ከዘመኑ የተፋቱ አገልግሎቶች

ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን፤ በቴክኖሎጂ ሥርዓት ውስጥ ማለፍ ግድ ይላል። ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀድመው የሄዱና ብልጽግናን ያረጋገጡ ሀገራት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

ኢትዮጵያም አልረፈደም ብላ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጋ መሥራት ከጀመረች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያን የመፍጠር ጉዞ ከተጀመረበት ማግሥት ጀምሮ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችም ይበል የሚያስብሉ ሆነው እየታዩ ነው። የማይቻል ይመስል የነበረው ነገር ሁሉ ተችሎ በተቃራኒው በነበረው የመጠቀም ነገር ነውርነቱ እየታየ መጥቷል።

ለአብነትም በ2015ዓ/ም ማብቂያ ላይ የነዳጅ የክፍያ ሥርዓት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ እንዲፈጸም እንደሀገር ሲወሰን ነገሩን በአዎንታዊ ከማየት ይልቅ አሉታዊ ጎኑ አመዝኖ የተፈጠረው ብዥታ አይዘነጋም። እንደ ውሃ፣ መብራት የመሳሰሉ አገልግሎቶችም በተመሳሳይ ገንዘብ አልባ በሆነ የአከፋፈል ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ሲደረገም ቅብሉነቱ ላይ ተግዳሮቶች ነበሩ። ብዙዎች እንዴት የሚል ጥያቄ ነበራቸው። የባንክ አሠራር ለውጥ ላይም እንዲሁ ምቾት ያልተሰማቸው እንደነበሩ ማስታወስ ይቻላል።

ዛሬ የኤሌክትሮኒከስ ግብይቱ ለትራንስፖርት ከፍሎ ቢሮ ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ በእጅ ስልክ ባሉበት ቦታ ሆኖ ክፍያን በመፈጸም ጊዜና ገንዘብን ማትረፍ፣ ድካምን ማስቀረት ተችሏል። ገንዘብ ተሸክሞ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለስርቆት እንዳረግ ይሆን የሚለውን ስጋትም እንዲሁ አስቀርቷል።

እንደሀገርም ኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን መጠቀም መጀመሯ፣ የለውጥ እንቅስቃሴውም ብዙዎችን በማበረታታቱና በመስፋፋቱ በዓመት እስከ አራት ትሪሊዮን የሚደርስ ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጭ እንዲዘዋወር ማስቻሉም ከፍተኛው ጥቅም ነው።

ይህን መልካም ዜና ያበሰረን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ ወደ 170 የሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ ገብተዋል። ይሄ የቴክኖሎጂው አስፈላጊነትና ወደትግበራ ከተገባ በኋላም እያስገኘ ያለው ጥቅም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዋና ዓላማም በኢትዮጵያ አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚ ማልማት እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዲጂታል ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ጉዞ በሌሎችም ሀገሮች ትብብር፣ ድጋፍና ማበረታቻ እያስገኘ ነው። ዲጂታል ኢትዮጵያን የመፍጠሩ ጉዞ እንዲሳካ የአውሮፓ ህብረት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በቴክኒክና በገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ከዚህ ሁሉ ጎን ለጎን ደግሞ የመንግሥት፣ የባለድርሻ አካላትና የማህበረሰብ የጋራ ትብብር ወሳኝ እንደሆነ ደግሞ መዘንጋት የለበትም። ከአስተሳሰብ ጀምሮ ለውጡን መደገፍና የለውጡ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል።

በሂደት ላይ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት ትግበራ፤ ሙሉ ለሙሉ ስኬት ላይ ለመድረስ ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩትም ይታመናል። አሠራራቸውን ወደ ዲጂታል ቀይረው ከወረቀት አልባ አሠራር የተላቀቁ ሀገራት በአንድ ጀንበር ሳይሆን በሂደት ብዙ ፈተናዎችን አልፈው፣ ብዙ ሥራዎችን እንደሠሩም ይታወቃል። አንዳንድ አሠራሮች ግን ጊዜ ሳይወስዱ መስተካከል ያለባቸውና ዲጂታል ኢትዮጵያ የመፍጠሩን ጉዞ እንዳያውኩ ማስተካከያ ሊደርግባቸው ይገባል።

ለዚህ በርካታ መሣያዎች አሉ። አሁን ላይ ስለቴክኖሎጂው ጥቅም ግንዛቤ እያገኘንና መጠቀምም በመጀመራችን ለቀደመው አሠራር ፍላጎት እያጣን ብቻ ሳይሆን፤ ትእግሥትም የሚያሳጣ አሠራር ሆኖብናል። በግሌ ኋላቀር አሠራር ምን ያህል ተዋህዶን እንደነበርም አሁን ላይ ነው የተገነዘብኩት።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ከደንበኞቹ ጋር ውል ለማደስ፤ ባደረገው ጥሪ ላይ ያስተዋልኩት ጉዳይ ነው ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝ። ተቋሙ ውል ለማደስ እየተጠቀመ ያለው አሠራር የቀድሞ አሠራርን የተከተለ ነው። ክፍተቱ ለደንበኞቹ ጥሪ ከማድረስ ይጀምራል።

ተቋሙ ደንበኞቹን በመረጃ ተደራሽ ለማድረግ ቀድሞ መሥራት የነበረበትን ሥራ አልሠራም። ደንበኛው በሰሚስሚ ወደ ተቋሙ በሚሄድበት ወቅትም የተሟላ መረጃ ይዞ ባመለቅረቡ ሁለቴ ሶስቴ የሚመላለስበት ግዴታ ነበረበት።

እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ነው የታዘብኩት። አንዱ ደንበኛው ተራውን ለማወቅ የግድ ተቋሙ ድረስ መሄድ ይጠበቅበታል። በአጋጣሚ የተራው ቀን ካልሆነ ለሁለተኛ ጊዜ መሄድ ይጠበቅበታል ማለት ነው። በቀኑ ሄዶ ያልተሟላ ነገር ቢኖርና ወረፋም ከበዛ ለሶስተኛ ጊዜ ሊሄድ ይችላል። ሌላው የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ደንበኛ ሊያየው በሚችለው ግልጽ ቦታ ሳይሆን በቢሮ ግድግዳ ላይ ነው ተደብቆ የተለጠፈው።

ለእኔ ትልቁ ስህተት መስሎ የታየኝ ነገር ቢኖር ደግሞ ተቋሙ ለደንበኞቹ ለውል ማዋዋያ ብሎ ያዘጋጀው ፎርም የፎቶ ኮፒ አገልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች እጅ ሆኖ ደንበኛው በገንዘብ ኮፒውን ገዝቶ እንዲያቀርብ መደረጉ ነው። ይህ ኮፒ በአንዱ የድርጁቱ ቅርንጫፍ በ50 ብር፤ በሌላኛው የድጅቱ ቅርንጫፍ ደግሞ በ30 ብር ነው የሚሸጠው። ይሄን በአካል ያረጋገጥኩት ነው።

ይሄን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቱ ማቅረብ የሚገባው ሆኖም ደንበኛው እንዲያቀርብ የተገደደበትን መረጃዎች እየተመላለሱ ኮፒ ማድረግ ግዴታ ነው። በሌሎች የድርጅቱ ቅርንጫፎች የጠየቀውን ኮፒ በራሱ አሟልቶ አገልግሎት የሰጠ የድርጅቱ ቅርጫፍ መኖሩንም ከቅርብ ወዳጄ ሰምቻለሁ። በአንድ ተቋም ውስጥ እንዲህ ያለ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ለመፈጠሩ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ቴክኖሎጂን የተከተለ አሠራር ባለመተግበሩነው።

ተቋሙ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ውል ማደስ ነው። ደንበኛው መታወቂያውንና ከድርጅቱ ጋር ውል የገባበትን መረጃ ማቅረብ ብቻ በቂ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ተቋሙ በዚህ የውል ማደስ የቀድሞ አሠራሩን ነው የደገመው። ምክንያቱም ደንበኞች በኮፒ ማስረጃ እንዲያቀርቡ የጠየቁት ወረቀት ተሰብስቦ ተቀመጠ እንጂ ወደ ዲጂታል የተቀየረ ነገር አላየሁም። ተቋሙ የውል ማደሱን ሥራ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ እንደሚያከናውን ነው ያስታወቀው። እንደአያያዙ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ የሚያጠናቅቅ አይመስለኝም።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ለአብነት አነሳሁ እንጂ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ላይም ተመሳሳይ ክፍተት አስተውያለሁ። እዚህ ተቋም ላይ ደግሞ ያጋጠመኝ፤ የስም ዝውውር ነው። ደንበኛው ስሙን ለማዘዋወር 1780 ብር ይከፍላል። ይህ ሲያደርግ ግን ደንበኛው ተመላልሶ ኮፒ እንዲያደርግ ይገደዳል። የማስፈፀሙንም ተግባር ደንበኛው ነው ያከናወነው።

አንደኛ የከፈለው ክፍያ የደንበኛውን ተጨማሪ የኮፒ ክፍያ አላስቀረለትም። ሁለተኛ ደንበኛው በተቋሙ ሠራተኞች ሥራው ሊጠናቀቅ ሲገባው ኃላፊ ጋር ቀርቦ ማስፈረምና መዝገብ ቤት ሄዶ ማህተም የማስደረግ ሥራው የተገልጋዩ ነው። አሠራሩም በዲጂታል ማለቅ ሲገባው ሙሉ ለሙሉ ከወረቅት ጋር የተያያዘ ነው።

እንዲህ ያሉ ተቋማት እራሳቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ለማሳለጥ የተቋማትን አሠራር አብሮ ማራመድ ይገባልና ዘልማዳዊ አሠራርን የሚከተሉ ተቋማት ቢፈተሹ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You