አዲስ አበባ፤ በአገር አቀፉ ደረጃ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመጪው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ከሁለት መቶ ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ መታቀዱን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ጨበቃ ቀበሌ የችግኝ ተክላ መርሃ ግብር ትላንት አካሂዷል።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አነሳሽነት በአገር አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለአገሪቱ የሚያበረክተው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካ ፋይዳ በርካታ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
ለአብነት የሃይል ማመንጫዎች አስፈላጊውን ውሃ እንዲያገኙ እና በደለል እንዳይሞሉ መከላከልን ጨምሮ በአጠቃላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠው ሃላፊነት ስኬታማ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡
ትሩፋቱ በርካታ የሆነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአንድ ሰሞን ተግባር ብቻ እንደማይሆንና በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፤ በመጪው ሐምሌ መጀመሪያም በአገር አቀፍ ደረጃ ከሁለት መቶ ሚሊየን በላይ ችግኞን ይተከላሉ ብለዋል፡፡ ሐምሌ አንድ ቀን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ችግኝ የሚተከልበት ቀን መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አዲስ ታሪክ ሆኖ በክብረ ወሰንነት ሊመዘግብበት የሚችለበት ዕድል እንደሚኖርም አመላክተዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መሳተፍ ብቻም ሳይሆን የፅድቀት መጠናቸውን በየጊዜው እንደሚከታተልም አስረድተዋል።
የውሃ መስኖና ኢንርጂና ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት ወልደሃና በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም መሰል የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ቢካሄዱም ለፅድቀታቸው አስፈላጊው ክትትል ሰለማይደረግ በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ መሆን አለመቻሉን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ይህን ለማስተካከል ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
«በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መትከል ብቻ ሳይሆን አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ ከተቻለ፤ በቀጣይ አምስትና አስር ዓመታት የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን» ብለዋል።
በሌላ ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ 10 እስከ 13 በአዲስ አበባ የተካሄደው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የታለመለትን ዓላማ ያሳካና በርካታ ጠቃሚ ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን ሚኒስቴሩ ትላንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በውሃና ኢነርጂ ሳምንት ከአንድ ሺ በላይ ተሳታፊዎች መታደማቸውና 88 የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ታምራት ተስፋዬ