አዲስ አበባ፡- ከዓለም ባንክ በብድር የተገኘው 300 ሚሊዮን ዶላር በገጠርና ከተማ ንጹህ የውሃ አቅርቦትና ንጽህና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ እንደሚሆን ተገለፀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ብድሩ ቀደም ሲል የንጹህ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ባልሆኑ የገጠር አካባቢዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ይሆናል፡፡ የንጹህ ውሃ አቅርቦት በሌለባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም ከባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡ ፡ በከተማ አካባቢ ያለው የውሃ አጠቃቀም በተገቢው መንገድ እንዲከናወን ሙያዊ እገዛዎች ይደረጋሉ፡፡
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማት ላይ ያለው የውሃ አቅርቦት ይሻሻላል፡፡ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ያለውን የውሃ መቋረጥ ለመቀነስ የሚያስችል መሰረተ ልማት የሚዘረጋ ሲሆን፤ የውሃ አካላትን ከብክለት ለመከላከል የሚያስችሉ የግንባታ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ ለውሃ አቅርቦት የሚሰሩ የግንባታ ሥራዎች የጎርፍ እና የድርቅ አደጋን መከላከል የሚያስችሉ ተግባራትም ይከናወናሉ፡፡
የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ወይዘሮ ካሮሊን ተርክ በበኩላቸው፤ ባለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያ የውሃ አቅርቦት ተደራሽነት መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት ጥራት ያለው የመጠጥ ውሃ ተደራሽነትና የንጽህና አጠባበቅ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፡፡ የጎርፍና የድርቅ አደጋዎችን ለመከላከል ግን አሁንም መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ጠቁመው፤ ለዚህም የዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ዋለልኝ አየለ