ለብዙዎች የዓይን ብርሃን መመለስ ምክንያት የሆኑት ሐኪም

የምሁር ዕውቀት የሰዎችን ኑሮና አኗኗር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ፤ ስለዚህ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው፡፡ ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ለዚህ ቃል ብቁ ሆነው የተገኙ ጥቂት የሚባል ቁጥር የሌላቸው በስራና በሙያቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ችግር መፍትሔ ይዘው በመምጣት መድረስ የቻሉ ዕንቁዎች አሉ። ከእነዚህም የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር የዓይን የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሚታወቁት ዶክተር ጌትነት ንጉሴ አንዱ ናቸው፡፡

ዶክተር ጌትነት ንጉሴ ባለፉት 30 ዓመታት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በመዘዋወር የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖቻቸውን ብርሃን በመመለስ ሙያዊ ግዴታቸውን የተወጡ ሰው ናቸው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከሀብታም፣ እስከ ድሃ፣ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከአርሶ አደር እስከ ነጋዴ፤ ከሙስሊም እስከ ክርስቲያን ወዘተ ዶክተር ጌትነት ሁሉንም አይነት ወገኖቻቸውን በነፃ በማገልገል የዓይን ብርሃናቸውን መልሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ አካባቢ የተወለዱት የ53 ዓመቱ ሐኪም ዶክተር ጌትነት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፈለገ ህይወት፤ በየካቲት 23 እና ከዚያም በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡ ከትምህርት ቤቱ ጎበዝ ተማሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ዶክተር ጌትነት፤ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው የህክምና ትምህርት ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመግባት ከ7 ዓመታት በኋላ በጠቅላላ ሐኪምነት ተመርቀዋል፡፡

የመጀመሪያ የሥራ ዓለምን የተቀላቀሉት በመርሀ ቤቴ አለም ከተማ ነበር፤ አዲስ አበባ ለዚያውም መርካቶ አካባቢ ተወልዶ ላደገና ከከተማ ወጥቶ ለማያውቅ ሰው አለም ከተማን በቀላሉ መልመድ ከባድ ነበር። መብራትና ውሃ እንደ ልብ ባልነበረባት አለም ከተማ በየጊዜው የሚመደቡ ሀኪሞች አይበረክቱባትም ነበር፤ ዶክተር ጌትነትም ተመድበው እንደሄዱ የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደ ሌሎች ሀኪሞች ተማረው ለቀው እንዳይሄዱ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር የተቀበሏቸው፤ እየዋለ ሲያድር የእዚያ ገጠር ሕዝብ ችግርን በሙያቸው መጋፈጥ ጀመሩ።

ለራሳቸውም ቃል ገቡ፤ ለ3 ዓመት በአለም ከተማ ሲቆዩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህል አጠኑ፤ እንደ ባህል ከተያዙ ጉዳዮች መካከል ልጆችን ክትባት ማስከተብ አልተለመደም፤ ዶክተር ጌትነት ቦታው ላይ ሲሄዱ በአካባቢው ከሚወለዱ ሕፃናት 36 ከመቶ ብቻ ነበሩ የሚከተቡት፤ ይህንኑ ችግር በመመልከት ‹‹ሜንሽን ፎር ሜንሽን›› ከተባለው የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባባር ፕሮጀክት በመቅረፅ የአካባቢውን የክትባት መጠን ‹ከ36 ከመቶ ወደ አንድ መቶ ከመቶ አደርሰዋለሁ› ብለው ለክልሉ ጤና ቢሮ እቅድ አስገቡ፤ የክልሉ ሰዎች ‹ሊሆን የማይችል እቅድ!!› በሚል ስሜት ቢቀበሉትም እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት አልነበራቸውም፤ ግን የጠየቁትን በጀት ፈቀዱለቸው፤ በዓመቱ ግን የአካባቢው ህብረተሰብ የሕፃናት ክትባት ምጣኔ 106 በመቶ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ፤ በወቅቱ የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ዶክተር ጌትነት እውቅና አገኙ።

ከመርሀ ቤቴ ወደ ደብረ ብርሃን ተዛውረው ለ3 ዓመታት ያህል የሰሩት ዶክተር ጌትነት፤ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ተወልደው በአደጉበት በአዲስ ከተማ አካባቢ የግል ክሊኒክ ከፈቱ፤ ክሊኒኩ ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም አትራፊ ሆኖ ሊቀጥል አልቻለም፤ ክሊኒኩ አትራፊ ሊሆን ያልቻለው የሚያስከፍለው ክፍያ እንደ መንግሥት ሆስፒታል በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ ሰዎች በየዕለቱ በነፃ ህክምና በመስጠቱ ነበር።

ክሊኒኩ ሲዘጋ ዶክተር ጌትነት ከጠቅላላ ሀኪምነት የዓይን ህክምና በመማር የዓይን ስፔሻሊስት ሀኪም ሆኑ፤ የጠፋውን የወገኖቹን ዓይን የማብራት ተግባሩን ‹ ሀ ›ብሎ የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖቹን ለመርዳትም ከኦርቢት ኢንተርናሽናል ጋር ይገናኛሉ፤ ኦርቢስ በገጠር አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ የዓይን ህክምና ይሰጥ ስለነበር ለዶክተር ጌትነት ዓይን የማብራት ፍላጎታቸውን አሳካላቸው።

የመጀመሪያ ጉዟቸው ወደ ወልቂጤ ነበር፤ የ300 ሰዎች ዓይን ቀዶ ጥገና በማድረግ ብርሃናቸውን መለሱ፤ እንደገና በወሩ እዚያው ወልቂጤ ተጨማሪ 300 ሰዎች በድምሩ ለ600 ሰዎች ህክምና አደረጉ፤ ለዓመታት ዓይነ- ስውር ሆነው በመንገድ መሪና በረዳት ተቸግረው የነበሩ ሰዎች ዓይናቸውን ታክመው ዓይናቸው ሲበራ ፊታቸው ላይ የሚያዩት ደስታ ሥራቸውን ይበልጥ እንዲቀጥሉ አደረጋቸው።

በወልቂጤ የተጀመረው የአይን ብርሃን የማብራት ህክምና ላለፉት 30 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በመዟዟር ለተቸገሩና ብርሃን ላጡ ወገኖች ብርሃን መሆን ችለዋል፤ ጉራጌ ዞን ቸሃ፣ ሀላባ፣ ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሶማሌ ደገሃቡር፣ ጂግጂጋ፣ ቀብሪ ደሃር ሐረር፣ ደሴ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ወልዲያ፣ ጎዴ፣ አሰበ- ተፈሪ፣ አሳይታ፣ አሰላ፣ ፍኖተ- ሰላም፣ ደብረ ታቦር ወዘተ የአይን ብርሃን የማብራት ሥራውን ኑሯቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርገው ለብዙዎች ተስፋ ሰጥተዋል፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከ600 እስከ 1200 ድረስ ሰዎች ህክምናውን ያገኙ ነበር።

ዶክተር ጌትነት በመጀመሪዎቹ ሁለት ዓመታት በገጠር እየዞሩ ህክምናውን ሲሰጡ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ገቡ፤ የዓይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ሆነው በአስተዳደርም በህክምና ሥራ ለ7 ዓመታት ያህል ቆዩ፤ በወቅቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ለዓይን ህክምና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች በወቅቱ የሚሰጣቸው ቀጠሮ 2 ወር ከ15 ቀን ነበር፤ ዶክተር ጌትነት ክፍሉን በበላይነት መምራት ከጀመሩ በኋላ ግን ከሀኪሞች ጋር በመነጋገርና ፕሮግራም በማውጣት ዛሬ የመጣ ሰው ነገ ቀጥሮ ተሰጥቶት ታክሞ አይኑ በርቶ ወደ ቤተሰቦቹ እንዲሄድ ማስደረግ ችለዋል።

የተበላሹ የሆስፒታሉ የህክምና መስጫ መሳሪያዎችንም ከኪሳቸው አውጥተው በማሰራት የህክምና ሂደቱ እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥረት አድርገዋል፤ ሐኪሞች ከመደበኛ የሥራ ሰዓታቸው በኋላ በዚያው በሆስፒታሉ ውስጥ በተወሰነ የክፍያ ለውጥ ህክምና እንዲሰጡ የተደረገውም ዶክተር ጌትነት ምኒልክ ሆስፒታልን በሚመሩበት ወቅት ነበር፡፡ ሰዎችን ከማከሙ በተጨማሪ የህክምና ቡድን አደራጅተው ከላየንስ ክለብ ጋር በመተባበር ወደ ገጠር እያቀኑ የብዙዎችን የዓይን ብርሃን መልሰዋል።

ዶክተር ጌትነት የህክምና ቡድኑን ይዘው የዓይን ሞራ ህክምና ወደሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራም መሰረት ሲሆን፤ በመንግሥት ሆስፒታል እዚያው አካባቢ በሚገኙ ሐኪሞች በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ተመዝግበው እንዲዘጋጁ ያደርጋሉ፤ ህክምናውም የሚሰጠው በመንግሥት ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ከህክምናው በኋላ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ህመምተኞች የሆስፒታሉ ሀኪሞች እንዲከታተሏቸው እድል ይሰጣል፤ በመሆኑም ቡድኑ በቦታው ሲደርስ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ በቀጥታ ወደ ቀዶ ጥገናው ነው የሚገባው፤ በቀን ከ60 እስከ 80 ሰዎችን በአንድ የጉዞ ፕሮግራም እስከ 800 ሰዎችን የሚያክሙት ዶክተር ጌትነት ቀዶ ጥገና የተደረገለት ሰው ዛሬ ተሰርቶለት ነገ ዓይኑ ስለሚበራለት በሰው ድጋፍ የመጡ ሰዎች እየጨፈሩ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ መመልከት ስራውን እንድወደው አድርጐኛል ይላሉ።

ያም ሆኖ የመንግሥት ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጠው ለተላላፊ በሽታዎችና ገዳይ ለሚባሉ በሽታዎች በመሆኑ ለእንደዚህ ዓይነት የዓይን ህክምና ጉዳይ የሚይዘው በጀት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ህብረተሰቡም የዓይን ሞራ ግርዶሽ በህክምና በቀዶ ጥገና የሚስተካከል መሆኑን ስለማያውቅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ዓይናቸው ጠፍቶ ከምርታማነት ውጪ ሆነዋል ይላሉ።

ይህንን ችግር ለመፍታትም ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ከለጋሾች ጋር በመተባባር መንግሥት ብሄራዊ የዓይነ-ስውርነት ማስወገጃ ኮሚቴ በመመስረት ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ተሞክሯል፤ የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ጌትነት፤ በዚህ በኩል ህክምና የማግኘት እድሉ ያልነበራቸው የገጠር ነዋሪዎች ህክምናውን በነፃ እንዲያገኙና ብርሃናቸው እንዲመለስ አድርገዋል፡፡

ዶክተር ጌትነት የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች ብርሃናቸው ተመልሶ ማየት ሲችሉ የሚያሳዩት ድርጊት እየማረካቸው ሲመጣ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸውን ሰዎች ከህክምናው በፊትና በኋላ ቪዲዮ ማስቀረፅ ጀመሩ፤ በዚህ መልክ ከሰሯቸው ከ22 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል ከ1500 በላይ የሚሆኑ ባለ ታሪኮችን በቪዲዮ አስቀርጸው ይዘዋል፡፡ ብዙዎቹ በሰዎች ድጋፍ ሲመጡ የሚታዩ ሰዎች ቃለ- ምልልስ ሲደረግላቸው ዓይናቸው የሚበራ አይመስላቸውም፤ ህክምናው ተሰጥቷቸው ዓይናቸው ሲፈታ ደግሞ የሚታየው ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነው፤ ዶክተር ጌትነት ህክምናውን ሰርተው ዓይናቸውን ሲፈቱላቸው በአንዳንድ ሰዎች ድርጊት አብረው ያለቅሱ ነበር።

ድምፃቸውን አጥፍተው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየዞሩ የዓይን ብርሃን ላጡ ወገኖቹ ብርሃን ሲሰጡ የኖሩት ዶክተር ጌትነት ልታይ ልታይ የማይሉ ብርሃናቸው በተመለሰላቸው ሰዎች ደስታ የሚደሰቱ በጎ አድራጊ ናቸው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ስላከናወኗቸው የበጎ አድራጎት ተግባራትም ከ53 በላይ የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በርካታ ምስክር ወረቀቶችና ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

በአይን ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ቢያንስ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አይነ ስውራን ሰዎች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 50 ከመቶው ሊታከም በሚችለው በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡ በዶክተር ጌትነትና ሌሎች በጎ አድራጊ ተቋማት በየጊዜው በሚደረገው በየጊዜው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ቁጥሩን ለመቀነስ ጥረት ቢደረግም ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም የሚሄደው፡፡

የዚህ ምክንያት ደግሞ ከዚህ በፊት በህክምና እጦት በአይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር እንዳለ ሆኖ ከስር ከስር ደግሞ በየዓመቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡ በመሆኑ ነው። እድሜ ሲጨምር አይን በሞራ የመጋረድ እድሉ ሰፊ ስለሆነ ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ይነገራል።

በግላኮማ፤ በስኳር፤ በደም ግፊትና በልዩ ልዩ በሽታዎች ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ያም ሆኖ በህክምና እርዳታ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህመም ተጠቂዎችን ዶክተር ጌትነትና የሥራ ባልደረቦቻቸው ኑሮአቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርገው ብርሃን ላጡ ብርሃን እየሆኑ ነው፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት በሀገራችን የዓይን ሐኪሞች ቁጥር ከ120 በላይ አይደለም፤ያም ሆኖ ግን በግለሰብ ደረጃ ለ22 ሺህ ሰዎች ብርሃናቸውን መመለስ የውቅያኖስን ውሃ በማንኪያ ቢመስልም ጉዳዩ የዓይን ጉዳይ መሆኑ ሲታሰብ የዶ/ር ጌትነት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡

እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት ሙያና የሥራ ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ እውቁን የአይን ህክምና ባለሙያ ዶክተር ጌትነት ንጉሴ ላበረከቱት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ አመሰገንን። ሰላም!

ለዚህ ጽሑፍ በምንጭነት ተወዳጅ ሚዲያ ድረ ገፅን ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

 

 

Recommended For You