. ከፖለቲከኞችና ነጋዴዎች ነፃ ይሆናል
አዲስ አበባ፡- በሙያተኞች የሚመሰ ረተው ኢትዮ ዋርካ መልቲ ሚዲያና ኮምኒኬሽን ሼር ካምፓኒ የጋዜጠኝነት ሙያን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገለጸ። ሚዲያው የጋዜጠኝነትን ሙያ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ከነጋዴዎችና ፖለቲከኞች ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የሚቋቋም መሆኑንም ተጠቁሟል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት ክፍል እንዲሁም የኢትዮ ዋርካ የቦርድ ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃን የሚመሩትም ሆነ ስራቸው የሚከናወነው ከሙያው ውጪ በሆኑ ሰዎች ነው።
ይህም የሙያው ሳይንስ በተጨባጭ ሥራ ላይ እንዳይውል ከማድረጉም ባሻገር ነፃና ገለልተኛ የሆነ ተቋም እንዳይፈጠር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ባለሙያዎች በአክሲዮን የሚመሰርቱት ይህ ተቋም ከዚህ ቀደም በዘርፉ ይታይ የነበረውን ክፍተት ለመፍታት ይሰራል።
«የፖለቲካው ሁኔታ በተቀያየረ ቁጥር የሚቀያየር ሚዲያ ነው ያለው» ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ፤ የአዲሱ ሚዲያ መመስረት ሙያተኞች ዳር ቆመው ከመታዘብ ባለፈ ዘርፉ በተግባር እንዲመሩት ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል። በተለይም በሌሎች ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን የፖለቲከኞች ጣልቃገብነት ለማስቀረት አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም አክሲዮኑ በባለሙያዎች መመስረቱ በፖለቲከኞችና በነጋዴዎች እንዳይጠመዘዝ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል። «ሚዲያዎች ትልቁ ችግራቸው የገንዘብ ችግር ነው። በዚህም ምክንያት የነጋዴዎች ወይም የፖለቲከኞች ዓላማ ማስፈጸሚያ ይሆናሉ። ዋርካ ሚዲያ በባለሙያዎች ብቻ በአክሲዮን መመስረቱ ከዚህ ነፃ ያደርገዋል» ብለዋል።
ከመስራቾቹ ውስጥ በህትመት ሚዲያ፣ በብሮድካስት ሚዲያ፣ በአይ.ሲ.ቲ እና በመሳሰሉት ሙያዎች ልምድ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይም በህክምና፣ በምህንድስና፣ በህግና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ያሉ ባለሙያዎች ይሳተፉበታል። ዋርካ ሚዲያ ሙያ ላይ ትኩረት አድርጎ ስለሚሰራ በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ‹‹ስፔሻላይዜሽን›› እንዲኖር ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢትዮ ዋርካ መልቲ መዲያና ኮምኒኬሽን ሼር ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ገለቱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ሚዲያውን መመስረት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ጋዜጠኛው ሙያውን የሚያሳድግበትና ነፃ ሆኖ የሚሰራበት የሚዲያ ምህዳር ለመፍጠር ነው። በየዘርፉ የሚተነትኑ ባለሙያዎችን በማፍራት የአንድ ዘርፍ ተንታኞች እንዲኖሩት ይደረጋል።
ከዜና ባለፈ ጥልቀት ያላቸው ትንታኔዎች የሚሰሩበት መሆኑን አመልከተው፤ «ኪነ ጥበብ ከሆነ በኪነ ጥበብ ሰዎች ይተነተናል፤ ኢኮኖሚ ከሆነ የኢኮኖሚ እውቀት ባላቸው ሰዎች ነው፤ ማንም በማይመለከተው እየገባ የሚተነትንበት አይሆንም» በማለት ተናግረዋል። በአገሪቱ ጋዜጣ የሚያትም አንድ ማተሚያ ቤት ብቻ መሆኑ ጋዜጦች በዕለታቸው እንዳይወጡ ያደረጋቸው መሆኑን ያመለከቱት አቶ እሸቱ፣ይህንን ችግር ለመፍታት ያስችል ዘንድ ሚዲያው የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ ሳይሆን ማተሚያ ቤትም የሚኖረው መሆኑን አስረድተዋል።
ሚዲያው እንደ ቢቢሲ ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ተሞክሮ በመውሰድ ቋሚ የሆኑ ተንታኝ ሠራተኞች እንደሚኖሩ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በአገሪቱ ውስጥ ለረጅም ዓመት በአንድ ሚዲያ ላይ ያለመቆየትን ችግር የሚቀርፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።
«ጋዜጠኛ ልምድ የሚኖረው በአንድ ሚዲያ ላይ ለረጅም ዓመት ሲሰራ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ ያልተለመደ በመሆኑ ዋርካ ሚዲያ ይህን ለመፍታት የተመሰረተ ነው» ብለዋል። በተጨማሪም በሚዲያና ኮምኒኬሽን የልህቀት እንዲሁም የምር ምርና ሥልጠና ማዕከል የሚኖረው መሆኑን ጠቁመው፣ይህም የጋዜጠኝነት ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችለው መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ዋለልኝ አየለ