አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እያንዳንዱ የሃይማኖት ተቋም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳስቡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት 400 ከሚሆኑ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ሃይማኖቶች በአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሃይማኖት ተቋማት አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ርዕስ በርዕስ በመናበብ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባና በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ውይይቱ በተለያዩ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን፤ ይህም በአሁኑ ወቅት በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከል እየታየ ያለውን የመከፋፈል አዝማሚያ ለማስቀረት ጠቅላይ ሚንስትሩ ዶክተር አብይ ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ የሃይማኖት ተቋማት ያሏቸውን ልዩነቶች በማክበር የሚመሳሰሉባቸውን ጉዳዮች ለማጉላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም ለተከታዮቻቸው አርአያ ሊሆን የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ፈቃድ በሚያወጡበት እና በሚያሳድሱበት ጊዜ ያሉ ችግሮችን፣ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት በአብያተ ክርስቲያናት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታንና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተዋል። በአብያተ ክርስቲያናቱ እና ምእመኑ አንድነትና ሕብረት እንዲሁም ውስጣዊ ችግሮች ላይ ጥናት አድርጎ የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ 15 አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሯል።
በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአክሱም ሐውልት ጥገናና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ማብራሪያ የሰጡት የጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስት ኢማኑኤል ሲ ዴል ሪ እንዳሉት፤ የልዑካን ቡድኑ የአክሱም ሐውልት ያለበትን ሁኔታ እንደጎበኙና ቅርሱ ያለበትን ሁኔታ በመመልከት የጣሊያን ቴክኒካል ቡድን ሐውልቱ ዳግም ማደስ የሚቻልበትን መንገድ አጥንቷል፡፡
‹‹ የቅርስ ቦታዎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ልምድ አለን፡፡›› ያሉት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ልምዳቸውን በመጠቀም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል፡፡
በቻይና በተካሄደው ቤልት ኤን ሮድ ፎረም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከጣሊያኑ አቻቸው ጉሴፔ ኮንቴ ጋር የአክሱም ሐውል መልሶ የሚጠገንበት መንገድ ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ 2019 ሰኔ 10 ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአክሱም ከተማ በመገኘት ሐውልቱ ያለበትን ሁኔታ መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
በጋዜጣው ሪፖርተሮች