አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ተቀጥረው የሚሠሩ ከ120 ሺ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች የፐብሊክ ሰረቪስ ሳምንት በዓልን ምክንያት በማድረግ ነገ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ሊሰጡ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ፍሬህይወት ገብረህይወት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የፐብሊክ ሰርቪስ ሳምንትን በመዲናዋ በተያዘው ዓመት ለስድስተኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
ከአሁን በፊት የከተማ አስተዳደር ሠራተኞች በዓሉን ሲያከብሩ የነበረው የተለያዩ ግምገማዎችን፣ ውይይቶችን እንዲሁም ስብሰባዎችን በማድረግ ሲሆን፤ ዘንድሮ ግን ሥራ በማይኖርበት ቅዳሜ ዕለት ለከተማዋ ነዋሪ አገልግሎት በመስጠት አክብረው የሚውሉ ይሆናል፡፡
በዓሉን የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማበረታታትና የሥራን ክቡርነትን ለማሳየት በማሰብ ነገ በመዲናዋ ከ120 ሺ በላይ የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ተገኝተው በመደበኛው የሥራ ቀናት የሚሰጡትን አገልግሎት በበጎ ፈቃደኝነት ለመዲናዋ ማህበረሰብ አገልግሎቱን ለመስጠት እንደተዘጋጁ ገልፀዋል።
ዓላማው የመንግሥት ሠራተኛው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ባህሉን ለማሳደግ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተሯ፤ ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ሰኔ 16 ቀን የመዲናዋ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት <<ሆ>> ብሎ በመውጣት ለውጡን እንደሚደግፍ ያሳየበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰው፤ ስለዚህ የዛሬ ዓመት በዚህ ወቅት የመዲናዋ ህዝብ ለውጡን ደግፎ ላሳየው አንድነት የፐብሊክ ሠራተኛው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ምስጋና ለማቅረብ ታሳቢ የተደርገ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ሶሎሞን በየነ