ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተማሪዎች ዝግጅት

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አልፎ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መቀላቀል የተማሪዎች ህልም ነው። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የፈተና አሰጣጥ ሥርዓቱ ለኩረጃና ስርቆት የተጋለጠ እንደነበር ይነገራል። በዚህም በርካቶች ያልዘሩትን ሲያጭዱ ተስተውሏል።

በፈተና ስርቆት ሳቢያ ለሚደገመው ፈተና ሀገር ላልተገባ ወጪ ተዳርጋለች። በተማሪዎች ላይ ይዞት የሚመጣው ሥነ ልቦናዊ ጫና ቀላል የሚባል አልነበረም። በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል።

በዋናነት የፈተና ስርቆትንና ማጭበርበርን ለማስቀረት በኤሌክትሮኒክስ መስጠት እስከሚጀመር የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርሲቲ እንዲሰጥ አድርጓል። ይህም ተማሪዎች ትምህርት በጥናትና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀው በርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው የሚያስችል መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ታዲያ ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመስጠት ባለፈ የ2016 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በተመረጡ ከተሞች በኦንላይን እንደሚሰጥ አሳውቋል። ለፈተናውም ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፖችና ታብሌቶችን ጨምሮ ሌሎች ግብአቶችን የማሟላት ሥራ በስፋት እየሠራ ይገኛል።

ተማሪ ማዕዶት ብርሃኑ የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። እሱ እንደሚለው፤ ትምህርት ቤቱ የተለያዩ ለፈተና የሚያስፈልጉ የድጋፍ ትምህርት በመስጠት፣ ጥያቄዎችን በመሥራት፣ የሥነ ልቦና ዝግጅትና ስለ ኦንላይ ፈተና አወሳሰድ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ይናገራል።

በቤተ መጽሐፍት ቀደም ሲል የነበሩ የመማሪያ መጽሐፍትን ጨምሮ ፈተናዎችን እና አስፈላጊ ግብዓቶች መቅረባቸውን በመጥቀስ፤ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥያቄዎችን መሥራትና መርጃ መጽሐፍትን በማንበብ ለፈተናው የሥነ ልቦና ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳል።

ሌላዋ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜላት ደረጄ እንደምትገልጸው፤ በዘንድሮ በኦላይን ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂ ፈተና ትምህርት ቤታቸው ኦንላይ ፈተና አወሳሰድ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰጣቸው መሆኑን ነግራናለች። እሷና ጓደኞቿም በዌብሳይቶች አማካኝነት ልምምድ እያደረጉ ነው።

ትምህርት ቤቱ ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ተጨማሪ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን በመስጠትና ቤተ መጽሐፍትን በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ትናገራለች።

‹‹መምህራን ጥያቄዎችን በመሥራት፣ ያለፉትን ትምህርት ተመልሶ በማስተማር፣ የመለማመጃ ጥያቄዎች በማዘጋጀት ይረዱናል›› ስትል ገልጻለች።

እንደ ተፈታኝ ተማሪ የሚጠበቅባትን ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝና ከጓደኞቿ ጋር በጋራና በቤተ መጽሐፍት በማጥናት፣ ጥያቄዎችን በመሥራት፣ ለፈተና የቀረውን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም እየጣሩ እንደሚገኙ ታብራራለች።

‹‹አንድ ሰዓትም ቢሆን ያለ አግባብ መባከን የለበትም፤ ምክንያቱም ይሄ ብሔራዊ ፈተና ነው›› የምትለው ተማሪዋ፤ የትምህርት ቤቱ መምህራንም ተማሪዎቹ ያልገባቸውን ጥያቄዎችን በማስረዳት ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ታመለክታለች።

ዘንድሮ በኦንይን የሚሰጠው ፈተና የመጀመሪያ እንደመሆኑ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጻ፤በፈተና ወቅት የመብራት፣ኢንተርኔት፣የተለያዩ ችግሮች እንዳያጋጥሙ ሥጋት እንዳደረባትም ትልጻለች።

ዘንድሮ በኦንላይ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች በብቃት መውሰድ እንዲችሉ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወይዘሮ ቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኤፍሬም አይተንፍሱ ናቸው።

ርዕሰ መምህሩ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮው በኦንላይ ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ተማሪዎችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

ትምህርት ቤቱ በዘንድሮ ዓመት 185 የማህበራዊና 145 የተፈጥሮ ሳይንስ በድምሩ 330 ተማሪዎችን ለማስፈተን መዘጋጀቱን ይገልጻሉ። በዚህም ተማሪዎች የኦንላይ ፈተና አሠራር ሂደትን እንዲገነዘቡ በአይሲቲ መምህራን አማካኝነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ። በተለይም በባለፈው ዓመት የተሰጡ ፈተናዎችን በኦንላይን እንዲለማመዱ መደረጉን ይናገራሉ።

ለተማሪዎች የማጣቀሻ መጽሐፍትን የማቅረብ፣ የሥነ-ልቦና ድጋፍ፣ የኮምፒውተር አቅም ማሳደግ እና የትምህርት ይዘት ሽፋን እየተሰጠ ነው። መምህራንም ተማሪዎችን ለፈተና ብቁ ለማድረግ የሚያስችሉ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሚገኙ ያስረዳሉ።

ትምህርት ቤቱ ለፈተናው የሚያስፈልጉ የኮምፒውተር፣ የኢንተርኔትና የመብራት አቅምን የማሳደግና ግብዓት ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You