– በሕገወጥ መንገድ ሲመነዘር የተገኘ 15 ሚሊየን 906 ሺ ብር በቁጥጥር ሥር አዋለ
– ለ13 ሺ 649 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠረ
አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በመዲናዋ ባደረገው ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ቁጥጥር 13 ሺ 800 ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር 15 ሚሊዮን 906 ሺ 858 ብር በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና ለ13 ሺ 649 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ መከታ አዳፍኔ እንዳብራሩት፤ ቢሮው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባደረገው ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ቁጥጥር 13 ሺ 800 ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ እነዚህ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ያለ ንግድ ፈቃድ፣ ያለ ደረሰኝ በመነገድ እንዲሁም ሚዛን በማጉደል፣ በህገ-ወጥ የምርት ክምችት በመሳሰሉት ህገወጥ ተግባራት ተሰማርተው የተገኙ ሲሆን፤ በ7 ሺ 654 ነጋዴዎች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 5 ሺ 588 ንግድ ድርጅቶችን የማሸግ፣ 249 ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ መሰረዝ፣ 70 ነጋዴዎች ንግድ ፈቃድ ማገድ፣ 239 ንግድ ድርጅቶችን ከትስስር የማስወጣት ሥራ ተሠርቷል፡፡ እንዲሁም 38 የምሽት ጭፈራ ቤቶች በድምፅ ብክለት እና 282 የንግድ ተቋማት ሺሻ በማስጨስና ጫት በማስቃም ተሰማርተው በመገኘታቸው የማሸግ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡
በ308 ሺ 152 የንግድ ድርጅቶች ላይ በድግግሞሽ የበር ለበር የህገ-ወጥ ንግድ ክትትል እና ቁጥጥር እንደተደረገ የጠቆሙት አቶ መከታ፤ በህጋዊ ንግድ ፈቃድ ሽፋን በጥቁር ገበያ የተለያዩ አገራት ገንዘብ ሲመነዝሩ የተገኙ 64 የንግድ ድርጅቶች በግብረ-ሃይል የማሸግ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዶባቸው ወደ ሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተለያዩ አገራት ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ብር ሲቀየር 15 ሚሊየን 906 ሺ 858 ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም 31 ሺ 181 ሊትር የድጎማ ፓልም ዘይት፣ 372 ነጥብ 53 ኩንታል ስኳር፣ 30 ኩንታል ስንዴ ዱቄት እና 24 ሺ 815 ሊትር ቤንዚን እንዲሁም 544 ነጥብ 9 ኩንታል ለውጭ ገበያ የሚውል ቡና በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩና ተከማችተው በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ መንግሥት ገቢ ተደርገዋል ብለዋል።
204 ኩንታል ከጤፍ ዱቄትጋር የተደባለቀ ጄሶ በቁጥጥር ስር ውሎ ወንጀለኛው ለሕግ እንደቀረበ የጠቆሙት አቶ መከታ፤ 501 ኪሎ ግራም በሕገ- ወጥ መንገድ የታረደ የበሬ ሥጋ ሲዘዋወር ተይዟል፡፡
14 ሺ 328 ራኒ ጁስ እና 14 ሺ 581 ልዩ ልዩ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች የአገልግሎት ጊዜያቸው አልፎባቸው በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው እንዲወገዱ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም ከህጋዊ ንግድ ፈቃዳቸው ውጭ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 92 ደላሎች እና 41 ኤጀንሲዎች ላይ ከሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር አስተዳደረዊ እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተደረገ የኮንትሮባንድ ክትትልና ቁጥጥር በርካታ ምርቶች በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ 113 የሺሻ ዕቃዎች፣ 95 ቦንዳ ሺሻ፣ 627 ፓኬት ሲጋራ፣ 14 ብርድልብስ፣ 50 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ እና 13 እሽግ ኒዶ ወተት በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ መከታ አክለው ገልፀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በከተማችን የሚስተዋለውን መደበኛ ያልሆነ ንግድ ሥርዓት ለማስያዝ በጎዳና ንግድ ላይ ለተሰማሩት ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በማሳደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛው ንግድ እንዲቀላቀሉ ፖሊሲ፣ ደንብ እና መመሪያ አውጥቶ ወደ ተግባር ገብቷል ያሉት አማካሪው፤ በዚሁ መሰረት እስካሁን 32 ሺ 906 ዜጎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 13 ሺ 649 ያህሉ አስፈላጊው ቅድመ ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ሶሎሞን በየነ