

በወሎ በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ ዘመቻ ዋለልኝ ተብሎ ተሰይሟል። ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ሲሆን የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ነበር። ኢህአዴግ ይህን የተጠቀመው ዋለልኝ መኮንን የወሎ ተወላጅ ስለሆነ ወሎዎች ይወዱታል ብሎ ሳይሆን ምናልባትም የብሔር ፖለቲካ ጀማሪና አቀንቃኝ ስለነበረለት ይሆናል።

በጎንደር በኩል የነበረው ዘመቻ ደግሞ እስከ ጎጃም ድረስ ‹‹ዘመቻ ቴዎድሮስ›› ይባል ነበር። በዚያ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ የአጼ ቴዎድሮስ ነገር ሲነሳ ወኔው ይቀሰቀሳል ብሎ ስላሰበ ይመስላል።

አራተኛውና አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት የመጨረሻው ዘመቻ ደግሞ ‹‹ዘመቻ ወጋገን›› ይባላል። ‹‹የመጨረሻዋ ጥይት የተተኮሰችበት›› ይሉታል የኢህአዴግ ሰዎች። በእርግጥ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከቤተ መንግሥቱ ዙሪያ በስተቀር መሃል ከተማ ውስጥ የውጊያ ተኩስ እንዳልነበር በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ጽፈዋል። ለዚህ ክስተት አለመኖር የደርጉ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሳምንት በፊት (ግንቦት 13 ቀን) አገር ለቀው መሄዳቸው አስተዋፅዖ ሳይኖረው አይቀርም።

በ2008 ዓ.ም ግንቦት 20 ሲከበር የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ካቀረበው ጽሑፍ፤ የግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ክስተት የሚከተለውን እናስታውስ።

‹‹…. አዲስ አበበ በሦስት አቅጣጫ በኢህአዴግ ሰራዊት ተከባለች። ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚወጣም ሆነ የሚገባ የለም። የቀለበቱ ማጥበብ ቀጥሏል። አምቦ የነበረው ሰራዊት ወደ ሆለታና ታጠቅ ተጠጋ። በጅማ በኩል የነበረው ግልገል ግቤን ተሻግሮ ወሊሶን አልፎ ወደ አለም ገና ተጠግቷል። ደብረ ብርሃን የነበረው ሃይል ገሚሱ ወደ ደቡብ ምስራቅ በመጓዝ ደብረ ዘይትን ከበባት። ማንኛውም የጦር አውሮፕላን ወደ ሰማይ አልወጣም፤ አልወረደም።

….ግንቦት 19 ቀን 1983 ልክ ከቀኑ 10 ሰዓት ወታደራዊ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስተባብረው ቡድን ለመጨረሻ የሰላም ውይይት ሎንደን ከነበረው የበላይ አመራር ‹‹ቀጥል›› የሚል አጭር መልዕክት ደረሰው። ቀድሞ በተደረገው ጥናት አዲስ አበባ በሦስት ግንባር ተከፍላለች።

በአምቦ ግንባር የነበረው በጎጃም በር በኩል ወደ ፒያሳ በመዝለቅ መርካቶን ተቆጣጥሮ ወደ ጅማ መንገድ ያመራል።

ሁለተኛው ግንባር በደብረ ዘይት የሚመጣ በአቃቂ ገብቶ ንፋስ ስልክ፣ ጎተራ፣ ቄራ፣ አራተኛ ክፍለ ጦር፣ ስታዲየም ጨምሮ እስከ ሜክሲኮ ያለውን ይይዛል።

ሦስተኛው በሰንዳፋ የሚመጣ በኮተቤ በመውረድ ብረታ ብረት ፋብሪካ ከደረሰ በኋላ ለሦስት ንኡስ ግንባር ይከፈላል። አንዱ በመገናኛ በኩል ወደ ኤርፖርት ያመራል። ሁለተኛው ክፍል በ22 ሰንጥቆ ወደ መስቀል አደባባይ በመሄድ ታችኛውን ቤተመንግስት ይቆጣጠራል። ሦስተኛው ክፍል በእንግሊዝ ኤምባሲ አቅጣጫ በግንፍሌ አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በመግባት ቤተ መንግሥትን ይቆጣጠራል።

ኮማንደሮቹ ይህንን ድልድል በማድረግ ሌሊቱን በሙሉ ሲዘጋጁ አደሩ። እነ ሐየሎም በነበሩበት አቅጣጫ ታጠቅ አካባቢ የነበረው ሃይል ማታ ወደ ከተማ የመፍረስ ምልክት ስለታየ ይህ ሃይል ወደ መሃል ከተማ ከገባ አላስፈላጊ ዋጋ የሚያስከፍል ውጊያ ስለሚያስከትል አስቀድሞ መያዝ አለበት ተብሎ ስለተወሰነ በዋዜማው የተወሰነ ሃይል ቀድሞ ወደ ቦታው እንዲጠጋ በማድረግ በኮልፌ 18 ማዞሪያ በኩል ተዘጋ። ከከተማው ወደ ውጪ እንዲበተንም ተደረገ።

አስቀድሞ የወጣው ስትራቴጂ በሚገባ የሰራ መሆኑ እየተረጋገጠ መጣ። የመንግሥት አብዛኛው ወታደር ከአዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት እንዲበታተን ተደረገ። ገሚሱ መሳሪያ የያዘ ገሚሱ መሳሪያ የሌለው እየተንቀረፈፈ ከሚገባ በስተቀር ተደራጅቶ ወደ ከተማዋ የሚያፈገፍግ ሰራዊት አልነበረም። ይህ ለኢህአዴግ ትልቅ ድልና ስኬት ነበር። በህዝቡ ዘንድም ስጋትን የቀነሰ ነበር።

የወጋገን ዘመቻ ዋና ዓላማው የቀረውን ሰራዊት መደምሰስ ሳይሆን ከተማዋን በብልሃት መቆጣጠር ነበር…››

ኢህአዴግ ይህን እያደረገ በለንደን ደግሞ ከደርግ መንግሥት ጋር ድርድር ነበር። የፖለቲካ ተንታኞች የለንደኑን ኮንፈረንስ ‹‹ሳይጀመር የተጠናቀቀ ድራማ›› በማለት ሲገልጹት ነበር። በእርግጥም ኮንፈረንሱ የግማሽ ቀን ዕድሜ ብቻ ነው የነበረው። ዋና አደራዳሪው ሚስተር ሄርማን ኮህን ተደራዳሪዎቹን በተናጥል ማነጋገራቸው ብቻ ነው። በሚቀጥለው ቀን ግን ሚስተር ሄርማን ኮህን ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ ጉባኤ በመጥራት ኮንፈረንሱ መሰረዙን አስታወቁ። ኢህአዴግ በአዲስ አበባ፣ ህግሓኤ በአስመራ የየራሳቸውን መንግሥት እንደሚመሰርቱም ገለጹ።

ለኮንፈረንሱ መበተን ምክንያት የሆኑት በመጨረሻው ሰዓት የኢህዲሪ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት ሌተናል ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ናቸው። ጄኔራል ተስፋዬ ለሚመሩት መንግሥት ባለስልጣናት ሳያስታውቁ ዕለተ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 1983 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ለአሜሪካ ኤምባሲ ‹‹የጦር ሰራዊቱ ከቁጥጥሬ ውጭ ሆኗል፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም ዘረፋ ተጀምሯል›› የሚል መረጃ ሰጡ፤ ለራሳቸውም የኢጣሊያ ኤምባሲ ገብተው ጥገኝነት ጠየቁ (በወቅቱ ወደ ኤምባሲው አብረዋቸው የገቡት ባለስልጣናት አቶ ሀይሉ ይመኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሻምበል ብርሃኑ ባይህ የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እና ሌተናል ጄኔራል ሐዲስ ተድላ የኢህዲሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ናቸው)።

የአሜሪካ ኤምባሲም ከጄኔራል ተስፋዬ የሰማውን መረጃ ለንደን ለሚገኙት ሚስተር ሄርማን ኮህን አስተላለፈ። በዚህም መሰረት ሚስተር ኮህን ምሽት ላይ በኮንፈረንሱ አካሄድ ላይ ለውጥ መደረጉን አስታወቁ። አዲስ አበባ እንደ ሞቃዲሾ እና እንደ ሞኖሮቪያ እንዳትሆን የኢህአዴግ ጦር ወደ ከተማዋ መግባት እንዳለበትም ተናገሩ። የኢህአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም ጦራቸው አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር ትዕዛዝ ሰጡ። በመሆኑም የኢህአዴግ ጦር ከሌሊቱ 8፡00 ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ መግባት ጀመረ። ያንን ኦፕሬሽን የመሩት አዝማቾች ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ፣ ጄኔራል ሐየሎም አርአያ፣ ጄኔራል አበበ ተክለ ሀይማኖትና ጄኔራል ሳሞራ የኑስ እንደሆኑ ይነገራል።

ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ከጧቱ 1፡ 00 ሰዓት አንድ የኢህአዴግ ታጋይ ከኢትዮጵያ ድምጽ ብሔራዊ አገልግሎት (የኢትዮጵያ ሬዲዮ) እንዲህ ሲል ተሰማ።

‹‹የዘመናት የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት ደርግ ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ሬድዮ ጣቢያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል፤ ግንቦት 20 ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሦስት ዓመተ ምህረት››

በሕወሓት ጀማሪነትና መሪነት የተደረገው የትጥቅ ትግል በዚህ መልኩ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ለ27 ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን መራ። በ2010 ዓ.ም ለውጥ መጣ፤ ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ ሳይሆን ዜና ነው። እነሆ ግንቦት 20 ግን ታሪክ ሆነ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You