ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው:: ሁሉም ሰው አንድ አይነት ምንነትና ማንነት እንዲኖረው አይጠበቅም:: እንዲያውም በሠለጠነው ዓለም ትልቁ የልዕልና መገለጫ ልዩነትን ማክበር ነው:: የሠለጠኑ ናቸው በሚባሉት የምዕራባውያን ሀገራት አንዱ መገለጫ የግለሰቦች ልዩነት መከበር ነው:: አንድ ሰው ፍላጎቱ ያዘዘነውን ነገር ሲያደርግ ማንም ከምንም አይቆጥረውም ማለት ነው:: ይህ የሰዎችን መብት ማክበር የሰው ልጅ የልዕልና መገለጫ ነው::
የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩነት ግን አደገኛ ልዩነት እየሆነ ነው:: የልዕልና ልዩነት ሳይሆን የጥላቻ ልዩነት፣ የመሠልጠን ልዩነት ሳይሆን የኋላቀርነት ልዩነት፣ የደግነት ልዩነት ሳይሆን የክፋት ልዩነት… እየሆነ ነው:: ልዩነት ውበት የሚሆነው የሌላውን ልዩነት (መብት ማክበር ሲኖረው ነው:: እነዚህ አደገኛ ልዩነቶች በተለይም የተማረ ነው በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ በስፋት እየተንፀባረቁ ነው::
ለምሳሌ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችን የሚጠቀመው የተማረ የሚባለው ክፍል ነው:: ዲጂታል ሚዲያዎች የግለሰብ ነፃነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው:: አንድ ሰው በውስጡ የሚሰማውን ነገር ያለምንም ገደብ የሚናገርበት ነው:: ስለዚህ የእነዚያ ሰዎች የውስጥ እምነት ያ የሚያንፀባርቁት ነገር ነው ማለት ነው:: በሌላ ቦታ (በዋናዎቹ ሚዲያዎች፣ በስብሰባ፣ በመድረኮች…) እንደዚያ ማለት ስለማይችሉ እንጂ የልባቸው እምነት ያ ነው ማለት ነው:: ልዩነት በጣም ሲሰፋ ይከራል፣ ሲከር ደግሞ ይበጠሳል ማለት ነው::
ብዙ ጊዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ ሁለት የኢትዮጵያ መሪዎች ፎቶ ይደረግና ‹‹ማን ይሻላል?›› የሚል ጥያቄ ይጠየቃል:: ነገርየው ለቀልድና ጨዋታ ተብሎ የሚደረግ ተራ እና ቀላል ጥያቄ ቢሆንም ግብረ መልሶች ግን የተማረ የሚባለውን ክፍል አስተሳሰብ ያንፀባርቃሉ:: ይህን ለማስተዋል የግድ በሆነ ፋውንዴሽን ወይም በዓለም አቀፍ ተቋም የሚሠራ ጥናት መጠበቅ አያስፈልግም:: ብዙዎች የውስጥ አስተሳሰባቸው በእነዚህ ቀላል ነገሮች ውስጥ ይንፀባረቃል::
መለስ ዜናዊን የሚያደንቅ ሰው ዶክተር ዐቢይን ‹‹እንዴት ከዚህ ሰይጣን ጋር ታነፃፅራለህ?›› ይላል:: ዶክተር ዐቢይን የሚያደንቅ ደግሞ መለስ ዜናዊን ‹‹እንዴት ከዚህ ሰይጣን ጋር ታነፃፅራለህ?›› ይላል:: ከሳይንስም ከሃይማኖትም፣ ከሞራልም የተጣላ የጥላቻ ሃሳብ ነው:: እንዲህ አይነት ሰው የአቶ መለስ ዜናዊን ብቃት ወይም ድክመት ከዶክተር ዐቢይ ብቃት ወይም ድክመት ጋር ማነፃፀር ስለማይችል ያለው አማራጭ ከሳይንስም ከሃይማኖትም የተጣላ የጥላቻ ስድብ መሳደብ ብቻ ነው::
ሃጫሉ እና ቴዲ አፍሮን በሙዚቃ ሥራዎቻቸው እያነፃፀረ የሃጫሉ ዜማው እንዲህ ነው፣ ግጥሙ እንዲህ ነው፤ የቴዲ አፍሮ ዜማው እንዲህ ነው፣ ግጥሙ እንዲህ ነው… ቅንብሩ ምናምን እያለ ማወዳደር አይችልም:: የሚችለው የአንደኛው አድናቂ የዚያኛውን አድናቂዎች መሳደብ ነው:: እሱ የሚያደንቀውን ቅዱስ ያኛውን ሰይጣን ማድረግ ነው:: ታዲያ ይህ ልዩነት ‹‹ውበት›› የሚባል ነው?
ይህ የትንንሽ ነገሮች የሰፋ ልዩነት ወደ ፖለቲካውም አደገ:: በፖለቲከኞች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና ምድር ያህል የተራራቀ ነው:: ለምሳሌ፤ በትጥቅም ሆነ በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን የሚታገሉ ኃይሎች አሉ:: የሚገርመው ግን ከመንግሥት ጋር ካላቸው ልዩነት ይልቅ እርስ በእርሳቸው ያላቸው ልዩነት ይበልጣል:: አንደኛው ታጋይ ኃይል ቢያሸንፍ ታግሎ ከጣለው መንግሥት የከፋ ተቃዋሚና ታጋይ ያጋጥመዋል:: አንዱ ተቃዋሚ ከሌላኛው ተቃዋሚ ጋር ወደ ጦርነት የሚወስድ ልዩነት ያላቸው ናቸው:: ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ፤ እጅግ ኋላቀር የሆነ አመለካከት ስላለን ነው::
በሀገራችን እንደ ዕውቀት የሚታየው የግሪክ ፈላስፎችን ጥቅስ መደርደር፣ እና የተሸመደደ ‹‹ቲዎሪ›› ማነብነብ ነው:: ወደ ሥልጣኔ የሚወስደው ግን ቅንነትና የሞራል ልዕልና ነው:: አለበለዚያ የዲግሪ መዓት መደርደር፣ ከኢንተርኔት የተገለበጡ ጥናቶችን እያሳተሙ መደርደሪያ ማሞቅ ምሁር አያሰኝም::
አንዳንድ ጊዜ የሞራል ልዕልናን ልብ ብላችሁ ታውቃላችሁ? የተማረ ከሚባለው ይልቅ ፊደል ያልቆጠረው የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ የሞራል ከፍታ አለው:: ለሠለጠነው ዓለም ሥነ ልቦና የሚቀርበው በኢትዮጵያ የተማረ ከሚባለው ይልቅ ምንም ያልተማረው ገበሬ ነው:: ለእንስሳት ሕይወት ይቆረቆራል:: የቤት እንስሳት ሲታመም ውስጡ ይረበሻል፣ የቤት እንስሳት ሲሞት ያለቅሳል:: ይህን የሞራል ልዕልና የምንሰማው የሠለጠኑ ናቸው በሚባሉት ሀገራት ነው:: የሰውን መብት አልፈው የእንስሳት መብት ተሟጋች አላቸው:: ሕይወትን ማጥፋት ነውር ነገር ነው::
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ‹‹በለው! ግደለው!›› ሲል ትንሽ አይሰቀጥጠውም:: ‹‹የእነ እገሌን ዘር ማጥፋት ነው!›› እያለ የሚናገረው የተማረ የሚባለው ነው:: በዚህ ልክ ልዩነታችን ለምን ሰፋ?
የሚገርመው እኮ ደግሞ የሠለጠኑ ናቸው ከሚባሉት ሀገራት በላይ ሠብዓዊነት ያለውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው:: ለሞተ አስከሬን ክብር የሚሰጥበት፣ ‹‹ውሃ አይነፈግም›› የሚባልበት፣ ‹‹ቤት ለእንግዳ ነው›› የሚባልበት ባህልና ወግ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም:: በአውሮፕላን አደጋ ወይም በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ምንም ለማያውቋቸው ሰዎች ደረታቸውን እየደቁ የሚያለቅሱ እናቶች ያሉት ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን አይቀርም:: ሶሪያ ውስጥ ለደረሰ ዘግናኝ ጥቃት ‹‹አታሳዩኝ›› እያሉ ፊታቸውን የሚያዞሩት፣ ዓይናቸውን የሚጨፍኑት ‹‹እርም›› የሚባል የሞራል ልማድ ስላለ ነው:: የጋራ የሆነ የሰው ልጅነት ስላለ ነው:: ምንም ሰው የሌለበት አንድ ሕንጻ ቢደረመስ ምናልባትም ሳቅ ነው የሚሳቀው:: ምክንያቱም ሰው አይደለም:: ችግሩ ግን ለማያውቁት ሰው በሰውነት ብቻ የሚያለቅሱ እንዳሉ ሁሉ በሰው ሞት የሚስቁና የሚደሰቱም አሉን:: ለምን ይሆን ልዩነታችን እንዲህ የሰፋው?
በየትኛውም የሠለጠነ ዓለም ቢሆን በሰዎች መካከል ልዩነት አለ:: ልዩነቱ ግን የኢትዮጵያን ያህል የተራራቀ ነው ማለት አያስደፍርም:: ልዩነታቸው ግለሰባዊ መብትና ነፃነት ላይ፣ ግለሰባዊ ፍላጎት ላይ እንጂ ሰዋዊ ሞራል ላይ አይደለም:: በአንድ ዘፋኝና በሌላ ዘፋኝ መካከል ያለው ልዩነት ሙያዊ ልዩነት እንጂ የሰይጣንና የቅዱስነት ልዩነት አይኖራቸውም:: የግል ፍላጎታቸው የፈቀደውን ነገር ያደርጋሉ እንጂ ሌሎች ላይ ጉዳት የሚያደርስን ነገር እንደ መብት ሊያዩ አይችሉም:: ልዩነታቸው የማስተካከል እንጂ ቀዶ የመጣል ወይም ጫፉ አይነካም የሚል አይደለም:: ራሳችንን የሠለጠኑ ናቸው ከሚባሉት ሀገራት አንፃር እንየው ከተባለ በጣም የሰፋ ነው::
ልድገመውና፤ ልዩነት አይኑር አላልኩም:: ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው:: ልዩነት ሲባል የግድ ከባህል፣ ቋንቋና ማንነት ጋር ያለውን ማለት አይደለም:: ሞራል ባለው እና ሞራለ ቢስ በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማለቴ ነው:: ነውር በሚያውቅና ሀፍረተ ቢስ በሆነው መካከል ያለው ልዩነት ማለቴ ነው:: አዛኝ እና ጨካኝ በሆነው መካከል ያለው ልዩነት ማለቴ ነው:: በአጠቃላይ ሞራል ባለውና በሌለው መካከል ያለው ልዩነት ለምን ሰፋ?
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2016 ዓ.ም