ተውልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) በአካውንቲንግ ተመርቃለች። ቀጣይ እቅዷ ሦስት ጉልቻ መቀለስ ሆነና ትዳር መሠረተች። ግን አልተሳካም። ትዳሯ መቀጠል ተሳነው። በፍቺ ምክንያት ልጆቿን ብቻዋን ማሳደግ ግድ ሆነባት። በአንድ ድርጅት ውስጥ ሂሳብ ሠራተኛ ሆና ተቀጠረች። የሚከፈላት ደመወዝ ግን ከልጆቿ የትምህርት ቤት ክፍያ ፈቀቅ የሚል አልሆነም። ለተሻለ ሕይወት ፍለጋ ስደትን መረጠች። እናቷና እህቷ ልጆቿን በአደራ ለማሳደግ ኃላፊነቱን ወሰዱ። እርሷም ወደ ደቡብ አፍሪካ አቀናች።
በሄደች በስምንተኛው ወር ልጇ ‹‹ሻሎም›› ታመመች። እናትና እህት ልቧ እንዲያርፍ ብለው ‹‹እኛ እናስታምማታለን አንቺ እዛው ቆዪ›› አሏት። የልጇ ሕመም ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ሄደ። አሁን ነገሮች እየባሱ ስለመጡ እናት ወደ አገሯ መምጣት እንዳለባት ተነገራት። ወደ ሀገሯም በሠላም ገባች። የልጇ ሕመም ግን ሠላም ነሳት። ልጇ የካንሰር ታማሚ መሆኗን ብታውቅም እንደምትድን እርግጠኛ ነበረች። አልሆነም፤ ልጇ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየቻት።
ይህን ችግር ያስተናገደችው ብርቱዋ ሴት ፌቨን ጋሻው ናት። ፌቨን በልጇ ሞት እጅጉን ተፈተነች። የሽንፈት ስሜት ተሰማት። በዚህ በኩል ደግሞ ‹‹አልተሸነፍኩም›› ስትል ራሷን ታበረታለች። በሰው ፊት ጠንካራ ለመምሰል ትሞክራለች። ነገሩ ተቃራኒ ነው። ብቻዋን ስትሆን ማልቀስ፣ ‹‹እንዲህ ቢሆንኮ እንዲህ ይሆን ነበር›› የሚለው ቁጭት እና ጭንቀቷ አየለ። እንቅልፍ ከዓይኗ ጠፋ። በድባቴ ተሰቃየች።
ለራሷ ‹‹ልጄ አልሞተችም።›› እያለች ካለችበት ነገር ለመውጣት ራሷን ማበርታት ጀመረች። በድጋሚ ወደ ደቡብ አፍሪካ ብታቀናም የእርሷ ሕይወት ለብዙ ሴቶች ትምህርት እንደሚሰጥ በመተማመን ወስና ዳግም ወደ እናት አገሯ መጣች። ‹‹የንጉሱ ሴት ልጆች የልማት፣ የማብቃት እና የበጎ አድራጎት ድርጅት›› የተሰኘ ድርጅትም መሠረተች። ድርጅቷን ከመመሥረቷ በፊትም ቢሆን የሱስ ተጠቂ የሆኑ ወጣቶችን ታስተምር የነበረችው ፌቨን ፤ ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላም በአራት ዘርፎች ሴቶችን የማሰልጠን፣ የማማከር አገልግሎት፣ የበጎ አድራጎት እና የሚዲያ ሥራ መሥራቷን ቀጥላበታለች።
የሱስ ሕይወት ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ዕድሜን፣ ቤተሰብን… ያሳጣል። ብዙዎች ወደ ሱስ የሚገቡት በአቻ ጓደኞቻቸው ግፊት እና ጉትጎታ እንዲሁም ፈተና ሲገጥማቸው ከችግራቸው ለመደበቅ ሲሉ ይመርጡታል። የፌቨንም ህይወት ከዚህ የተለየ አልነበረም። የ‹‹ነቃች››፣‹‹አሪፍ›› እና ‹‹አራዳ›› ለመባል ገባችበት። በወቅቱም ብዙ ነገሮችን አሳጥቷታል። ከቤተሰብ ጋር ያላትን ግንኙነት፣ የሰዎች እምነትና ክብር እንዳታገኝ፣ በሰዎች ዘንድ የተተወች አድርጓታል። በሱስ ሕይወት ውስጥ ያለች አንዲት ሴት ደግሞ ለቁምነገር፣ ለትዳር እና ለኃላፊነት እንዳትታጭ የሚያደርግ መሆኑን መገመት ቀላል ነው። ሱስ ማንነትን ያሳጣል። ተስፋ ያስቆርጣል። የሱስ ሕይወት በከበባ ተጀምሮ በብችኝነት የሚጠናቀቅ ሕይወት ነው።›› ስትል ትገልጸዋለች ፌቨን ።
ፌቨን ከዚህ ቀደም በገጠማት ተደራራቢ ችግር ራሷን ለመደበቅ እና ‹‹አራዳ›› ለመባል የገባችበት ሱስ ለመግባቱ እንደቀለላት መውጫው ጠፍቶባትም ያውቃል። ዋናው ነገር ለመተው መወሰን ነው። በመንፈሳዊም ይሁን ሕክምናውን ተከታትሎ መላቀቅ እንደሚቻል ታምናለች። ዋናው ግን ያንን ሕይወት መጥላት አለበት።ያን ጊዜ የሕክመና ባለሞያም ይሁን ፈጣሪ ይረዳዋል ትላለች። የቀደሞ ውሎዋን መሸሽ እና በፊት የነበሯትን ልምምዶች መቀየሯም ወደ ኋላ እንዳታይ አድርጓታል።
እንደ ፌቨን ሃሳብ፤ አንዳንድ ወላጆች ሴት ልጆቻቸው በሱስ ውስጥ ይኖራሉ ብለው በፍጹም አይገምቱም ወይም አያውቁም። ብዙዎቹ ግን በድባቴ እና በሱስ ሕይወት ውስጥ እየተዘፈቁ ይገኛሉ። ሴቶችም ራሳቸውን ‹‹ሱሰኛ ነን›› ብለው እንዳያጋልጡ ማሕበረሰቡ ያሸማቅቃቸዋል። ፌቨን በሱስ ሕይወት ብዙ ያሳለፈች ሴት እንደመሆኗ በሱስኝነት እና ድባቴ (ዲፕሬሽን) ላይ እየሠራች ትገኛለች። በዚህ ዓመት ለሴቶች ብቻ የሚሆን ከሱስ ማገገሚያ ቦታ ለማዘጋጀት አቅዳለች።
ፌቨን በአንድ ቀን ውሳኔ ብቻ ከሱስ ወጥታ ታውቃለች። በሂደት ያቆመችባቸው ጊዜያት ነበሩ። ከሱስ ለመውጣት ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ዋናው የተሻለ ሕይወት መኖር ነው የምትለው ጠንካራዋ ፌቨን፤ መንፈሳዊ ቦታ ብቻ ካልመጡ ወይም ወደ ሕክመና ካልሄዱ መዳን አይችሉም ማለት እንዳልሆነም ታሳስባለች። ዋናው ጉዳይ ውሳኔ እና በውሳኔ ላይ መጽናት ብቻ ነው። ነገር ግን በሱስ ውስጥ ያለ ሰው ‹‹በምን መንገድ ነው ከዚህ መውጣት የምችለው? ብሎ በሚገባ ማሰብ እንደሚኖርበት ታምናለች።
ፌቨን ከሱስ እና ከድባቴ ተላቃለች። በድጋሚ ትዳር መመሥረት ችላለች። ስለራሷ ከማሰብ ይልቅ ለብዙዎች ለመድረስ ሩጫ ላይ ናት። ጎጆ መቀለሷን ተከትሎ ‹‹ጎጆ መውጫ›› በሚል ዘመቻ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣በማረሚያ ቤቶች፣በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላሉ ሴት ተማሪዎች እስከ ሁለት ዓመት የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያዎችን በአዲሰ አበባ እና በክልሎች ድጋፍ አድርጋለች። ያለፈችባቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች ለብዙዎች ለማስተማር ‹‹የንጉሱ ሴት ልጅ ወርቃማ መንገዶች›› የተሠኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች። በቅርቡም ‹‹ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለምን? እስከ ምን›› በሚል ርዕስ ሁለተኛ መጽሓፏን አስመርቃ ለንባብ አብቅታለች።
ፌቨን ከሱስ እና ድባቴ ሕይወት ተላቃ ለብዙዎች በመድረሷ የደስተኝነት፣ የኩራት እና የአሸናፊነት መንፈስ እንድትላበስ አድርጓታል። በከባድ የሕይወት ፈተና ውስጥ ያሉ ወጣቶች ራሳቸው ላይ መጥፎ እርምጃ ለመውሰድ አስበው የእርሷን ታሪክ ሰምተው ሃሳባቸውን መቀየራቸውን ስትሰማ ‹‹እንኳንም ወደዚህ በጎ ሥራ ገባሁ›› ትላለች።
የጉድ ላክ የሱስ ማገገሚያ እና ስልጠና ማዕከል መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮናታን ሊዮን የሱስን መንገድ የጀመረው ገና ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ ነበር። ለ22 ዓመት በሱስ ሕይወት ውስጥ ነበር። በሱስ ምክንያት ጤናውን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን አጥቷል። ከሞት ተርፎ ለብዙዎች እየደረሰ እና ለወደፊት ብዙ እንደሚሠራ እድል ስለተፈጠረለት ‹‹እድለኛው ዮናታን›› የሚል ስያሜ ለራሱ አውጥቷል ። ዛሬ ላይ አደንዛዥ እጾች በመጠንም በአይነትም በዝተዋል። ከልክ በላይ ደስታን የሚሰጡ እጾችን መጠቀምም በተማሪዎች ዘንድ ተበራክቷል የሚለው ዮናታን፤ ሱስ የብዙ ቤት ችግር ሆኗል።ከሱስ ለመላቀቅ ውሳኔ እና በሚገባ አምነውበት ሲሆን ውጤታማ ያደርጋቸል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን እንደ እስር ቤት ያዩታል በማለት ልምዱን ያጋራል።
ዶክተር አስራት ሃብተ ጊዮርጊስ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም ሳይካትሪስት ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት ሱስ አብዝቶ ንጥረ ነገሮችን ከመጠቀም የሚመጣ ነው።በተለይም የአእምሮ ሕመም፣ እንድ ድብርት እና ጭንቀት ያለበት ሰው ለሱስ ሕመም የበለጠ ተጋላጭ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ በሚገጥማቸው ችግር የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም የችግራቸው መደበቂያ እና መሸሸጊያ አድርገው በመጠቀማቸው ወደ ሱስነት ደረጃ ይሸጋገራል።
ከሱስ ሕመም በሕክምና መዳን ይቻላል። ሕክምናው በዋናነት የሚያተኩረው የስነ ልቦና ሕክምና ወይም የንግግር ሕክምና ሲሆን ከሕክምናው ጎን ለጎን፤ የታካሚው ለመዳን ያለው ፍላጎት ብሎም ውሳኔው ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለውም የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስቱ እና ሳይካትሪስቱ ያብራራሉ ።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም