አዲስ አበባ፤- 143 ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ይከሰታል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 43ቱ ከፍተኛ ስጋት ያለባቸው በመሆኑ በቅርቡ አስፈላጊው ዝግጅት እንዲደረግ ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸው ተጠቁሟል። የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የብሔራዊ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና አስቸኳይ ግዜ ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚጥል 143 ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ይከሰታል ተብሎ ይገመታል።
ከነዚህ ውስጥም 43ቱ ከፍተኛ ስጋት ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 126 አካባቢዎች ደግሞ የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ይችላል ተብሎ ተለይተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ችግሩ ይከሰትባቸዋል ተብሎ ስጋት ያለባቸውን ቦታዎች በመለየትና ታሪካዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ የጎርፍ መከላከያ ፕላን እየተዘጋጀ ይገኛል። ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑት እንደ ቤት፣ መድሀኒትና የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ቀድመው ተለይተው በገንዘብ ተሰልተው መዘጋጀት አለባቸው።
በመሆኑም ምን ያህል ሰው ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆን ይችላል? ምን ያህል ሰው ሊፈናቀል ይችላል? የሚለውን በመገመት በየዘርፉ በግብርና፣ በጤና፣ በተፋሰስና ሌሎችም ዘርፎች ተገቢው ዝግጅት እንዲከናወን እየተደረገ ይገኛል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ በበልግ ወቅት በሚያዚያ ወር አካባቢ ከፍተኛ ዝናብ በጣለባቸው ቦታዎች ተከስቶ ስለነበር ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር የጎርፍ መከላከል ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ከሚያዚያ ጀምሮ የመጀመሪያውን ማስጠንቀቂያ በማውጣት ሲሰራ ቆይቷል።
በተጀመረው ክረምትም ከብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ በተገኘው መረጃ መሰረት ተመሳሳይ ችግር ሊደርስባቸው ይችላል ተብለው የተለዩ ቦታዎች በመኖራቸው ግብረ ሀይሉ በድጋሚ ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል።
እንደተሰጋው ችግሩ ከተከሰተም በፍጥነት ለመድረስ በክልሎች በኩል የተዘጋጀው ብላን ኮፒ የሚላክ ሲሆን በዛ መሰረት እያንዳንዱ ክልል የየአካባቢን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የራሳቸውን እቅድ በማከል መከላከያ ግብረ ሀይል አቋቁመው ወደስራ የሚገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ