ስንመካከር ችግሮቻችን ከእኛ በታች ናቸው

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰላም በላይ የሚናፍቀውና የሚያስቀድመው ነገር የለም። ወጥቶ ሲገባ ሰለ ሀገሩ ሰላም ይጸልያል፤ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ይመኛል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብነው። ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው። ከዚህም አልፎ የውጭ ሀገር ዜጎች ምንም አይነት የባዳነት ስሜት ሳይሰማቸው እንደሀገራቸው እንዲኖሩ የሚፈቅድ ድንቅ ሕዝብ ነው።

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን የጎረቤት ሀገራት ችግር ውስጥ ሲገቡ ህይወቱን ጭምር በመክፈል በጎረቤት ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን መስዋዕት የሚሆን ሕዝብ ነው። በዚህም በሱዳን፤ በሶማሊያ፤ በላይቤሪያ፤ በሩዋንዳና ብሩንዲ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ሀገራቱን ማረጋጋት ችሏል። የሰላም አምባሳደር ተብሎም ዕውቅና አግኝቷል። በብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት ከሰላምና ከነጻነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኗል።

ሆኖም ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባህል እና እሴት ባፈነገጠ መልኩ ከእኔ ውጪ ማንንም አልይ የሚሉ ቡድኖች በየቦታው ብቅብቅ ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እነዚህ ቡድኖች በብሄር ስም በመቧደን ፍላጎታቸውን በነፍጥ ለማሳካት ሲወጡ ሲወርዱ ይታያሉ። ከእኔ በላይ ለብሄሬ ተቆርቋሪ የለም በሚል ጭንብል ተሸፍነው የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ ላይ ይገኛሉ።

ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል።

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓጉሏል፤ አለፍ ሲልም የሀገር ህልውናም አደጋ ላይ ወድቋል።

ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ስለሚገቡ፣ በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ግጭቶች በርክተው ይታያሉ።

እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የአገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለአገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል። በየጊዜው ከሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥ ዳጎስ ያለ ጥቅም ስለሚያገኙም ሰላም የሚለውን ቃል በሩቁ ይሸሹታል።

‹‹ብሄሬ ተበድሏል፤ ኃይማኖቴ ተገፍቷል፤ ወዘተ›› የሚሉ ትርክቶችን በመፍጠር ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ ኃሜትን በማስቀደም ከግጭት ውስጥ ለማትረፍ ዘወትር ይታትራሉ።

የማህበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ህዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ።

በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳፍ ተገዷል። እነዚህ ቡድኖች ባሉበት አካባቢ ሁሉ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ነው። መማርና ማስተማር ዘበት ነው። ታሞ ታክሞ መዳን አይታሰብም። ነግዶ ማትረፍ፤ ዘርቶ ማጨድም ቅንጦት ነው።

በኦሮሚያ ክልል በሸኔ ታጣቂ በአማራ ክልል ከፋኖ ጋር በተያያዘ በየጊዜው እየደረሱ ያሉት ኪሰራዎችም ይህንኑ የሚያስረግጡ ናቸው። እነዚህ ሁለት ኃይሎች ላለፉት ዓመታት ቆሜለታለሁ የሚሉትን ብሄር ሲዘርፉ፤ ሲያንገላቱና ሲገድሉ ተመልክተናል።

ከዚህ ድርጊታቸው የሚያስቆማቸው የጸጥታ ኃይል ሲመጣ ደግሞ ግብረ አበሮቻቸውን ሰብስበው በሰፊው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሰራዊታችንንም በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ በጣም ሰላማዊና ለሕግ ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም እንጂ የእነዚህ አካላት ድርጊት ሀገርን የማፍረስ አላማ ጭምር ያለው ነው።

ስለዚህም ሀገር በሰላም ውላ እንድታድርና እድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ እነዚህን የሰላም ጸሮች በጋራ መመከት ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የስልጣኔ አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና።

በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው። በተለይም በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ምክክር ከገባንበት የግጭት አዙሪት ውስጥ እንደሚያወጣን እምነት መጨበጥ ይገባል።

ምክክሩ የቀድሞ ችግሮቻችንን፤ አሁን ያሉት ችግሮቻችንን መፍቻና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳያጋጥሙን የመፍትሄ አቅጣጫን የሚጠቁመን መድህን መሆኑን መተማመን ይገባናል። በሀገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረትም እርሾ ሆኖ እንደሚያግዝ እምነት መጣል አለብን።

ሀገራዊ ምክክሩ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሲችል ነው። የምክክር ሂደቱ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ የሚጠይቅና ውጤታማነቱም በእያንዳንዳችን አበርክቶ ላይ የሚወሰን ነው።

እያንዳንዱ ዜጋ በቅድሚያ ሁሉም ነገር በንግግር እና በምክክር ይፈታል የሚል እምነት መጨበጥ ይጠበቅበታል ። ዘመናትን የተሻገሩ ጥያቄዎችም ሆኑ እነሱን ተከትለው የመጡ አለመግባባቶች በምክክር እና በውይይት እንደሚፈቱ እምነት መጨበጥ ይገባል።

በየትኛውም ጫፍ ያለ ኢትዮጵያዊ በዚህ የምክክር ሂደት መሳተፍና የመፍትሄው አካል መሆን ሀገርን ማዳን መሆኑን ሊረዳ ይገባል ። አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን ማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ይፈጥራል።

ነፍጥ ይዞ መነሳት ጊዜ ያለፈበት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ከ1966 አብዮት ጀምሮ ነፍጥ ባነሱ ኃይሎች ስትደማና ስትቆስል ቆይታለች። ለ50 ዓመታት የቆየው የግጭትና የጦርነት ታሪካችንም ዛሬ በምክክር ሊታደስ ይገባል። ብሄራዊ ምክክሩ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሃሳብ አለኝ የሚል የህብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን ያለምን ገደብ የሚሰጥበትና በመደማመጥ ጉዳዮች እልባት የሚያገኙበት በመሆኑ ወደ ግጭትና ጦርነት የሚገፋ አንዳችም ምክንያት የለም።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለዘመናት የቆየውን መገፋፋትና ጥርጣሬ በመግፈፍ በኢትዮጵያ አዲስ የሰላም አየር እንዲነፍስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፤ ስለምክክር አስፈላጊነትም ግንዛቤ ማስጨበጥ ችሏል።

ሆኖም በሀገራችን ያለው የሰላም መደፍረስ ጉዳይ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዳይሄድ እንቅፋት ሆኗል። እስከ አሁን በትግራይ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ስራውን ለማከናወን ችግሮች አጋጥመዋል።

በመሆኑም በቀሩት ጊዜያት መሰል ችግሮችን መልክ አስይዞ በፍጥነት ሁሉም ክልሎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ወደምክክር የሚመጡበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋልⵆ ግጭት ባለባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ካለሆነ በስተቀር በበርካታ የኢትዮጵያ ክልሎች አንጻራዊ ሰላም ስለሰፈነ ከህዝቡ ጋር በሰፊው ለመምከር የሚያዳግት ነገር የለም።

በአማራ ክልልም ቢሆን የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ የመጣ በመሆኑ በቅርቡ ወደ ምክክር ይገባል ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን አሁን ስራው ተጀምሯልⵆ ትግራይ ክልልም እንደዚሁ ስራዎች እየተሰሩ ነው፤ በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ መልክ ማስያዝ ከተቻለ በቀሪዎቹ ጊዜያት የታሰበውን ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ይቻላል።

ለዚህ ሁሉ ቁልፍ ነገሩ ግን እምነት መጨበጥ ነው። ችግሮቻችን የሚፈተቱት በምክክርና በውይይት ብቻ ነው ብሎ ማመን ግድ ይላል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው። ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ሕዝብ ነው። ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ መኖር ትልቁ እሴት ነው።

ይህ አኩሪ እሴት በየዘመኑ እየተሸረሸረ ቢመጣም ጨርሶውኑ ጠፍቷል ማለት አይቻልም። በመሆኑም ኢትዮጵያዊ እሴቶች ሙሉ ለሙሉ ተሸርሽረው ከመጥፋታቸው በፊት መመካከር ይጠበቅብናል። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። ስለኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ሊጨነቁ ይገባል። ፓርቲም ሆነ ስልጣን የሚኖረው ሀገር ሲኖር ነው።

የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት የሚገኘው ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንዳልሆነ ሁሉም ሊረዳ ይገባል። ለዘመናት የኖርንበት የግጭትና የጦርነት ታሪክ ሀገራችንን ቁልቁል እንደሰደዳት ማንም በቀላሉ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። ጦርነት ንፁኃንን ሲፈጅ፣ ንብረታቸውን ሲያወድም፣ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ሲያስከትልባቸው፣ የሀገርን ኢኮኖሚ ሲያደቅና ሲያዋርድ ነው ያየነው። በተለይም ነፍጥ እያነሱ የብሄር ጠበቃ ነኝ በሚሉ ቡድኖች አማካኝነት በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በተለያዩ ሥፍራዎች በርካቶች አልቀዋል፣ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ወድሟል።

በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል በሚካሄዱ ግጭቶችም ሀገር ሰላም አጥታለች። ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ተቸግረዋል፤ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ለገበያ ማቅረብ ተስኖታል።

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት ሀገር ናት። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት አለ። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት አላገገምንም ፤ሥራ አጥነት አሁንም አሳሳቢ ነው ፤ አሁንም ከድህነት ያልወጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ድርቅ ደጋግሞ እያጠቃን ነው።

ስለዚህም እነዚህን ችግሮች ለመሻገርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ለማምጣት ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሳሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመወያየት ባህልን ማዳበር ይገባል።

ከውይይት ይልቅ ፍላጎታቸውን በመሳሪያ ለማስፈጸም የሚከጅሉ ቡድኖችንም ሕዝቡ ዕውቅና ሊነፍጋቸው ይገባል። ማንም ተነስቶ የብሄር ጠበቃ ነኝ ባለ ቁጥር አምኖ መቀበል ይብቃ። በብሄር ስም ራሳቸውን እየሾሙና እየሸለሙ ሕዝቡን ለመከራና ለስቃይ የሚዳርጉ ቡድኖች ታሪክ ሊቋጭ ይገባል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ነፍጥ የሚነሳ ሳይሆን ሃሳብ የሚያንሸራሽር ዜጋ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሻው በጠመንጃ ከሚማርክ ይልቅ በሃሳብ የሚማርክ ትውልድ ነው። ስለዚህም ጊዜው የምክክርና የውይይት በመሆኑ ነፍጥ ያነገበ በሙሉ ነፍጡን አስቀምጦ ለውይይት ልቡን መክፈት አለበት።

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ግንቦት 22/ 2016 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You