አዲስ አበባ፡- የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ አካል የሆነው የኮካ ኮላ ፋብሪካ በኢትዮጵያ አራተኛና ትልቁን ፋብሪካውን በሰበታ ከተማ ለመክፈት በ2 ቢሊየን ብር የግንባታ ሥራውን በይፋ አስጀመረ፡፡
ካምፓኒው ከሰበታ ከተማ በተረከበው 14 ነጥብ ሦስት ሄክታር መሬት ላይ በኢትዮጵያ ትልቁን የኮካ ኮላ ፋብሪካ ለመክፈት የግንባታ ሥራው መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ወቅት ግንባታው በሁለት ምዕራፍ እንደሚጠናቀቅ አሳውቋል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ የፕላስቲክ መጠጦች ፋብሪካ ግንባታ የሚከናወን ሲሆን፤ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የጠርሙስ መጠጦች ፋብሪካ እንደሚገነባ አሳውቋል፡፡ ፋብሪካዎቹ በአጠቃላይ በ2 ቢሊየን ብር እንደሚገነቡና ለአንድ ሺ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር ሃላፊ አቶ አህመድ ቱሳ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰበታ ለአዲስ አበባ ቅርበት ያላትና ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን በመጥቀስ የከተማዋ ምልክት የሆነውን አንጋፋውን የሜታ ቢራ ፋብሪካን ጨምሮ ከሰባት መቶ የሚበልጡ ፋብሪካዎች በከተማዋ መገኘታቸውን አስታውሰዋል፡፡
ይህ የኮካ ኮላ ፋብሪካም ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንና አገሪቷ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር አቅም እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ የግል ባለ ሀብቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንዳሉ የተናገሩት አቶ አህመድ፤ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃርም ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው እስከ አሁን በከተማው ውስጥ ባሉት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ከስልሳ ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ ገልፀው፤ የዚህ ፋብሪካ መከፈትም ሌላ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ በፋብሪካው ውስጥ የሥራ ዕድል ከሚፈጠርላቸው ዜጎች በተጨማሪ ምርቱ በገበያ ሥርዓት ውስጥ ሲገባ ለዜጎች ሌላ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
የደቡባዊና ምሥራቃዊ አፍሪካ የኮካ ኮላ ንግድ ሕብረት ፕሬዝዳንት ቡርኖ ፔትሪሺያ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፋብሪካው ለአካባቢው ማህበረሰቦች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ችግኞችን በመትከል የወዳደቁ ፕላስቲኮችን ዳግም ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢን የመጠበቅ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የኮካ ኮላ ፋብሪካ ከአሁን በፊት በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋ እና በባህርዳር ከተሞች ተገንብቶ ምርት እየሰጠ ሲሆን፤ እስከ አሁንም ከ2 ሺ ሁለት መቶ የሚበልጡ ቋሚ ሠራተኞ አሉት፡፡ አሁን በሰበታ በግንባታ ሥራ ላይ የሚገኙ ከሦስት መቶ በላይ ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡ ካምፓኒው በቀጣይም በሀዋሳ ከተማ ሌላ የማስፋፊያ ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንዳለም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ኢያሱ መሰለ