መጪው ክረምት እና የጎርፍ ስጋት!

ዝናብ ከዘነበ ጎርፍ የማይቀር ተፈጥሯዊ ክስተት በመሆኑ የሰው ልጅ ጎርፍን ሊቆጣጠረው እንጂ ሙሉ በሙሉ ሊያስቆመው አይችልም። ጎርፍ ተፈጥሯዊ ክስተት ቢሆንም በጎርፍ አደጋ ምክንያት የሰዎች ሕይወት እንዳያልፍ፤ አርሶ አደሮች የዘሩት አዝመራ በጎርፍ እንዳይወሰድ እና ንብረት እንዳይወድም መጪው የክረምት ወራት ከመድረሳቸው በፊት ከወዲሁ የመከላከል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።

በተለያዩ አካላት ቸልተኝነት የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ስለሚደፈኑ እና ቅድመ ጥንቃቄ ስለማይደርግ እንጂ ኢትዮጵያ የአየር ንብረቷ ተስማሚ ስለሆነ በአንጻራዊነት ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ ተመጣጣኝ ዝናብ ስለሚዘንብና በመሬት አቀማመጧ ምክንያት ከሌላ ሀገር በሚመጣ ጎርፍ ስለማትጠቃ ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ የጎርፍ አደጋ እምብዛም ሊያሰጋት አይገባም ነበር።

ለአብነት ሱዳንና ግብፅ ብንመለከት ክረምት በመጣ ቁጥር ከላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በሚዘንብ ዝናብ ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ ጎርፍ ስለሚያጥለቀልቃቸው ለበርካታ ሰዎች ሞት እና ከፍተኛ መጠን ላለው ንብረት ውድመት እንደሚጋለጡ በተደጋጋሚ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ተመልክተናል።

የኢትዮጵያ አጎራበች የሆነችው ኬንያ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጎርፍ ተወስደዋል፤ በታንዛኒያም እንዲሁ ለሳምንታት በተከታታይ በጣለው ከባድ ዝናብ በደረሰው የጎርፍ አደጋና የመሬት መንሸራተት የበርካታ ዜጎች ህይወት አልፏል፤ ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ የተለያየ አይነት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም በተመሳሳይ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ የብዙ ሰዎች ህይወት ማለፉን፤ ከፍተኛ ቦታዎች በሚያጋጥማቸው ናዳ በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ያለ መጠለያ መቅረታቸውን፣ መንገዶች፣ ድልድዮች እና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች እየወደሙ መሆናቸውን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ሁላችንም ሳንመለከት የቀረን አይመስለኝም።

አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች ያደጉ ሀገራትም ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ጎርፍ የብዙ ሰዎችን ሕይወት በአልታሰበ ሁኔታ ሲቀጥፍ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ሲወድም፤ ሕንፃዎቻቸው ፈራርሰው የነፍስ አድን ሰዎች ሲረባረቡ፤ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ፈራርሰው ሰዎች ያለመጠለያ ሲቀሩ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲዘገብም አስተውለናል። ለጎርፍ አደጋ አባባሽ የሆኑ ምክንያቶችን በመከላከል የሰው ሕይወትን ከሕልፈት፣ ንብረትን ከውድመት ማዳን ይቻል እንደሆነ እንጂ ጎርፍን ማስቆም እንደማይቻል እነዚህ ያደጉ ሀገራት ማሳያ ናቸው።

በእርግጥ በእኛ ሀገር መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም በ1998 ዓ.ም ከደጋማው የሀገሪቱ አካባቢ በጣለው ዝናብ የድሬዳዋ ከተማ በጎርፍ ተጥለቅልቃ የብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን እናስታውሳለን። የጎርፍ አደጋው የደረሰው በሌሊት መሆኑ ደግሞ አደጋውን የከፋ አድርጎት እንደነበረም ብዙዎቻችን የምናስታውስ ይመስለኛል።

በተለይ በምሥራቁ ሀገሪቱ ክፍል የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ እየሞላ አቅጣጫውን ስለሚስት በዝቅተኛው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን እና እንስሳትን እንደሚወስድ፤ በማሳ የተዘሩ ሰብሎችን እንደሚያጥለቀልቅ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት እንደሚያወድም እና ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ያለመጠለያ እንደሚያስቀር በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃን ስለምንሰማ ዘንድሮም ችግሩ እንዳይከሰት ከወዲሁ የመከላከል እና ጥንቃቄ የማድረግ ሥራ ሊሠራ የሚገባ ይመስለኛል።

በአደጉት ሀገራት ጎርፍ ከቁጥጥራቸው ውጪ ሆኖ የዜጎቻቸውን ሕይወት የሚቀጥፍ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት የሚያወድም ከሆነ ለአፍሪካ ሀገራት ምን ያህል ፈተና ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ መፍትሔው መከላከልና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ነው ።

ለኢትዮጵያ ፈጣሪ ሁሉንም የአየር ንብረት አስተካክሎ የሰጣት በመሆኑ የክረምት ወራት ከመምጣታቸው በፊት የመከላከል እና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ቢሰሩ ጎርፍ ለኢትዮጵያ እምብዛም ስጋት የሚሆኑት አይደለም። ነገር ግን ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች በሚፈጥሩት ቸልተኝነት ከዛም በላይ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ለችግሩ በቂ ትኩረት ሰጥተው አለመስራታቸው ክረምት በገባ ቁጥር የጎርፍ አደጋ ተከስቶ የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ይወድማል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የበልግ ወቅት ነው። ከዚህ ወር በኋላ ደግሞ የአብዛኛው ሀገራችን ክፍል የክረምት ወቅት በመሆኑ ጎርፍ ጥፋት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ሥራ በመሥራት፤ የሰዎችን ሕይወት ከሕልፈት፣ ንብረትን ከውድመት ለመታደግ የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ የሚጠበቅባቸው ሥራ መሥራት አለባቸው።

በአዲስ አበባና በሀገሪቱ አንዳንድ ክልሎች ንፋስ እና በረዶ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ በማሳ ላይ ያለ ሰብል መወሰዱንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት ማውደሙን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሲዘዋወርም አስተውለናል።

የአየር ትንበያ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖር ስለሚጠቁሙ ሊከሰቱ ከሚችሉ አደጋዎች ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የሚመለከታቸው አካላት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር የጥንቃቄ መልዕክት በማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል።

ግለሰቦችም ለጎርፍ አደጋ አባባሽ የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ የሰዎችን ሕይወት ከሕልፈት፣ ሰብልና ንብረትን ከወድመት የማዳን ግለሰባዊ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። ከቁጥጥር ውጭ ከሆነም የሰው ሕይወት እንዳያልፍ፣ በሰብል እና በንብረት ላይ ጥፋት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።

ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመተባበር በወንዝ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት በማስተላለፍ የሰዎችን ሕይወት ከሕልፈት፣ ሰብልና ንብረትን ከውድመት ለማዳን በትኩረት መሥራት ያለባቸው ይመስለኛል።

የሰው ልጅ የየአካባቢውን የአየር ንብረት ተቋቁሞ እና ተቆጣጥሮ ለመኖር ፈጠሪ ፀጋ ቢያድለውም ከቁጥጥሩ ውጪ ከሆነ ደግሞ ጥንቃቄ ማድረግ ሌላው ከፈጣሪ የተሰጠው ፀጋ መሆኑን በመገንዘብ ዝናብ ሲዘንብ በሚፈጠረው ጎርፍ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። ጥንቃቄ ካላደረገ ግን የሰው ልጅ ከፈጣሪ የተሰጠውን ፀጋ አልተጠቀመበትም ማለት ይቻላል።

ስለዚህ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” እንደሚሉት እንዳይሆን በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋ ጥፋት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን ማጽዳት እና ከቁጥጥር ውጪ ከሆነም ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን መጠንቀቅ ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር መሆን ይኖርበታል።

አንዳንድ ሰዎች በቸልተኝነት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጨለማ ተገን አድርገው ወይም በጠራራ ፀሐይ በማን አለብኝነት ወደ ጎርፍ መውረጃ ቦዮች በሚጥሏው የውሃ ኮዳዎች፣ የጫት ገራባዎች፤ የቤት ጥራጊዎች፣ ሌሎች ጠጣር ነገሮች እና የመሳሰሉት ቆሻሻዎች የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ስለሚደፈኑ ለጎርፍ አደጋ መከሰት ምክንያት ይሆናሉ።

አበው “ሥራ ለሠሪው፤ እሾህ ለአጣሪው” እንዲሉ እነዚህ ወደ ጎርፍ መውረጃ ቦዮች በየቀኑ የሚጣሉ ቆሻሻዎች የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን ስለሚደፍኑ በድንገት ዝናብ ሲጥል ጎርፉ አቅጣጫውን ስቶ በአስፋልት በመፍሰስ ብዙ ጥፋት ያደርሳል። ጎርፉ ለጊዜው ጥፋት ባያደርስ እንኳን የሰዎችን እንቅስቃሴ ስለሚገታ ሌላ ያልታሰበ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል።

ለምሳሌ በጎርፍ ምክንያት መንገድ ቢዘጋ የታመመ ሰው ይዞ ሲጓዝ የነበረ አምቡላንስ ሕመምተኛውን ወደ ሚፈለገው ጤና ተቋም ማድረስ ስለማይችልና በከተማው ውስጥ የእሳት ቃጠሎ ቢነሳ ባለሙያዎቹ በወቅቱ ደርሰው እሳቱን ማጥፋት ስለማይችሉ የጎርፍ አደጋው በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለንብረት መውደም ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ “የጨው ክምር ሲናድ ሞኝ ይልሳል፤ ብልህ ያለቅሳል” እንደሚባለው እንዳይሆን በመጪው ክረምት የጎርፍ መውረጃ ቦዮች እንዳይዘጉ ሁሉም ሰው ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ፤ ተዘግተው ከሆነም ማጽዳት የሁሉም ሰው ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

በከሞቻችን ያለው ነዋሪ ጥግግት ከፍተኛ ስለሆነ የጎርፍ አደጋው የሚያደርሰው የጥፋት መጠንም ሊጨምር ስለሚችል ለከተሞቻችን የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ያ ሲባል ግን ጎርፍ በገጠር አካባቢዎች የሚያደርሰው ጥፋት ቀላል ነው እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ስለዚህ በወንዝ አካባቢ የሚኖሩ የገጠርም ሆኑ የከተማ ነዋሪዎች በተለይ በክረምት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

“ያልቃል ማለት በበጋ፣ ይመሻል ማለት በማለዳ” እንዲሉ አበው የሚመለከታቸው አካላት ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን በማጽዳት እና በጎርፍ መውረጃ ቦዮች ቆሻሻ እንዳይጣል የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክት በማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡም ይገባል።

በአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ደግሞ ከብት የሚያግዱ ሕፃናት ከብቶቻቸውን ውሃ ለማጠጣት፤ ሌሎች ሰዎችም በወንዞች አካባቢ የተለያዩ ሥራዎችን ሲያከናወኑ በደራሽ ውሃ የሰዎች ሕይወት ሊቀጥፍ፤ ንብረት ሊያወድም ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው በየጊዜው መልዕክት ማስተላለፍ ያስፈልጋል።

በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋ ተከስቶ የሰዎች ሕይወት እንዳያልፍ፤ ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት እንዳይወድም መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር በመሥራት የጎርፍ አደጋ የሚያደርሰውን ጥፋት ከወዲሁ መከላከልና የጥንቃቄ መልዕክት ማስተላለፍ አለባቸው በማለት የዛሬውን አበቃሁ። ቸር እንሰንብት!

ጋሹ ይግዛው (ከወሎ ሠፈር)

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You