ባህላዊ መድሃኒትን የማሳደግ ጅምር

የባህላዊ መድሃኒት ሲነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቻይና፣ ህንድ፣ ታይላንድና ጃፓንን የመሳሰሉ ሀገራት በግንባር ቀደምትነት አብረው ይነሳሉ። እነዚህ ሀገራት ባህላዊ መድሃኒትን ለራሳቸው ከማምረት አልፈው ለተቀሩት የአለም ሀገራትም አበርክተዋል። በዚህም የራሳቸውን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አልፈው በዘመናዊው ህክምና ከሚታዘዘው መድሃኒት በተጨማሪ ባህላዊ መድሃኒቶችን ለገበያ በማቅረብ ለአለም ህዝብ ጤና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል።

እነዚህ ሀገራት በባህላዊ መድሃኒት በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፉት ባህላዊ መድሃኒቶቻቸውን በሳይንሳዊ መንገድ መርምረው ጥራታቸውን፣ ደህንነታቸውንና ፈዋሽነታቸውን አረጋግጠው ለገበያ በማቅረባቸው ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መድሃኒታቸውን በአለም አቀፍ ደረጃ በሚገባ ስላስተዋወቁም ዛሬ መድሃኒታቸው በስፋት አለም ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው።

ኢትዮጵያም ብትሆን ሀገር በቀል የባህላዊ መድኃኒት ቅመማ እውቀት ያለባትና ለመድሃኒትነት የሚሆኑ እፀዋት በስፋት ሚገኙባት ሀገር ናት። ይሁንና በኢትዮጵያ የባህላዊ መድሃኒቶች እውቀት በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈና ልዩ ልዩ የሙከራ ሂደቶችን አልፎ ለገበያ የሚቀርብ አይደለም። የባህላዊ መድሃኒት እውቀቶችም ቢሆኑ ከአዋቂው ውጪ ሌላው አያውቃቸውም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከባህላዊ መድሃኒት ዘርፍ እምብዛም ተጠቃሚ አይደለችም።

እንዲያም ሆኖ ግን ባህላዊ መድሃኒት በሳይንሳዊ መንገድ ተረጋግጠው ለገበያ እንዲቀርቡ የሚያስችሉ ስርአቶች በመንግስት በኩል ተዘርግተው እየተሰራባቸው ይገኛል። የባህል መድሃኒት ለህክምና የሚያቀርቡ አካላትም ፍቃድ አግኝተው እንዲሰሩ የማድረግ ጅምር እንቅስቃሴዎች አሉ። የባህል መድሃኒቶች በዘመነ መልኩ ተመርተው ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው በሚመለከተው አካል ተረጋግጦ ወደገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ሂደት ግን አሁንም ገና ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

ዶክተር ግዛው በቀለ የግሪን ኬር ናቹራል መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ናቸው እርሳቸው እንደሚናገሩት ኩባንያቸው ስራውን በኢትዮጵያ ከጀመረ ሰባት አመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ አመታትም በርካታ ስራዎችን አከናውኗል። በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ባህላዊ ህክምና እውቀት ወደ ገበያ እንዲወጣና ህብረተሰቡ ከዘመናዊው ህክምና ጎን ለጎን በባህላዊ ህክምናም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ልዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ባህላዊ ህክምና በበጎ መልኩ የሚታይ ባለመሆኑ ይህ አመለካከት እንዲቀየር ህብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችንም ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል።

ከዚሁ ስራ ጎን ለጎን ኩባንያው በተለይ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ እድሚያቸው እስከ አስራ አራት አመት ለሚደርሱ ህፃናትና ታዳጊዎች እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች ነፃ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። የተደበቀው ባህላዊ መድሃኒትና እፀዋት እንዲታወቅ በማድረግ ረገድም ሰፊ ርቀት ተጉዟል። በዚህም በርካታ በባህል ህክምና አገልግሎት ውስጥ ያሉ ሰዎች ተገቢው እውቀት ኖሯቸው ህክምናውን ሳይደብቁ ለህብረተሰቡ እንዲሰጡ አስችሏል። በህክምና ሂደት ችግሮች ሲያጋጥሙ ተጠያቂነት እንዲኖርም እየሰራ ይገኛል።

ኩባንያው በካናዳ ስራውን እያከናወነ በነበረበት ግዜ ፍቃድ ያለውን የፀጉርና የቆዳ ቅባት ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ ያለው የገበያ ሁኔታ በደምብ ስለሚታወቅ በቀጥታ ወደ ማከፋፈል አልገባም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ምርቱን ተረድተው እንዲገዙና እንዲጠቀሙ የማስተማርና የማስገንዘብ ስራ ሰርቷል። ይህም ሰዎች ለከፈሉበት ባህላዊ መድሃኒት የሚገባቸውን የጤና ጥቅም ለማግኘት አስችሏቸዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደሚሉት የቡና ዘይት በአለም አቀፍ ገበያ ለተለያዩ የቆዳ በሽታዎች ህክምና በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ገበያ ይበልጥ ለማሳደግ ደግሞ ኩባንያው ረጅም አመት ፈጅቶበታል። የቡና ዘይትን አምርቶ ለገበያ ለማቅረብም በርካታ ቡና ተጠቅሟል። ህብረተሰቡ ከዚህ የቡና ዘይት ምርት በልዩ ልዩ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆንም ኩባንያው ዘይቱን እዚሁ አምርቶ ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ ለአለም አቀፍ ገበያም ጭምር እንዲተርፍ እየሰራ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ኩባንያው ከ100 ኪሎ ቡና 5 ሊትር የቡና ዘይት ማምረት ችሏል። ይህ ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዘይት ከሚያመርቱ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም ከፍተኛ ነው። ይህ መጠን ወደ ገንዘብ ሲቀየር የ1 ሊትር የቡና ዘይት ወጋ 1 ሺ ዶላር ያወጣል። ኢትዮጵያ በ300 እና 400 ዶላር ወደ ውጪ የምትልከው ጥሬ ቡና በዘይት መልክ በማምረት ቢላክ ወደ 5 ሺ ዶላር ሊጠጋ ይችላል። የቡና ዘይትን በስፋት በማምረትና ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ለማምጣት ኩባንያው ፐርፐዝ ብላክ ከተሰኘውና በግብርና ላይ ከሚሰራው ድርጅት ጋር ተፈራርሟል።

በዚህ ቡናን በዘይት መልክ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ ሂደት አንደኛ አምራቹ ገበሬ ምርቱን በመሸጥ ገቢውን ማሳደግ ይችላል። ሁለተኛ ህብረተሰቡ የቆዳና ተያያዥነት ያላቸው የጤና እክሎች ሲያጋጥመው ዘይቱን እንደ አንድ ተፈጥሯዊ የመድሃኒት አማራጭ እንዲጠቀም ያስችለዋል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ምርቱ ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጪ ገበያ ሲቀርብ ለሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የውጪ ምንዛሬ ያስገኛል።

የቡና ዘይት በኢትዮጵያ ብዙም ጥቅሙ ላይታወቅ ይችላል። በሌላው ሀገር ግን እጅግ የታወቀና በርካታ የጤና ጥቅሞች ያሉት ነው። በዚሁ ምክንያት ኩባንያው ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኩል የቡና ዘይቱን አምርቱልን ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። ነገር ግን ይህን ጥያቄ ወደ ጎን ትቶ የቡና ዘይትን በኢትዮጵያ አምርቶ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። ይህም ከቡና ዘይቱ ከሚገኘው የውጪ ምንዛሬና ከሚሰጠው የጤና ጥቅም ባለፈ የኢትዮጵያን ባህላዊ መድሃኒት የማሳደግና ለተቀረው አለም የማስተዋወቅ ጅምር ስራ ነው።

እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ማብራሪያ ኩባንያው አስካሁን በሀገር በቀል እፀዋት ዙሪያ ለበርካታ ሰዎች ትምህርት ሲሰጥ ቆይቷል። ነገር ግን ትምህርቱ በቂ ባለመሆኑ ከኢትዮጵያ ባህላዊ መድሃኒት ጋር በተያያዘ በዘርፉ እውቀት ያላቸውን ሰዎች በማሰባሰብ ያላቸውን እውቀትና ልምድ የሚያካፍሉበትን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለማስጀመር እቅድ ይዟል። ሰዎች ከመታመማቸው በፊት በሽታ መከላከል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ ጥረት እያደረገም ይገኛል።

በተለይ ህብረተሰቡ ለምግብነት የሚያውላቸው እፀዋቶች ዙሪያ ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲኖረው ግንዛቤ የመፍጠርና ራሱን ከበሽታ የሚከላከልበት ሁኔታ እንዲፈጠር የግንዛቤ ባስጨበጫ ስራዎችን ይሰራል። ባህላዊ መድሃኒቶች ዘምነውና ሳይንሳዊ ሂደቶችን አልፈው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችንም ያከናውናል። ኢትዮጵያ ባህላዊ መድሃኒትና ህክምና ቱሪዝሟን እንድታሳድግም የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ኩባንያው በቡና ዘይት የተለያዩ የቆዳ በሽታዎችን ለማከም ጥቅም ላይ ከማዋሉ በፊት ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ፍቃድ አግኝቷል። ይህም በዚህ ዘርፍ ፍቃድ ያገኘ የመጀመሪያው ኩባንያ ያደርገዋል። በተመሳሳይ የላብራቶሪ ፍተሻዎችን አልፎ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን የመድሃኒት ማረጋገጫ ፍቃድ አግኝቷል።

ዘመናዊ መድሃኒቶች መነሻቸው ባህላዊ መድሃኒቶች ናቸው። ስለዚህ ባህላዊ መድሃኒቶች ከዘመናዊ መድሃኒቶች ጎን ለጎን ጉዳት በማያስከትል መልኩ በህክምና ባለሞያዎችና በባህላዊ ሀኪሞች ንግግር መሰረት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። ኩባንያውም የበባህላዊ ህክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ የሚሰጠው የህክምና ወረቀት ተቀብሎና ታካሚው ከዚህ በፊት የነበረውን የህክምና ታሪክ መርምሮ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት የፋርማሲዩቲካል ኬሚስትሪና ፋርማኮግኖሲ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ቢኒያም ጳውሎስ እንደሚገልፁት የባህላዊ ህክምና በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያስቆጠረና ሁነኛ የጤና ችግሮች መፍትሄ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ቢሆንም ለዘርፉ እምብዛም ትኩረት ባለመሰጠቱ የታሰበለትን ግብ እየመታ አይደለም።

በኢትዮጵያ የባህላዊ ህክምና እውቀት የተደበላለቀ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት እውቀቱን ለማጎልበት የሚያስችሉ እድሎች በሃገሪቱ ባለመመቻቸታቸውና ህክምናው የሚሰጠው በባህላዊ ሃኪሞች ፍላጎት ብቻ በመሆኑ ነው። ባህላዊ ሃኪሞቹ ህክምናውን ለገቢ ምንጭነት ብቻ መጠቀማቸውና እውቀቱንም ከቤተሰቦቻቸው በዘለለ ለሌሎችም የማስተላለፍ ልምዳቸው ደካማ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ በየግዜው የሚተላለፈው የባህላዊ ህክምና እውቀት የተመዘገበና የጠራ አይደለም።

በማህበረሰቡ ዘንድ ከባህላዊ ህክምና ጋር በተያያዘ የተሳሳተ ግንዛቤ በመኖሩ ባህላዊ ሃኪሞችን የማግለልና የተለያዩ ስያሜዎችን የመስጠት ችግሮች በመኖራቸው እውቀቱ በጥቂት ባህላዊ ሃኪሞች ብቻ ተገድቦ ቀርቷል። አሁን ባለው ሁኔታም ወጣቱ ትውልድ ህክምናውን ተቀብሎ የመተግበርና እውቀቱን የማስቀጠል አዝማሚያው እየቀነሰ መጥቷል።

በሃገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ለባህላዊ መድሃኒትነት የሚያገለግሉ እፀዋቶችና የተለያዩ ባህላዊ እውቀቶች መኖራቸው ህክምናውን ለማሳደግ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታዩ ቢሆንም ለህክምናው በበቂ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ባለመሆኑ የታሰበውን አገልግሎት መስጠት አልተቻለም። በዘመናዊና ባህላዊ ህክምና ሃኪሞች መካከል ትውውቅ ባለመኖሩና ተግባብተው የሚሰሩበት ሁኔታ ባለመፈጠሩ ለባህላዊ ህክምና እድገት አንዱ ተግዳሮት ሆኗል።

ባህላዊ መድሃኒቶችን ለማሳደግ በመንግስትም ሆነ በግል የሚደረገው ጥረት አነስተኛ መሆኑንና ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ የባህላዊ ህክምና መመሪያዎችና ደንቦች በበቂ ሁኔታ አለመዘጋጀታቸው፣ አንዳንድ የባህላዊ ሃኪሞች ሞያቸውን በድብቅ ማከናወናቸውና ሌሎችም የባህላዊ ህክምና ተጨማሪ ተግዳሮቶች ናቸው።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የባህላዊ ህክምናን በሚፈለገው መጠን በማሳደግ ከዘመናዊ ህክምና ጎን ለጎን አገልግሎት ለመስጠት ህክምናውን ተቋማዊ ማድረግ ያስፈልጋል። በበላይነት የሚቆጣጠረውን አካልም መለየት ይጠይቃል። በዘርፉ ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ ሃኪሞችም እውቅና መስጠት ይገባል።

የባህላዊ ህክምና መድሃኒቶች በተለይም ፈዋሽነታቸው እንዲረጋገጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ ከሚመለከተው አካል ሊቀርብላቸው ይገባል። የባህላዊ ህክምናና መድሃኒት እውቀቶችን ለመጠበቅ የሚያስችል አስገዳጅ የህግ ማእቀፎችን በማዘጋጀትና ህክምናው በመደበኛ የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካቶ በዘርፉ ያሉ ሃኪሞች ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ህክምናውን የበለጠ ማሳደግ ይቻላል።

ለባህል ህክምና መንግስት የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ የማይቀጥል ከሆነና በዘመናዊ ህክምና ውስጥ ያሉ ባለሞያዎችም ለህክምናው ሳይንሳዊ ድጋፍ በማድረግ መድሃኒቶቹ እውቅና እንዲያገኙ ካልሰሩ ህክምናው እውቀቱ ባላቸው ግለሰቦች እጅ ብቻ ቀርቶ የታሰበለትን አስታዋፅኦ ሳያበረክት ሊጠፋ ይችላል። ይሁን እንጂ ለባህላዊ ህክምና በሚፈለገው ልክ ትኩረት በመስጠት ከዘመናዊ ህክምና ጋር አጣጥሞ ማስኬድ የሚቻል ከሆነ በሃገሪቷ የተሻለ የህክምና ስርዓት መፍጠር የሚቻልበትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እድል ይኖራል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You