ዛሬም በአፍካዋ መዲና አዲስ አበባ ንጋት ላይ በየመንገዱ ጥጋ ጥግ ላስቲክ ለብሰው ያሸለቡ ወገኖች ማየታችን አልቀረም፡፡ እንደትላንቱ በየ መንገዱ ያደፈ ሹራብ ለብሰው በእጅጊያቸው ብልቃጥ አልያም ደግሞ የሃይላንድ ላስቲክ በመሸጎጥ ቤንዚን እየሳቡ አካልን የሚቆራርጠው ብርድ እንዳይሰማቸው በባዕድ ነገር እራሳቸውን የሚያደነዝዙ ለጤናቸው አስጊ የሆነና ንፅህናው ያልተጠበቀ ምግብ ተናጥቀው የሚበሉ የጎዳና ልጆችን መመልከታችንን ቀጥለና፡፡
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት በኩል ለእነዚህ ወገኖች መልካም ነገር መታሰቡ ተሰምቶ ነበር፡፡ ከ50 ሺ ያላነሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚኖሩባት አዲስ አበባ፤ አዲስ መላን ዘየድኩ በቋሚነትም ላቋቁማቸውና ወደ ማዕከል ልሰበስባቸው አሰብኩ ማለትዋና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማደረግ መጀመርዋን ይፋ አድርጋለች፡፡
በተለያዩ ማዕከላት ገብተው የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎች በመውሰድ አምራች ዜጋ ይሆናሉ የተባሉና ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች “የተያዘውና የታሰበውን አላማ በሚያሳካ መልክ አልተያዝንም! የሚገባንን አገልግሎት ከማግኘት ይልቅ በደል እየደረሰብን ነው፡፡” በማለት በአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
አስኮ ብርጭቆ ፋብሪካ ሚኪሊላንድ ሳይት ቁጥራቸው ከ125 የማያንሱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰባስበው የከተሙበት ነው፡፡ ከዚሁ የማቋቋሚያ ማዕከል ተወክለን ተገኝተናል ያሉ ቁጥራቸው 52 የሚደርሱ ወጣቶች በማዕከሉ ውስጥ የሚደርስባቸው በደል በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ሰሚ ማጣቸውን ይናገራሉ ፡፡
ወጣት በረከት ሽመልስ ችግራቸውን ለቢሮው ለማቅረብ ከቀረቡት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ ጎዳና ተወልዶ ማደጉን የሚናገራው በረከት የከተማ አስተዳደሩ አመቻቸሁት ባለው ዕድል የመጠቀምና የመለወጥ ትልቅ ተስፋ እንደነበረውና አሁን በቦታው ያለው ሁኔታ ተስፋ አስቆርጦት ድጋሚ ጎዳና ማሰብ መጀመሩን ይናገራል፡፡
በሚኖርበት ሚኪሊላን ካምፕ መሰረታዊ ፍላጎት ተሟልቶ ማግኘት ብርቅ ሆኖብናል ያለው በረከት “የሚመለከተው አካል ያለብንን ችግር ተረድቶ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል” በማለት ቅሬታውን ያቀርባል፡፡ ወጣት በረከት ብዙ ጓደኞቹ በካምፕ ውስጥ ያለው አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም አቅቷቸው ወደ ጎዳና መውጣታቸውና አሁን ያሉትም በጊዜው ቁጥራቸው እየቀነሰ መሆኑንም ይናገራል፡፡
ወጣቶቹ በተጨማሪም የሚቀርብላቸው አልባሳትና መገልገያ ቁሳቁሶች የተሟሉ ካለመሆናቸው በተጨማሪ የምግብ የውሃ አቅርቦት፣ የመኖሪያ (ማደሪያ ቤት) ንፅህና ችግር በማዕከሉ ውስጥ የገጠማቸው ዋንኛ ችግር መሆኑን ይዘረዝራሉ፡፡
ሽመልስ ጫላ ከ4 ወር በፊት ጎዳና ላይ ከተኛበት “ህይወትህ ይለወጣል ስልጠና ተሰቶህ ትቋቋማለህ” በሚል የተስፋ ቃል ኮተቤ በሚገኝ የማቆያ ካምፕ እንደገባ ይናገራል፡፡ “አሁን ካለሁበት በተሻለ ጎዳና ላይ ምቾት ነበረኝ፡፡” የሚለው ወጣት ሽመልስ፤ ከመሰረታዊ ፍላትና አገልግሎት መጓደል በተጨማሪ የሚሰጣቸው ስልጠና ፍላጎታቸውን ያላማከለ መሆኑን ይገልፃል፡፡
ወጣት ሽመልስ አክሎም በሚኖርበት ካምፕ ለጤናቸው አስጊ መሆኑንና ንፅህናው የተጠበቀ የመጸዳጃና መታጠቢያ ቤቶች እንደሌሉ ይናገራል፡፡ ከመንግሥት የተመደበልን በጀት እና በትክክል እየደረሰን አይደለም የሚለው ሽመልስ በተደጋጋሚ ችግሮቻችንን ለሚመለከተው አካል ብናቀርብም መፍትሄ ከማቅረብ ይልቅ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ይናገራል፡፡
በቢሮው ቅጥር ግቢ ውስጥ በመገኘት ወጣቶቹን ያነጋገሩት የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አለሙ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብም መረጃ መስጠት እንደማይችሉና ከከንቲባው ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሰክሬተሪያት ስለጉዳይ ጠይቆ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬትሪያት በበኩሉ ለፕሮግራሙ የሚሆኑ ፈንዶች ማፈላለግና ትረስት ፈንዱን መምራት ላይ እንደሚሠራ ገልፆ ዋንኛው የሥራው ባለቤት የአዲስ አበባ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መሆኑን ገልፆአል፡፡
በተጨማሪም ለችግር ተጋልጠናል ያሉት ወጣቶች በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ተገኝተው ያለባቸውን ችግር በዝርዝር ቢያቀርቡም ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማው ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስለሆነ ጥያቄያቸውን እዚያው አቅርቡ መባላቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011
ተገኝ ብሩ