‹‹እንተዛዘብ›› ከተባለማ …

ከህይወት ልምዳችን ደጋግመን እንዳየነው በየትኛውም አጋጣሚ ከለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ይኖራሉ። ልብ ብለን ካስተዋልነው ደግሞ አንዳንድ ለውጦች ልክ እንደ ፍርድ ቤት ውሳኔ ናቸው። ለሁለቱም በእኩል አይመዝኑም። አንዱን ወገን አስደስተው ሌላኛውን ማሳዘን፣ ማስከፋታቸው አይቀሬ ይሆናል።

ይህ እውነት በተለያዩ የህይወት አጋጣሚዎች ሲስተዋል ያየነው ሀቅ ነውና ለምን ስንል የምንሟገትበት አይደለም። እንዴት ካልን ደግሞ ለአባባሉ ብዙ ማሳያዎች በመኖራቸው በክርክሩ ልንረታ እንችላለን።እኔ ግን ለአሁኑ የማነሳው ይህን መሰሉን ሀቅ የሚጋፋውን አይደለም። እንደ ክፍተት የምጠቁመው ከለውጦች ጋር ተያይዞ ክስተቶች ሲኖሩ ሆን ተብለው ስለሚፈጠሩ ችግሮች እንጂ ።

መክረሚያውን በከተማችን የኮሪደር ልማቱ ቀን ተሌት እየተሰራ ነው።ይህ አጋጣሚ ደግሞ ብዙ ነገሮችን መለስ እያልን እንድናስብ አስችሎናል። አሁን አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷ እንደሚመጥናት ሆኖ በልኳ ልትታይ የቆረጠች ይመስላል። መቁረጥ ሲባል ደግሞ እንዲሁ በሃሳብ ብቻ አልሆነም። ትናንት በክፉ እሳቤ እጅ ሲጠቆምባት፣ ጥርስ ሲነከስባት የኖረ ታሪኳን በሥራ ልትሽረው ተነስታለች። ዛሬ ይህን የጀመሩ እጆች እረፍት አልባ ናቸው። ዕቅዱን የወጠኑ አእምሮዎችም ስለ ትግበራው ስኬት በፈጣን ሩጫ ላይ ይገኛሉ።

ወደቀደመው ሃሳቤ ልመለስ። ከእንዲህ መሰሉ ለውጥ ጋር ተዳምረው ሊፈጠሩ ወደሚችሉት ችግሮች የከተማችን የኮሪደር ልማት አሁን ብዙ መልኮችን እያሳየን ነው። እግረ መንገዱን ደግሞ የሚያስተዛዝቡን እውነታዎች ያጋጥሙን ይዘዋል ።

አንዳንዴ የአንዱ አጋጣሚ ለሌላው ክፉና ደግ ገጽታ አለው። አንዱ ‹‹ጎድሎብኛል›› በሚለው ነገር ሌላው ደግሞ አጋጣሚው ሲሳይ ሆኖት ፈገግታው ሲበራ፣ ውስጡ ሀሴት ሲያደርግ ይስተዋላል።

ይህ እውነት እንደየሁኔታው ይለያይ እንጂ በየአጋጣሚው ልናልፍበት መገደዳችን አልቀረም። የኮሪደር ልማቱ በተጀመረ ማግስት ራስ ወዳድነታቸውን ያሣዩን አንዳንድ ባለታክሲዎች ዛሬም ድረስ በማንአለብኝነት ዘልቀዋል። እንዲህ አይነቶቹ ሁሌም መነሻና መድረሻቸው የግል ጥቅምና ትርፋቸው ብቻ ነው።

እነዚህ ወገኖች አጋጣሚው ዛሬም ድረስ ሲሳይ ሆኖላቸዋልና መንገዱን እያሳበቡ ከታሪፍ በላይ ያስከፍላሉ። በስራው እያመሀኙ አንዱን በአንዱ ይደርባሉ። ባሻቸው ቦታ ጭነው ከፈለጉት ስፍራ ቢያወርዱ ‹‹ለምን ?››ባይ ጠያቂ የላቸውም ። አብዛኞቹ አንደበታቸው የተገራ ድርጊታቸው የታረመ አይደለም።

በእንዲህ አይነቶቹ ማንነት ብዙኃኑ ቢያማርርም ዳግም አገልግሎታቸውን ከመጠቀም ሌላ ምርጫ የለውም። ዛሬ በትንሹ ያሳዩትን ሙከራ ነገ በእጥፍ አሻሽለው ያስቀጥሉታል። ይህ እውነት እስካአሁን እያስተዛዘበ አብሮ አዝልቆናል። ለምን የሚል የሕግ አካል መርምሮ የሚያስቀጣ ደንብና መመሪያ አለመኖሩ ደግሞ ትርፍን ከኪሳራ አጨባብጧል።

የኮሪደሩ ልማት መካሄድ ከጀመረ ወዲህ ድንገቴ የመንገድ መዘጋትና የአቅጣጫ መቀየር ጉዳይ የተለመደ ሆኗል። መንገዱ ደግሞ ጠዋት አልያም ከደቂቃዎች በፊት ያለምንም ችግር ያለፉበት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባጋጠመ ጊዜ አርፍዶ ሥራ መድረስ፣ አምሽቶ ከቤት መግባት ብርቅ አይደለም።

ይህ ይሆን ዘንድ የልማት ሥራው ባህሪ ወሳኝነት አስገድዶ ነው ብለን እንገምት። እንዲህ አይነቱን ዋጋ መክፈልም የዜግነት አንዱ መገለጫ ስለመሆኑም ግድ ይበለን። አስቀድሞ መረጃ ባለመኖሩ ምክንያት ለሚደርሰው እንግልት ግን ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ሊኖር ይገባል።

ሌላው የሚያስተዛዝበን ጉዳይ ከዚሁ መንገድ መዘጋጋት ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ወከባና ጥድፊያ ነው። አንዳንዴ በስፍራው የሚገኙ የሕግ አካላትና ደንብ አስከባሪዎች እግረኞችን በእጅጉ ሲያዋክቡና ሲያመናጭቁ ይስተዋላል። እርግጥ ነው ባልተገባና ባልተፈቀደ የሥራ ቦታ ላይ መራመዱ አግባብ ላይሆን ይችላል። ማንም ግን ይህን እውነት አስቀድሞ እንዲያውቀው ካልሆነ ስፍራው ላይ መገኘቱ ብቻ ጥፋተኛ አያስብለውም።

በድንገት ከቤቱ የወጣ ሰው በክፉና ደግ አጋጣሚዎች ሊራመድ ይችላል። በተለይ በሄዱበት መንገድ አለመመለስ ግድ በሆነ ጊዜ ልምድና ቅልጥፍናው ያላቸው ፈጥነው አማራጭ መውሰዳቸው አይቀርም። ይህን ማድረግ የማይቻላቸው አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ደግሞ ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ። አስቀድሞ በቂ የመረጃ ልውውጥ ቢኖር ግን በመጠኑም ቢሆን ችግሩን መቅረፍ በተቻለ ነበር።

ሰፊ የኮሪደር ልማት በሚካሄድባቸው ስፍራዎች የቀድሞዎቹ መሠረተ ልማቶች እየተወገዱ በሌላ የመተካታቸውን ጉዳይ እያየነው ነው። ይህ መሆኑ ዘመናዊነትን፣ ጊዜ ወለድ አዲስነትን በተግባር ለማመላከት እማኝ ሆኗል። ይህኛው በጎነት እንዳለ ሆኖ በጎንዮሽ የሚባክኑ፣ የሚዝረከረኩ ንብረቶች የሌሎች ሲሳይ መሆናቸውን ማየቱ ደግሞ በእጅጉ የሚያስቆጭ ነው።

ብረታ ብረቶችን መለቃቀም መተዳደሪያቸው ያደረጉ አንዳንዶችን ጨምሮ አሁን ላይ የሥራ መደባቸውን ቀይረው ጭምር በለቀማው የሚሰማሩ ጥቂቶች ጠቃሚ ንብረቶችን እየተሻሙ ስለመሆኑ ልብ ይሏል። አሁን ቀድሞ በብረት ተዘግተው የነበሩ የመንገድ ላይ ቱቦዎች በልማቱ ምክንያት ተነስተው መልካቸው ተቀይሯል።

በስፍራው የነበሩ የብረት መዝጊያዎች ታዲያ በቀላሉ ከፈላጊዎቻቸው መዳፍ ለመግባት የሚያግዳቸው አልተገኘም። እነዚህ ከፍተኛ ወጪ የተደረገባቸው ንብረቶች በሌሎች በመተካታቸው ሂደት ቀድሞ የነበረው ሀብት ሁሉ ይጣል፣ ይወገድ ማለት አለመሆኑ ግልጽ ነው።

የአጋጣሚውን ክፍተት የሚሹት አንዳንዶች ግን ሁሌም ዓይንና እጃቸው ፈጣን ስለመሆኑ አይተን ታዝበናል። በኮሪደሩ ልማት እንደተስተዋለው ጠዋት ያለፉበትን መንገድ ሲመለሱ እንደነበረ ላይራመዱበት ይችላሉ። ይህ ፈጣን የሥራ ሂደትም ለብዙዎቻችን አዲስና እንግዳ መምሰሉ አይቀርም። ለአሰሪው አካል ግን ቀድሞ የተያዘ ሃሳብ ነውና የዕቅድ ክንውኑ ሆኖ ይመዘገባል።

ከዚሁ ተያይዞ ግን በመንገዱ ሁሌም እንደልማዳቸው ስለሚራመዱ አቅመደካሞችና አካልጉዳተኞች እንቅስቃሴ ማሰብና መጠንቀቁ የግድ ይላል። አሁን ላይ ለሥራ አመቺነት ሲባል ተከፍተው የሚተው ጥልቅ ጉድጓዶች በተለይ ለእነዚህ ወገኖች ስጋት መሆናቸው አልቀረም።

ከኮሪደሩ ግንባታ በኋላ ቀድመው የነበሩ የመንገድ ላይ አገልግሎቶች ከነጭራሹ ጠፍተዋል ባይባልም በተለይ አነስተኞቹ ሳስተው፣ ተፋዘዋል ለማለት ያስደፍራል። ዛሬ ከቤት ሲወጡ ድንገት ውሃ ጥም ቢያቃጥል፣ ሽንት አጣድፎ ቢይዝ፣ አረፍ ይሉበት አማራጭ አይገኝም።

አይበለውና ከዚህም የከፋ ሕመም ቢኖር መፍትሔው ቅርብ አይደለም። እንደትናንቱ መንገድ ላይ ካሉ መገበያያዎች ዕለታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን የሚገዙበት አማራጭም የለም። እርግጥ ነው የተጀመረው የልማት ይዘት ሰፋ ያለና ውጤቱ የተለየ ነው። አንዳንዴ ደግሞ የግድ ናቸው ለሚያስብሉ አሳሳቢ ፍላጎቶች ጊዚያዊ አገልግሎትን መፍጠሩ ይጠቅማል እንጂ አይከፋም።

እጅግ ፈታኝ ነው ባይባልም የልማቱ ለውጥ የአንዳንድ ሰዎችን አስቸጋሪ ባህሪ ጭምር አሳይቶናል። እንደ ትራንስፖርቱ ሁሉ የኮሪደር ልማቱ የመንግሥት ሠራተኞችን የፐብሊክ ሰርቪስ አጠቃቀም በውስን መልኩ ለውጦታል። አገልግሎቱ ብዙኃኑን ባማከለ ስፍራ እንዲሆን ሲደረግም የአውቶቡሶቹ የቀድሞ መነሻና መድረሻዎች መቀያየራቸው አልቀረም።

ችግሩ እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም። ብዙ ጊዜ ተጠቃሚ ሠራተኞች ወንበር ለማግኘት ፈጥነው ከቢሮ በመውጣት ሰልፍ ይይዛሉ። አሁንም ችግሩ ይህ አይደለም። አሳዛኙ ጉዳይ ሰአታቸውን አክብረው በአግባቡ ተራቸውን በሚይዙት ሀቀኞች ላይ የሚፈጽሙት በደል እንጂ ።

የእነሱ ያለሰአት ወጥቶ መደርደር ሳያንስ ያለአንዳች ይሉኝታ ሌሎች ባልንጀሮቻቸውን ከፊት ያስገባሉ። የመንቀሳቀሻ ሰአት ደርሶ ጉዞ ሲጀመር ታዲያ ሕገወጦቹ ያሻቸውን ወንበር አማርጠው ምቾታቸውን ለማጣጣም የሚቀድማቸው የለም ። አስቀድመው የቆሙት ታማኞች ግን ውስጥም ገብተው መንገዳቸውን እንደቆሙ ይጨርሱታል።

ወዳጆቼ! እንተዛዘብ ከተባለ የኮሪደር ልማቱ አጋጣሚ ሰበብ የሆናቸውን ጥቂቶች ተግባራት ለይቶ መደርደር ይቻላል። ለሁላችንም የሚበጀው ግን ችግሮቻችንን እያስተዋልን ፣ መፍትሄውን ማስቀመጡ ላይ ቢሆን ይመረጣል። ይህ ጊዜ አልፎ ሌላው ታሪክ ሲተካ በሥራዎቻችን መኩራትና ማፈር ይኖራልና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You